Tuesday, August 7, 2018

ፍልሰታ ኪዳነ ምህረት


«ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ»
ቅዱስ ያሬድ
click here For PDF
ፆመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ምእመናንን ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመሄድ አሊያም በአጥቢያቸው በመሰባሰብ እመቤታችን ለሐዋርያት በተለያዩ ጊዜያት ተገልጻ ሞትና ትንሣኤዋን የገለጸችበትን ሁኔታ ያስባሉ፡፡ ጌታም እናቱን መንበር አድርጎ ቀድሶ ማቁረቡን ይዘክራሉ በዚህ ወቅት በፆም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት ይማጸናሉ፡፡ ሁሉም እንደሚደረግላቸው ያምናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም «በእውነት ተነሥታለች» ብለው በደስታ የፆሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡
 ሞትና ትንሣኤዋ እንዴት ነው ቢሉ፡- የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡