Thursday, December 27, 2012

ታኅሣሥ ገብርኤል


ገብርኤል ማለትእግዚእ ወገብር” -የእግአብሔር አገልጋይ ማለት ነው። ፍጥረታት መፈጠር በጀመሩበት በዕለተ እሑድ እግዚአብሔር መላእክትን ከፈጠራቸው በኋላ ተሰወራቸው  መላእክትምመኑ ፈጠረነ፡ ማን ፈጠረንሲሉ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ ብሎ መላእክት በተረበሹ ጊዜየፈጠረንን አምላካችን እስክናውቅ በያለንበት ጸንተን እንቁም”  ብሎ ያረጋጋቸው መልአክ ነው። በዚህም ምክንያት ጌታበእንተዝ ይደልዎ ከመ ይጹር ዜናሃ ለማርያምእንዲል ሥጋዌውን ለድንግል እንዲያበስር አድሎታል። ከዚህም በኋላ ደጋግ ሰዎችን ለመርዳት የሚወጣ የሚወርድ ሆኗል።ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በተረዳኢነቱና በአማላጅነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ ይወደዳል፡፡ ምክንያቱም ያዘኑትን ለማጽናናት የምሥራች ለመንገር ከእግዚአብሔር ወደ ምእመናን ይላካልና፡፡
በዚህም ዕለት በታህሳስ 19 እግዚአብሔር አገልጋይ የሆኑትን አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን ከእቶነ እሳት አድኗቸዋል። (ትንቢተ ዳንኤል ዕራፍ 3)
ነገሩ እንደዚህ ነው -

Thursday, December 20, 2012

የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 3

ምንኵስና በኢትዮጵያ
ከ4ኛው መ/ክ/ዘ በፊት
ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ሀገራችን የገባው በኢትዮጵያ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአባ ጳኩሚስ ዘመን ቢሆንም የብሕትውና ኑሮ ግን በሀገራችን ከዚያም ቀድሞ እንደነበረ የሚጠቁሙ አንዳንድ መረጃዎች አሉ፡፡
አባ አሞንዮስ፡- ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት አሞንዮስ የተባሉ ባሕታዊ በተንቤን ቆላ ደብረ አንሣ በተባለው በረሃ በጾም በጸሎት ተወስነው ይኖሩ ነበር፡፡

Thursday, December 13, 2012

የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 2

2. የሥርዓተ ምንኩስና ታሪክ

 2.1   - አባ ጳውሊ  እና  አባ እንጦንስ
    2.1.1-  አባ ጳውሊ
አባ ጳውሊ  እና  አባ እንጦንስ
በተባሕትዎ መኖር ከጥንት ዘመን የመጣ ይሁን እንጂ የብሕትውናን ኑሮ ሥርዓት በወጣለት መልኩ የጀመረው አባ ጳውሊ የተባለው ግብፃዊ አባት ነው፡፡ በንጉሥ ዳክዮስ ዘመነ መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ በተነሣው ስደት ምክንያት አባ ጳውሊና ቆይቶም ደግሞ ሌሎች የአካባቢው ክርስቲያኖች በግብፅ በረሃዎች ውስጥ በምናኔ ይኖሩ ነበር፡፡
ይህንን አባ ጳውሊ የጀመረውን ሥርዓት አጠናክሮ ለማስፋፋት ያበቃው ደግሞ አባታችን አባ እንጦንስ ነው (251-356 ዓ.ም.)፡፡

  2.1.2- አባ እንጦንስ
አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ ቆማ በተባለች መንደር ከሀብታም ቤተሰቦች በ251 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወዳጆቹ ገና የ2ዐ ዓመት ወጣት እያለ ስላረፉ በማቴ.19÷21 ላይ ያለውን ትምህርት መሠረት አድርጐ የወረሰውን ሀብት በሙሉ በመሸጥ ለድኾች አከፋፈለና ወደ ግብፅ በረሃ በመውረድ ለ85 ዓመት በተጋድሎ ኖሯል፡፡

Thursday, December 6, 2012

የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 1

1.አጀማመር
1.1 በሕገ ልቡና
የብሕትውና ኑሮ የተጀመረው ከሰው ልጅ ወደዚህች ምድር መምጣት አንሥቶ ነው፡፡ ደቂቀ ሴት ከቃየል ልጆች ኑሮና ግብር ተለይተው በደብር ቅዱስ በንጽሕና በቅድስና ይኖሩ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል( ዘፍ.6÷1-3፤ ሄኖክ 2÷1-2)
አባታችን ሄኖክም በዘመኑ ከነበሩት ግብረ ሰዶማውያን ርቆ፣ ሰዎችን ለጥፋት ውኃ ከዳረገው ኃጢአት ተለይቶ፣ ንጹሕ እግዚአብሔር ንጽሕናን ይሻል በማለት በሕገ ልቡና ተመርቶ በእግረ ገነት ለሰባት ዓመታት በብሕትውና ከኖረ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ከአካለ ሥጋ ወደ ብሔረ ሕያዋን መነጠቁን መጽሐፈ ሄኖክ ያስረዳል፡፡ የመልከ ጼዴቅም የኑሮ ሥርዓት ይህንኑ የባሕታውያን ሕይወት የተከተለ ነበር( ዘፍ.14÷17-24)፡፡

Tuesday, November 27, 2012

እምነ ጽዮን - እናታችን ጽዮን

እንኳን ለኅዳር ጽዮን በሰላም አደረሳችሁ
በቅዱሳት መጻሕፍት ጽዮን የሚለው ቃል ተደጋግሞ በነቢያቱ ተነግሯል፡፡ ሆኖም የጽዮን ትርጉም እንደተነገረበት ዐውደ ትንቢት እንደተሰበከበት መዋዕለ ትምህርት ምስጢሩ ይለያያል፡፡
ድንግል ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳ
 ታቦተ ጽዮን በፈቃደ እግዚአብሔር በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ለሰው ልጆች ተሰጥታ እስራኤላውያን ሲባረኩባት፣ መሥዋዕታቸውን ሲያቀርቡባት ከእግዚአብሔር ሲታረቁባት ኖረዋል፡፡ከአራት ሺሕ ሦስት መቶ ሃያ ሰባት ዓመተ ዓለም (4327 ዓ.ዓ.) ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያህል እስራኤላውያንን በክህነት ያገለግል የነበረው ካህኑ ዔሊ ዕድሜው ሲገፋ ሁለት ልጆቹን ጠርቶ ምሉዕና ዱግ /ዋናና ምክትል/ አድርጎ ሾማቸው፡፡
በደብተራ ኦሪት ታቦተ ጽዮንን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሁለቱ ወጣት ካህናት /አፍኒን እና ፊንሐስ/ ፈቃደ እግዚአብሔርን ተላልፈው ሦስት ታላላቅ በደሎችን ፈጸሙ፡፡ የመጀመሪያው በደል፤ በሙሴ ሥርዓት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርታ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት የምትጠፋ መብራት እንድትቀመጥ የተሠራ ሥርዓት ነበር፡፡ ሆኖም አገልግሎት ከሌለ ሲበራ ማደሩ ለምን ? ብለው መቅረዙን አነሡ፤ መብራቱንም አጠፉ፡፡ ሁለተኛ፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ለመሥዋዕት እንዲሆን ከመጣው እንስሳ ታርዶ ስቡ ሳይጤስ፣ደሙ ሳይፈስ ሥጋውን እየመረጡ ተመገቡ፡፡ሦስተኛ ጸሎት እናደርሳለን ሥርዓተ አምልኮ፣ እንፈጽማለን ብለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጡ ከነበሩት እስራኤላውያን ቆነጃጅት ጋራ በዝሙት ወደቁ፡፡ አባታቸው ካህኑ ዔሊም የልጆቹን በደል እያየ እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ቸል በማለቱ እግዚአብሔር አዘነ፡፡ በዚህም ምክንያት ፍልስጥኤማውያንን አስነሥቶ በጦርነት ቀጣቸው፡፡

Wednesday, November 14, 2012

የቤተልሔም ሕጻናት እና የራሔል እንባ


« እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክየይ ፤ ለሥራሽ ፤ ዋጋ ይሆናልና ፥ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ ፥ ይላል እግዚአብሔር ፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸዎ ይመለሳሉ። » ኤር ፴፮ ፥፲፭ ፡፡

የቤተልሔም ህጻናት በግፍ ሲገደሉ
ቅዱሳን ነቢያት የሚናገሩት ስለ ዘመናቸው ብቻ አይደለም ፤ ከዘመናቸው ጋር በማገናዘብ ስላለፈው ይናገራሉ ፥ ስለሚመጣውም ይተነብያሉ። ዓረፍተ ዘመን ሳይገታቸው ኃላፊያትንም መጻእያትንም ይተረጉማሉ። በመሆኑም ይህ ቃለ ኤርምያስ ወደኋላም ወደፊትም የሚሠራ ነው። ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ የባርነት ዘመን የነበሩበትን ዘመን ያስታውሳል ፥ ለፍጻሜው ደግሞ በዘመነ ሥጋዌ መባቻ ማለትም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የተፈጸመውን ያሳያል።

Tuesday, November 6, 2012

መልከ ፄዴቅ የክርስቶስ ምሳሌ ክፍል 2



ካለፈው ክፍል አንድ የቀጠለ

ታዲያ የጌታችን ክህነት በመልከ ፄዴቅ ክህነት ለምን ተመሰለ?

የነገር ጥላ አለውና” ዕብ 10እንደ ተባለ ለሰው ረቂቁን በግዙፉ  የሚታየውን በማይታየው መስሎ መናገርና ማስረዳት የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም እኛ የሰው ልጆች ከህሊናት በላይ የሆነውን እግዚአብሄርን መረዳት የቻልነው በምሳሌ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ ነበር፡፡ በዚህም አንፃር መልከ ፄዴቅ የወልደ እግዚአብሄር ምሳሌው እንጂ ራሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ምሳሌ የሆነውም መልከ ፄዴቅ ብቻ አልነበረም ፦ዮናስ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል ማቴ 16 ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው እባብ ዮሐ 314  ሙሴ ዉሃን ያፈለቀበት ዐለት 1ኛቆሮ 10እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሳሌወችም አሉት፡፡ 

ታዲያ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልከ ፄዴቅ የተመሰለበት ምክንያትም የሚከተሉት ናቸው ;- 

Tuesday, October 30, 2012

መልከ ፄዴቅ የክርስቶስ ምሳሌ ክፍል 1


ዕብራውያን 7: 1-10 “ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።…….”

          አብርሃምና መልከጼዴቅ እንደተገናኙ
ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ጠቀሰው
በታላቁ መምህር በገማልያል እግር ሥር በትሕትና የተማረው ምሁረ ኦሪት ቅዱስ ጳውሎስ ከደማስቆ ከተማ ተጠርቶ፣ ሕገ ወንጌልን ተቀብሎ፣ በሕገ ወንጌል ጸንቶ ለወገኖቹ ለዕብራውያን ባስተላለፈው መልእክቱ ስለዚህ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፣ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ (ዕብ.3÷1)፡፡

Sunday, October 7, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 2


የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
  የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን  አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

Thursday, October 4, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 1

የጾም ትርጓሜ
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ - ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ አንድም ጾም ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ይህም ኃጢአቱን ለማስተሰረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥራም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ፍት.ነገ.ፍት. መ. አንቀጽ 15564፡፡ በዚህ መሠረት ጾም ማለት ከጥሉላተ መባልዕት /ሥጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል እንዲሁም የአልኮል መጠጦች/ መታቀብ ነው፡፡
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለፈቃደ ሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ ሰው ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት ስንቅ ነው፡፡ ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣ የጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው፣ የጸሎት ምክንያት /እናት/፣ የእንባ መገኛ ምንጭ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡ /ማር. ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/፡፡

Monday, September 24, 2012

መስቀሉ የት ነው ያለው? ክፍል 2

መስቀሉ እንዴት ጠፋከዳንኤል ክብረት
የሀገራችን ሊቃውንት እና መዛግብት መስቀሉ እንዴት እንደ ጠፋ የሚተርኩት ታሪክ የጥንታውያኑን መዛግብት የተከተለ ነው፡፡ በመስከረም 16 እና 17 የሚነበበው ስንክሳራችን የጌታችን መስቀል በጎልጎታ በጌታችን መቃብር እንደነበረ ይተርክልናል፡፡ አይሁድ በመስቀሉ እና በመቃብሩ የሚደረገውን ተአምር አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውንም ያትታል፡፡ እስከ 64 ዓም አይሁድ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ 64 ዓም አካባቢ ግን አይሁድ ራሳቸውን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ዐመጽ ጀመሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡