Friday, January 24, 2014

ምሥጢረ ጥምቀት ክፍል-3

ሠ-በማን ስም ልንጠመቅ ይገባል
  ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም  ያጠመቃችኋቸው፡፡››  (ማቴ. 28÷19) ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡
 ይህንን የወንጌል ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም ‹‹ምን እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38)፡፡
 2006 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር
ሐዋርያው ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ ማስተማሩ ለምን ነበር? ለምን ጌታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ያለውን ተከትሎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ አላለም? የሚል ጥያቄ ለሚያነሣ ሁሉ ምክንያቱ እንደሚከተለው ነው፡፡በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ ከጥንት ጀምሮ በነቢያት አንደበት ይወርዳል ይወለዳል እየተባለ የተነገረለትን መሲሕን ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ ሐዋርያውም ያ የተስፋው ቃል ዛሬ መፈጸሙንና በተስፋው ቃል መሠረት ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ 33 ዓመተ ከ3 ወር በምድር ላይ ተመላልሦ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሰውን ልጅ በደሙ የዋጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መሆኑን አምነው በሰው ካልተጠመቁ በስተቀር አብርሃም አባታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሚለው እምነት ብቻ አምነው ጌታን በሰቀሉት አይሁድ መንገድ የሚጓዙ ከሆነ እንደማይድኑ በመሲሕ አምነው በስሙም ከተጠመቁ ግን እንደ ሚድኑ ሊያስተምራቸው ስለፈለገ የጌታን ስም ለይቶ ጠራ፡፡ በዚህም የጌታን አዳኝነትና መሲሕነት አምነው እንዲቀበሉ በአጽንዖት መናገሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሐዋርያት ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ቤዛ የሆነልንን ጌታ ሰው ሁሉ አምኖ እንዲድን በየሄዱበት የጌታን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት አሰተምረዋል፡፡ የስብከታቸው ማዕከል የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክህደቱ ጸንቶ የነበረው በጌታ የባሕርይ አምላክነት ላይ ነበርና፡፡ በዚህ የተነሣ የእርሱን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት ለማሳመን ጌታን የስብከታቸው ማዕከል አደረጉ፡፡

Monday, January 20, 2014

ምሥጢረ ጥምቀት- ክፍል-2

ሐ-የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን
1-             ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት የዳኑባት መርከብ የአማናዊቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆንዋ በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠ ነው፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡናቸው ያደረው ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲድኑ እግዚአብሔርን ድምፅ ያልሰሙት የኖኀ ዘመን ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌነት እንዳለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ (ሲያስተምር) #ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኀ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡
ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቡናቸው ያደረው ኖኀና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲድኑ እግዚአብሔርን ድምፅ ያልሰሙት የኖኀ ዘመን ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌነት እንዳለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ (ሲያስተምር) ‹‹ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኀ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ›› 1ጴጥ.3÷20-12፡፡

Wednesday, January 15, 2014

ምሥጢረ ጥምቀት

ክፍል-1
ሀ-አስፈላጊነት

መጠመቅ ማለት መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነት የሚሰጥበት እና የኃጢአት ሥርየት የሚገኝበት ምሥጢር ነው፡፡
1.      ድኀነትበጥምቀትነው፤
ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ያልተጠመቀ ሰው አይድንም፡፡ የተጠመቀ ግን እንደሚድን በመዋዕለ ትምህርቱ እዲህ ሲል አስተምራል #ያመነ የተጠመቀም ይድናል$ ማር.16 ቁ 16፡፡ ያመነ ይድናል ብቻ አለማለቱን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ጥምቀት ለድኀነት ባያስፈልግ ኖሮ ጌታ ያመነ የተጠመቀም ይድናል ባላለ ነበር፡፡
2. በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንወለዳለን፤
ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ በሌሊት ወደ ጌታ ዘንድ ሊማር በሄደ ጊዜ ጌታ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› አለው፡፡ ይህ የጌታ ትምህርት ለኒቆዲሞስ ስለረቀቀበትና ስለተቸገረ ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኀፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡