Wednesday, January 7, 2015

የመገለጥ ሃይማኖት በአስተርእዮ

በዲያቆ ብርሃኑ አድማስ
የጥምቀት በዓል በጎንደር
ሃይማኖት የምንቀበለውና የምንጠብቀው እንጂ የምንሠራውና የምናሻሽለው አይደለም ከታኅሣሥ 29 ቀን ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት /ጊዜ/ ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ወራት/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በታኅሣሥ 29 ቀን የጌታችን ልደት ስለሆነ በዚህ አምላክ በሥጋ የተገለጠበት በዓል ይከበራል፡፡ ጥር 11 ቀን ደግሞ በጌታችን ጥምቀት የሥላሴ አንድነት ሦስትነት በይፋ የተገለጠበት ነው፡፡ ጥር 12 ቀን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ማስተማር በጀመረበት ጊዜ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ አምላክነቱን በይፋ የገለጠበት በዓል ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ዓበይት መገለጦች ወቅቱን በአጠቃላይ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተገለጠበትን መታሰቢያ አደረጉት፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን ትክክለኛ ሃይማኖት ከሚያሰኙት መሠረታዊ ነጥቦች ዋነኛውና ቀዳሚው የመገለጥ ሃይማኖት /Revealed Religion/ መሆኑ ነው፡፡
የአምላክን ማንነት በእምነት ለሚመረምር ሰው አምላክ ያልተፈጠረና ሁሉን የፈጠረ፣ የማይወሰን፣ በጊዜም የማይለካ ማለት ከጊዜና ቦታ ውጭ /Out of space time/ መሆኑ ሊጠረጠር አይችልም፡፡ስለዚህ አምላክ ከቦታና ጊዜ ውጭ ከሆነና በሁሉም ቦታ ደግሞ የመላ ወይም ምሉዕ ከሆነ /Omni present/ በቦታ ጊዜ ውስጥ ያሉ ፍጥረታት አምላክን ሊያዩት አይቻላቸውም ማለት ነው፡፡ ይህን ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት እናብራራው፡፡ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም «ዘመናትን» በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን» /ዕብ 11/ በሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ውስጥ «ዘመን» ወይም ጊዜ ፍጥረት መሆኑን በግልጽ እንረዳለን፡፡
መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም «ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶዎችንም አቆመች» /ምሳ 91/ በማለት በምሳሌው ተጨማሪ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ሊቃውንት በትርጓሜ እንዳብራሩት «ጥበብ» የተባለ ጌታ «ቤት» የተባለ ዓለምን ፈጥሮአል፡፡ ዓለሙ የጸናባቸው «ሰባት ምሰሶዎች» ደግሞ ዓለምን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚያጸኑት አዕዋዳት ሰባቱ ዕለታት ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ዓለምን የአጸናው ጊዜ ነው ማለት ነው፡፡ሙሴ «በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ» ዘፍ 11 ባለበት የሥነ ፍጥረት መጽሐፍም ጨለማ የነበረ መሆኑን ከተረከልን በኋላ « ብርሃን ይሁን አለ» ይልና ጠዋትም ሆነ ማታም ሆነ አንድ ቀን በማለት ዓለምና ጊዜ አንድ ላይ መፈጠራቸውን ይነግረናል፡፡ ከዚያም አስከትሎ የቀሪዎቹን የአምስት ቀን ፍጥረታትና የመጨረሻዋን /የሰባተኛውን/ ዕለት ዕረፍትነት ነግሮን ያጠቃልላል፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለም ይቀጥላል፤ የዕለታቱ ዑደትም ይቀጥላል፡፡ በሰባት ዕለት አጸናው ማለት ይህ ነው፡፡ ሁሉንም እርሱ እንደፈጠረ ደግሞ « ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለ እርሱ የሆነ የለም፤» ዮሐ 13
 «የሚታዩትና የማይታዩት ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በእርሱ ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል» /ቆላ.115-17/ ተብሎ ስለተጻፈ አምላክ በቅዱሳት መጻሕፍትም ከቦታ ጊዜ ውጭ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ፈጣሪ ከቦታ ጊዜ ውጭ ከሆነ ሊያየው የሚቻለው ፍጥረት የለም ማለት ነው፡፡ ወንጌላዊ ዮሐንስ «መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም» /ዮሐ 118/ እንዳለ፡፡ በመቃብያንም «አንተን ሁሉን ታያለህ እንጂ አንተን ማየት የሚችል የለም» ተብሎ ተጽፎአል፡፡ 3 መቃ.926 ቅዱስ ጳውሎስም «ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም፤ ሊያየውም አይቻለውም» /1 ጢሞ.616/ ሲል እንዳጸናው ለፍጥረት እግዚአብሔርን ማየት አይቻልም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ እርሱን በምርምር ማወቅም አይቻልም፡፡ አካሉ ረቂቅና ምሉዕ፣ በቦታ ጊዜ የማይወሰን ከሆነ ማን በምን ሊመረምረው ይችላል፡፡ በግብሩ በባሕርዩ እንመርምረው እንዳንል በእኛ ኅሊናችን ኅሊናን የፈጠረውን መመርመር ሸክላ ሠሪውን ለማወቅ ከመጣር የበለጠ የማይቻል ነው፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት «ወረሰየ ጽልመተ ምስዋሮ፤ ጨለማን መሰወሪያው አደረገ» እንዳለው ሊመረመር አይችልም፡፡ በጨለማ ማየት እንደማይቻል ሁሉ የእግዚአብሔር ባሕርይ ሊመረመር የማይቻል ነውና፡፡ ታዲያ ፈጣሪን እንዴት ማወቅ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ በዚህ ጊዜ ሊነሳ የሚገባ ነው፡፡ መልሱም ቀላል ነው፡፡ የምናውቀው እርሱ ራሱ ሲገለጥልንና ሲገልጥልን ብቻ ነው፡፡ ከተገለጠበትና ከገለጠውም መጠን በላይ ማወቅ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የእውነተኛ ሃይማኖትነት መሠረታዊ ማረጋገጫዎች መካከል አንዱና ዋናው መገለጥ ነው ያልነው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ራሱን ባይገልጥ ማን በምን መንገድ ሊያውቀው ይችላል፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን በሦስቱም ሕግጋት /በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ በሕገ ወንጌል/ ብንመረምረው መንገዱ ሁሉ መገለጥ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እግዚአብሔር ራሱን ለመላእክት በመፍጠር ገለጠላቸው፡፡ ለአዳም ተገለጠለት፣ አነጋገረው፣ ትእዛዝም ሰጠው፡፡ ከበደለውም በኋላ ፈለገው፤ አነጋገረው፤... የሚሉት በሙሉ መገለጥን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እግዚአብሔር አዳምን «አዳም አዳም ወዴት ነህአለው የሚለው ያለበትን ያለማወቅ ሳይሆን አዳም ከበደለም በኋላ ለኃጢአተኛ ባሕርዩ በሚስማማ ሁኔታ መገለጡን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ በሕገ ልቡና ለአባቶች ሁሉ በየዘመናቸው እንደ ሃይማኖታቸው ጽናት እንደ አእምሮአቸው ስፋት ሲገለጥላቸው ኖርአል፡፡ «በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት» ተብሎ ስለ አብርሃም የተጻፈው ነው፤ /ዘፍ. 181/ የሚለው የዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በየዘመኑ ለነበሩ ሰዎች የተገለጠበት መንገድ የተለያየ ከጥንት ወደ አሁን ጊዜ ስንመለከተውም የበለጠ እየተገለጠ እንደመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ የሕገ ኦሪት መሥራች ለምንለው ለሙሴ ሲገለጥለት ለአብርሃም ከገለጠለት በላይ ለእርሱ እንደገለጸለት ነግሮታል፡፡ «እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፣ አለውም እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአብርሃምም፣ ለይስሐቅም፣ ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፣ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር» /ዘጸ. 62-3/ ተብሎ የተጻፈው ሌላው ቀርቶ « እግዚአብሔር» የሚለው ስም እንኳ ከዚያ በፊት ላሉት እንዳልታወቀ ያረጋግጥልናል፡፡ ስለዚህ «እግዚአብሔር» የሚለውና ሌሎች ብዙ ነገሮች ከሕገ ኦሪት በኋላ እንደተገለጡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰፊ ምስክርነት ይሰጠናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ምሳሌያዊ /Allegorical/ በሆነ መንገድ የተገለጡትን ስንመለከት እጅግ እንደነቃለን፡፡
እግዚአብሔር ለነቢያቱም በተለያየ መንገድ ተገልጦላቸዋል፡፡ ለሙሴ በሐመልማል ወነበልባል /ዘጸ.31/ ለኢሳይያስ በአምሳለ አረጋዊ ነዋሕ፤ /ኢሳ. 61/ ለዳንኤል በአምሳለ ዕብን ቅውም ከረጂም ተራራ ላይ በተፈነቀለ ትልቅ ድንጋይ / ዳን 9 /... ለሌሎቹም በብዙ ኅብርና አምሳል ተገልጦላቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ « በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና» ያለው ይህንኑ ነው፡፡ /ዕብ.11/ በብሉይ ኪዳን የተጻፉ መጻሕፍትን በሙሉ ስንመለከታቸው «እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤...» በሚል መግቢያ የሚጀምሩ ናቸው፡፡ ይህም ቃልና ትምህርቱ በሙሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እንጂ የእነርሱ ላለመሆኑ በሌላ አነጋገር የመገለጥ ሃይማኖት፤ ትምህርት መሆኑን እየደጋገመ ያረጋግጥልናል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ፤ በብሉይ ኪዳን ብዙ ነቢያት ተነሥተው ቢያስተምሩም ብዙ መጻሕፍት ቢጽፉም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ግን እጅግ ምስጢራዊና ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እንጂ በግልጽ አልታወቀም ነበር፡፡ ምክንያቱም በሚገባው መንገድ ራሱን ገና አልገለጠም ነበርና፡፡
 ለአብርሃም የተገለጡት ሦስት ሰዎች፤ « እንውረድ፣» የሚሉት ዓይነት ቃላትና ይህንኑ ከሚመስሉት ጥቅሶች በቀር በጊዜው /ብሉይ ዘመን/ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ስለ እግዚአብሔር የአንድነትና የሦስት ምስጢር በበቂው አልተገለጠላቸውም፡፡ በመጽሐፈ ኢያሱ የተጻፈውንና ስለ እሥራኤል የዮርዳኖስ ወንዝ ተሻግሮ ከምድረ ርስትን መርገጥን በተመለከተ «ሙሴም እንዳዘዛቸው የሮቤል ልጆች፣ የጋድም ልጆች፣ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ተሰልፈው በእሥራኤል ልጆች ፊት ተሻገሩ፡፡» የሚል ተጽፎአል /ኢያ.417/፡፡ አንድ የጥንት የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ይህን ሲተረጉመው እነዚህ ቀድመው የተሻገሩት ከአሥራ ሁለቱ ነገድ ሁለቱ ነገድ በሙሉና ሦስተኛው ከፊሉ መሆኑ በብሉይ ኪዳን ዘመን ስለነበረው የሥላሴ ዕውቀት ምሳሌ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ስለ አብና ስለወልድ በመጠኑ ስለመንፈስ ቅዱስ ደግሞ እጅግ በብዥታ ያውቁ ነበር፡፡ ሦስተኛው ነገድ በከፊል የተሻገረው ለዚህ ነው፡፡ ሦስቱ ነገድ እንኳን አለመሟላቱም በዘመኑ ምስጢረ ሥላሴ በከፊል በምሳሌና በጥላ ብቻ ይታወቅ የነበረ ስለመሆኑ አሰረጂ ነው በማለት ይተረጉማል፡፡በርግጥም ቀደም ብለን እንዳየነውም የእግዚአብሔር መገለጥ እየጨመረ እየጨመረ እንደመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን ዘመን መገለጥ እየጨመረ እየጨመረ ከመጣ በኋላ ፍጹም መገለጥ ሲመጣ ያኛው የጥላውና የምሳሌው መገለጥ ይደመደማል፡፡ ፍጹሙ መገለጥም የአምላክ ሰው ሆኖ መገለጥ ነው፡፡ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ «መጀመሪያ ቃል ነበረ፣...» ካለ በኋላ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡ በዓለም ነበረ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ዓለሙም አላወቀውም» ዳግመኛም ከዚያው አስከትሎ «ቃልም ሥጋ ሆነ፣ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን» ሲል መገለጡን አበሠረ፤ /ዮሐ 11-18/፡፡ይህን መገለጥ ደግሞ እንኳን ሰዎች መላእክትም ተግተው ይሹት ነበረ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ «ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ» /1 ጴጥ. 11-12/ ሲል እንደገለጸው፤ መላእክቱ የአምላክን መገለጥ ለማየት እጅግ ጓጉተው ነበር፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ቢሆኑ አምላክን ለማየት ዕድል የሚያገኙት ሰው ሆኖ ሲገለጥ ብቻ ነውና፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ፤ «እግዚአብሔርንም የመምስል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፡፡ በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ» /1ኛጢሞ.316/ በማለት ለመላእክት የታየው በሥጋ በመገለጡ እንደሆነ አረጋግጦልናል፡፡ እነርሱም ምስጢረ ሥጋዌን ከሰው በላይ አጣጥመው ተጠቅመውበታል፡፡ በብሥራቱ ቅዱስ ገብርኤል ብቻ ቢሣተፍም በልደቱ ጊዜ ግን ብዙዎች መላአክት በአንድነት ለእረኞች ለማብሠር ታድለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በመዋዕለ ሥጋዌው ሁሉ እየተላላኩ አምላክን ማየት ጠገቡ፡፡ ሲሰቀልና ሲሞትም በአርምሞ በመደነቅ ተመለከቱ፡፡ ትንሣኤውን አበሠሩ፡፡ የቀሩትም በዕርገቱ ዕለት ሐዋርያትን አረጋግተው ዳግም ምጽአቱን አውጀው ተሰወሩ፡፡ ዳግመኛ ሲመጣ መለከት እየነፉ ከፊት ከፊት እየቀደሙ ከኋላም እየተከተሉ እንደሚመጡም ተጽፎላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የአምላክ መገለጥ የመላእክት ደስታ ሆነ፡፡ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ፤ እያሉ የዘመሩት ወድደው አይደለም፡፡ ተገልጦ ባዩት ጊዜ ለመደመማቸው ወሰን ቢያጡ ለሰው ያለውንም ፍቅር ይገልጡት ዘንድ ቢሳናቸው፤ ይህን ምስጋና እያጣጣሙ ክብርና ቅድስናቸውን ለራሳቸው አስጨመሩ፡፡ ይሁን እንጂ አምላክ ሰው በመሆኑ ከረቂቃኑ መላእክት ይልቅ የበለጠ የቀረቡት ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በዘመነ ብሉይ እንደ ነበረው እንደ ሄኖክ፣ እንደ መልከጼዴቅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ፣ ዳዊትና ሰሎሞን፣ ሙሴና ነቢያት ራሳቸውን የቀደሱና ያነጹ ብቻ ሳይሆኑ በኃጢአት የረከሱት እነ ዘኬዎስ፣ ማርያም እንተ ዕፍረት፣ መጻጉዕ፣ በዝሙት የተያዘችው ሴትና ሌሎቹም ሰውነቱን ዳሰሱት፤ አብረውት በሉ ጠጡ፤ . . .፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን መገለጡን በሰፊው አሰበችው፤ በተድላ በደስታ፤ በመብልና በመጠጥም ጭምር የምታከብረውም ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ መገለጥ በኋላ የተላኩ ሐዋርያትም የትምህርታቸው አቀራረብ ተለወጠ፡፡ እንደ ነቢያት በዚህ መንገድ አየነው፣ እንዲህ ሆኖ ተገለጠልን የሚለው ቀረና ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው፤ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም፣ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል እንመሰክርማለን፤ ከአብ ዘንድ የነበረንም ለእኛም የተገለጠውን፤ የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን» /1ኛዮሐ. 11-3/ እያሉ ለማስተማር ቻሉ፡፡
 ከዕርገቱም በኋላ ቢሆን እርሱ ከቅዱሳኑ ተሰውሮ አያውቅም፡፡ ይልቁንም ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ የለምና /ሰው ከሆነ በኋላ መታየቱ፣ መወሰኑ፣ መጨበጡ፣ መዳሰሱ አልቀረምና/ በየዘመኑ ይገለጣል፡፡ በየቅዱሳኑ ሕይወት እንደተጻፈው እነ አባ ብሾ// እግሩን አጠቡት፣ አዘሉት፡፡ በየዕለቱ ለሰማዕታቱ እየተገለጠ አጸናቸው፤ ጻድቃኑንም ምስጢሩን አብዝቶ ገለጠላቸው፡፡ በየገድላቱም ላይ ቅዱሳኑ ሲያርፉ «ይህን ያህል ቅዱሳኑን አስከትሎ መጣ፤ ነፍሱንም ተቀበለ፣. . .» የመሳሰሉት አገላለጾች ምንኛ ግሩም ናቸው፡፡አንድ ጊዜ ሰው ሆኖአልና እንደቀድሞው ለነቢያቱ እንዳደረገው ሳይሆን አሁን በሥጋ ተገልጦአልና በየጊዜው ይመጣል፣ ይታያል፣ ይጨበጣል፤ ይዳስሳቸዋል፤ ይስማቸዋል፤ ያወጋቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን በሮማ አደባባይ «ወዴት ትሔዳለህብሎ እንደመለሰው፤ በየዘመኑ እየተገለጸ ይመራቸዋል፤ ያነጋግራቸዋልም፡፡ መገለጥ፤ ግሩምና ድንቅ መገለጥ፤ ሃይማኖቱም የመገለጥ፡፡ እርሱ ራሱ «ይህ ዛሬ እናንተ የምታዩትን ብዙ ነቢያት ሊያዩ ወደው አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትን ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም፤ የእናንተ ግን ያዩ ዓይኖቻችሁ፤ የሰሙ ጆሮቻችሁ የተመሰገኑ ናቸው» እንዳለ የሐዲስ ኪዳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ባሕታውያን ስውራን ሁሉ ምን ያህል የተመሰገኑ ናቸው፡፡ በየዕለቱ ጌታቸውን ያዩታልና፤ ለዚህም ተጠርተዋልና፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጋት ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛነቷ ማረጋገጫዎች አሁንም ዋነኛዋ መገለጡ ነው፡፡ የሌሎቹ በተለይም ከኢንዱስትሪው አብዮት በኋላ የተነሡ የክርስትና ክፍልፋዮች /Denominations/ ሁሉ መሠረተ እምነታቸው የሚዋቀረው በዩኒቨርስቲዎችና በየተቋማቱ ባሉ ምሁራኖቻቸው አስተምህሮ በጠረጴዛ ዙሪያ ነው፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚመሠረተው ግን በገዳማውያን ቅዱሳን መገለጥ ላይ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ሊቃውንቱ ሁሉ በመማር ብቻ ሳይሆን በገዳም ተወስነው፣ ሱባኤ ገብተው፣ በእርሱ መገለጥ የተሰወረ ምስጢር ይገለጥላቸዋል፤ የረቀቀው ይጎላላቸዋል፡፡ ያንን ብቻ ያስተምራሉ፤ እርሱንም ብቻ ይዘን እናስተምራለን፤ በተገለጠውም መሠረት እንኖራለን፡፡ በእኛ ሀገር እንኳን እነ ቅዱስ ያሬድ፤ አባ ጊዮርጊስ፣ አባ ዜና ማርቆስ፤ አባ ተክለሃይማኖት፣. . . ሁሉም በሱባኤ፣ በገዳም፣ በምናኔ፣ በተጋድሎ ተወስነው፤ በተገለጠውና በሚገልጥላቸው መንገድ ብቻ ተጓዙ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚያረጋግጡልን ይህንኑ ብቻ ነው፡፡
ሃይማኖትን እንቀበለዋለን ከዚያም እንጠብቀዋለን እንጂ ልንሠራው አንችልም፡፡ የያዕቆብ ወንድም ቅዱስ ይሁዳ «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችኋለሁ» /ይሁ.13/ ሲል እንደገለጸልን፤ ሃይማኖት ለቅዱሳን በመገለጥ የተሰጠች እንጂ የተሠራች አይደለችም፡፡ ጌታችንም በወንጌል «ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡ የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል፡፡ የሰጠኸኝን ሁሉ ከአንተ እንደሆነ ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝ ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት. . .» /ዮሐ.1722/ ሲል እንዳስተማረው፤ ክርስትና የተቀበልነውና የምንጠብቀው እንጂ የሠራነውና የምናሻሽለው አይደለም፡፡ በዚያ ጊዜ ያልገለጸልንንም «የምነግራችሁ ብዙ ነገር አለ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም፤ መንፈስ ቅዱስ በመጣ ጊዜ ግን እርሱ ሁሉንም ያሳውቃችኋል» የሚል ተስፋን ሰጠን፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከእኛ ጋር የሚኖረውም እስከ ዕለተ ምጽአት መሆኑን አረጋገጠልን፡፡ ስለዚህም እስከ ዛሬ ድረስ መንፈሳቸውን ላላረከሱት በየጊዜው ይገለጣል፡፡ ለሐዋርያት ገለጠላቸው፤ ለሊቃውንት ገለጠላቸው፤ ለጻድቃን በየገዳሙ ገለጠላቸው፤ ለየመምህራኑም በየሱባኤያቸው በተቀደሱ ጉባኤዎቻቸው ገለጠላቸው፤ እኛም የተገለጠውን ይዘን እርሱንም እየጠበቅን እንጓዛለን፡፡ ከተገለጠው ውጭ መጓዝም የተወገዘ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ፤ «ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን» /ገላ.18/ በማለት አረጋገጡልን፡፡
ስለዚህም በዘመነ አስተርእዮ ይህን የአምላክን መገለጥ እና የመገለጥን ሃይማኖት የምንዘክርበት ምክንያት፤ ሃይማኖት ሰዎች ያልፈጠሩት ነገር ግን በአምላክ መገለጥና እርሱ በገለጠው ሃይማኖታዊ ዕውቀት ብቻ መጓዝን ማዘከር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በተገለጠልን ጸንተን ለቅዱሳን የተሰጠችውን ሃይማኖት ተጉዘንባት ለልጆቻችንም አውርሰናትና ጠብቀናት እንድናልፍ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ 
በዓሉን በዓለ ሰላም ፤ በዓለ ክብር ፤ በዓለ ፍስሐ ያድርግልን - አሜን፡፡

18 comments:


 1. ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጋት ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛነቷ ማረጋገጫዎች አሁንም ዋነኛዋ መገለጡ ነው፡፡ የሌሎቹ በተለይም ከኢንዱስትሪው አብዮት በኋላ የተነሡ የክርስትና ክፍልፋዮች /Denominations/ ሁሉ መሠረተ እምነታቸው የሚዋቀረው በዩኒቨርስቲዎችና በየተቋማቱ ባሉ ምሁራኖቻቸው አስተምህሮ በጠረጴዛ ዙሪያ ነው፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን "አስተምህሮ የሚመሠረተው ግን በገዳማውያን ቅዱሳን መገለጥ ላይ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ሊቃውንቱ ሁሉ በመማር ብቻ ሳይሆን በገዳም ተወስነው፣ ሱባኤ  ገብተው፣ በእርሱ መገለጥ የተሰወረ ምስጢር ይገለጥላቸዋል፤ የረቀቀው ይጎላላቸዋል፡፡ ያንን ብቻ ያስተምራሉ፤ እርሱንም ብቻ ይዘን እናስተምራለን፤ በተገለጠውም መሠረት እንኖራለን፡፡ በእኛ ሀገር እንኳን እነ ቅዱስ ያሬድ፤ አባ ጊዮርጊስ፣ አባ ዜና ማርቆስ፤ አባ ተክለሃይማኖት፣. . . ሁሉም በሱባኤ፣ በገዳም፣ በምናኔ፣ በተጋድሎ ተወስነው፤ በተገለጠውና በሚገልጥላቸው መንገድ ብቻ ተጓዙ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚያረጋግጡልን ይህንኑ ብቻ ነው፡፡"

  ወንድማችን ዲያቆን ብርሃኑ መግበ ነፍስ የሆነ ትምህርት ነው፡፡
  ሳነበህ ነፍሴ በሃሴት አየቶሞለች ነበር፡፡
  ቃለ ሕይወት ያሰማልን.የአገልግሎት አደሜህ ያርዝምልን ፡፡
  አግዝአብሔር የተምሰገነ ይሁን፡፡
  ተስፋዬ ከ ሸገር

  ReplyDelete
 2. Wawe! Endaet dese yelale kale hiwet yasmalen wendeme ageleglothen ybarke egziabeher.

  ReplyDelete
 3. Betam des yemil temhert new.hulem bezu neger eyetemaren new .Egziabher yistelen !

  ReplyDelete
 4. Betam des yemil temhert new.hulem bezu neger eyetemaren new .Egziabher yistelen !

  ReplyDelete
 5. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
  M/A
  Berlin

  ReplyDelete
 6. kalle heywate yassemallen.yagelegelot zamenehen yebarekelleh.

  ReplyDelete
 7. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

  ReplyDelete
 8. ቃለ ሕይወት ያሰማልን,ቃለ ሕይወት ያሰማልን,የአገልግሎት እድሜህን ያርዝምልን, እንዲህ የተገለጠውን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይዘን,ጠብቀን እንድናልፍ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!

  ReplyDelete
 9. ያገልግሎት ዘመንህን እግዚአብሄር ይባርክልህ

  ReplyDelete
 10. D. Berhanu, I know you are matured and able to write more.Your spiritual wisdom is given from the Holy spirit .Please,keep on disclosing the wealth of God s word from the Bible.The laity can learn
  a lot and consolidate their belief.The role you played,are playing and
  will play can make a big difference.MAY GOD BLESS YOU.

  ReplyDelete
 11. ቃለ ሕይወት ያሰማልን,ቃለ ሕይወት ያሰማልን,የአገልግሎት እድሜህን ያርዝምልን, እንዲህ የተገለጠውን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይዘን,ጠብቀን እንድናልፍ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!

  Your spiritual wisdom is given from the Holy spirit .Please,keep on disclosing the wealth of God s word from the Bible.The laity can learn a lot and consolidate their belief.The role you played,are playing and will play can make a big difference.MAY GOD BLESS YOU.

  ReplyDelete
 12. Egziabher lezich seat tebiko migbe nefs endinbela silabekan kibir misgana yigbaw. Wondimochachin kale hiwot yasemalin! Edmiachihun yarzimilin! Legnam mastewalun yadilen!

  ReplyDelete
 13. Kalehiwate yasemalen

  ReplyDelete
 14. Kale hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 15. ቃለ ሕይወት ያሰማልን የአገልግሎት እድሜህን ያርዝምልን::

  ReplyDelete
 16. ቃለ ሕይወት ያሰማልን የአገልግሎት እድሜህን ያርዝምልን::

  ReplyDelete
 17. "ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ።" እጅግ ጥልቅ ሚስጢር ያለው ትምህርት:ቃለ ሕይወት ያሰማልን::

  ReplyDelete