Wednesday, November 30, 2011

ግብረሰዶማዊነት - ሊወገዝ የሚገባው ተግባር



በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን።የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን ። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን? ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ። መዝሙር 137:1-6


የጽዮንን በዓል በምናከብርበት በዚህ ሰሞን በታቦተ ጽዮን መገኛ ፤ በግማደ መስቀሉ ማረፊያ ፤ መድኃኔዓለም በስደቱ በጎበኛት ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የግብረሰዶማውያን ጉባኤ ሊዘጋጅ መሆኑ ሰሞኑን ይነገራል፡፡

መላእክት ሎጥን ከከተማው ካወጡ በኋላ እግዚአብሔር
ሰዶምና ገሞራን በእሳትና በዲን አጠፋ የሎጥ ሚስት
የጨው ሀውልት ሆነች
በዘመናት ታሪክ ውስጥ በእግዚአብሔር ዘንድ መጸጸትን፣ የቁጣ ጅራፍን፣ መዓትንና እጅግ መራራ ቅጣትን ካስከተሉ እኩያን ተግባራት መካከል ተፈጥሮ ከሚያዘው ውጪ ወንዶች ከወንዶችና ሴቶች ከሴቶች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ወይም ግብረ ሰዶማዊነት አንዱ ነው፡፡ ግብረ ሰዶማዊነት ስያሜውን ያገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ድርጊቱን በፈጸሙ ሕዝቦች አገር ስም ነው፡፡ ይህ ኃጢአት በተለይ በሰዶም ይበዛ ስለነበር ግብረ ሰዶም ተብሏል፡፡ ሰዶምና ጐረቤቷ ገሞራ በዮርዳኖስ ሸለቆ አካባቢ የተቆረቆሩ ከተሞች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ተግባር ከሞራልና ከተፈጥሮ ሕግ የወጣ አስጸያፊ ስለነበረ እግዚአብሔር የቁጣ በትሩን አሳርፎባቸዋል፡፡ /ዘፍ. 18-20/ ሁለት መላእክት ሎጥን ከከተማው ካወጡ በኋላ እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን በእሳትና በዲን አጠፋ፡፡ ዘፍ.12-10-26፡፡ በነዋሪዎቿ ጥፋት በእሳትና በዲን የተለበለበችው ሰዶም ዛሬ ሕይወት አልባ በሆነው ሙት ባሕር ተሸፍና እንደቀረች ይነገራል፡፡

“ታቦተ ጽዮን” ፤ “ኅዳር ጽዮን“ ፤ “አክሱም ጽዮን “


 ክፍል -2

የቀዳማዊ ምኒልክ ጉዞና የታቦተ ጽዮን መምጣት
ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ በ12 ዓመቱ ከእናቱ የተሰጠውን ለታቦተ ጽዮንና ለንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ንግሥት ሳባም ለንጉሥ ሰሎሞን “ንጉሥ ሆይ ልጄን ሙሴ የጻፋቸውን ሕግጋት ሥርዓተ ክህነት አስተምረህ ላክልኝ፡፡” የሚል መልእክት ልካ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በኢየሩሳሌም ከአባቱ ዘንድ ለሦስት ዓመት ያህል ቆይቷል፡፡  በዚሁ ዘመን መጻሕፍተ ሙሴን፣ ሕገ መንግሥትን፣ ሥርዓተ ክህነትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ከሊቀ ካህናቱ ከሳዶቅ ተምሯል፡፡

Monday, November 28, 2011

“ታቦተ ጽዮን” ፤ “ኅዳር ጽዮን“ ፤ “አክሱም ጽዮን “ ክፍል -1



       የታቦተ ጽዮን መንበር -አክሱም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት አንዱ “ኅዳር ጽዮን” ሲሆን የሚከበረውም ኅዳር 21 ቀን ነው፡፡ የበዓሉን አከባበር ፤ ጥንተ ታሪኩን፤ ንግስት ሳባ ፤ቀዳማዊ ምኒልክና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን በተከታታይ ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ 
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  “ታቦተ ጽዮን” የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ተአምራት ለምእመናን እያስተማረች በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡  “ታቦተ ጽዮን” የሚለውንም ስያሜ ያገኘችው ጽዮን ተብላ በምትጠራው የእስራኤል ከተማ ስም ነው፡፡ ጽዮን ማለት ተፀወነ፡- ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ክቡረ ዳዊትም ጽዮንን አምባ፣ መጠጊያ አድርጎ ብዙ ጠላቶቹን ተዋግቶ አሸንፎ ድልን ተጎናጽፏል፡፡

Friday, November 25, 2011

ቅድስት አትናሲያ


ባለፈው የዮሐንስ ሐጺርን ታሪክ ስንመለከት የቅድስት አትናስያን ታሪክ እንደማቀርብ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ከዚህ እንደሚከተለው የቅድስት አትናስያ ታሪክ በጣም በአጭሩ የቀረበ ሲሆን ሰፊ የሆነውን የቅድስት አትናስያን ታሪክ በተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል በሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል ፡፡

“መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፡ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፣  ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ፡- የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል፡፡ እላችኋለሁ እንዲሁም ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል በማለት ጌታችን ለፈሪሳውያንና ጻፎች የንስሐን  ታላቅነት ለማስተማር በምሳሌ ነግሯቸዋል፡፡ ሉቃ.  15፤4-7፡፡
የቅድስት አትናሲያ  ታሪክ የንስሐን ታላቅነት ልንማርበት የሚያስችለን ታሪክ ነው ፡፡ ቅድስት አትናሲያ ሚኑፎ /በአረፈችበት ቦታ ስም/ በመባል ትታወቃለች፡፡

Wednesday, November 23, 2011

ጾመ ነቢያት

እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ
ዘመኑ ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡
ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡
ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር «የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡

Monday, November 21, 2011

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል


             የሰው ልጅ በገነት እንደ ቅዱሳን መላእክት በቅድስና አምላኩን በማመስገን በደስታ ይኖር ነበር ፡፡ ነገር ግን “ክፉና ደጉን ከምታሳውቀው ዕፀ በለስ እንዳትበላ” ተብሎ የተሰጠውን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት ከአምላኩ ተለየ(ዘፍ.3፡6) ፡፡እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ክብሩን አጣ፣ ጸጋው ተገፈፈ ፣ ፈጣሪውንም አሳዘነ ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረው ሰው ከክብሩ ተዋርዶ ሲመለከቱ ተከዙ ፡፡            

Friday, November 18, 2011

ሰማዕቱ ቅዱስ ሚናስ



ከቅዱሳን
ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ሚና 4ኛው መቶ  ክፍለ ዘመን ተጋድሎውን የፈፀመ ግብፃዊ ሰማዕት ሲሆን ህዳር 15 ቀን የሚነበበው ስንክሳር ቅዱስ ሚናስ በሚል ስያሜ ይገልፀዋል። በሶሪያ ቋንቋ ማር የሚለው ቃል  ‘ቅዱስየሚልትርጉም ሲኖረው ለወንድ የሚሰጥ ቅጥያ ሲሆን ለሴት ደግሞ ማርታ ይሆናል ይሄውም ቅድስት ማለት ነው።
ቅዱስ ሚናስ ከእናቱ ከአውፌምያ እና ከአባቱ ከአውዶስዮስ ልዩ ስሙ ኒቆስ ሻቲ በተባለ መንደር 276 ተወለደ። እናቱ አውፌምያ ልጅ መውለድ ባለመቻሏ ታዝንና ትጨነቅ ነበር። ወደ ቤተ-ክርስቲያን ስትሄድም እናቶች ልጆቻቸውን ሲያቆርቡ ስታይ በማልቀስ ፈጣሪዋን ልጅ እንዲሰጣት ትለምን ነበር። እግዚአብሔርም የልመናዋን ቃል ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጣት።

Tuesday, November 8, 2011

የአባ ዮሐንስ ኀፂር ሕይወት -ክፍል 2



ዮሐንስ ኀፂር ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ኮሎቦስ የሚል ነው፡፡ በሀገራቸው ቋንቋ አጭር፣ ድንክ ማለት ነው፡፡ በገዳመ አስቄጥስ በተጋድሎ ጸንተው ክብር ካገኙ ቅዱሳን መካከል አንዱና በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታላቅ ክብር ያለው አባት ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችንም ከምትዘክራቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ነው፡፡ /ነሐሴ 29/ ፍልስተ አጽሙን ቤተክርስቲያን ታከብራለች፡፡ 

አባ ዮሐንስ ኀፂር በላይኛው ግብኝ “ቴባን” በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም. ገደማ ተወለደ፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰቦቹ የተትረፈረፈ ምድራዊ ሀብት ባይኖራቸውም ትዳራቸው በፍቅርና በፈሪሃ እግዚአብሔር ያጌጠ ነበር፡፡ ገና ለጋ ሕፃን  ሳለ የዘወትር ምኞቱ መንኩሶ መኖር ነበር፡፡ ውሎ ሲያድር በልቡና ያሰበውን እውን ያደርግ ዘንድ መንፈሰ እግዚአብሔር አነሣሣው፡፡ መላ ዘመኑን በሥርዓተ አበው በተጋድሎ ሊፈጽም ራቅ ወዳለ በረሃማ ገዳም ሄደ፡፡ ይህችውም ገዳመ አስቄጥስ ናት፡፡

Thursday, November 3, 2011

ዮሐንስ ሐፂር


ዮሐንስ ሐፂር

ዮሐንስ ሐፂር በላይኛው ግብጽ ቴባን በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወደ ገዳም አስቄጥስ የገባው በልጅነቱ ሲሆን ያን ጊዜ አበምኔቱ አባ ባሞይ ይባል ነበር፡፡ አባ ዮሐንስ በተመሥጦው እና በታዛዥነቱ የታወቀ አባት ነበር፡፡ በመጀመርያው የአስቄጥስ ጥፋት ጊዜ ገዳሙን ትቶ ወደ ቁልዝም ተጓዘ፡፡ ያረፈውም በዚያ ነው፡፡
የዮሐንስ ሐጺርን ትምህርቶች ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡