Wednesday, August 29, 2012

የፓትርያርክ ምርጫ ታሪክና አፈጻጸም በኮፕት ቤተ ክርስቲያን”

ወልደ ማርያም
 የዚህ አጭር ጽሑፍ ዋና ዓላማ በትምህርተ ሃይማኖትና ከሞላ ጎደል በሥርዓተ እምነት ከሚመስሉን አኀት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በ2000 ዘመን ታሪኳ የሚመሯትን ፓትርያርኮች እየመረጠች የሄደችበትን ቀኖና ታሪክና ሥልት ጠቅለል ባለ መልኩ ማቅረብ ነው፡፡ ከሌሎቹ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የኮፕት ቤተ ክርስቲያንን የምርጫ ቀኖናና ሂደት ዳስሰን ለማቅረብ የፈለግንበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያኗ መንበረ ፕትርክና ለ1600 ዘመናት የቤተ ክርስያናችንም መንበረ ፕትርክና ሆኖ የቆየ ከመሆኑ አንጻር በጽሑፉ የሚወሳው ታሪክ የሚቀርበን በመሆኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ መንበረ ፕትርክናዋ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ወንጌላዊው ማርቆስ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በድምሩ 117 ፓትርያርኮችን እየመረጠች አስቀምጣለች፡፡ 
ፓትርያርኮቹም የተቀበሉትን ሰማያዊ ሓላፊነት በመያዝ ቤተ ክርስቲያኗ ክፉውንና ደጉን ዘመን አልፋ ዛሬ ካለችበት ደረጃ እንድትደርስ አድርገዋታል፡፡ አሁን ባለችበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኗ በግብጽና በመላው ዓለም ከ15 እስከ 18 ሚልዮን የሚደርሱ ምእመናን ያሏት ሲሆን እነዚህንም ምእመናን በእረኝነት የሚጠብቁ ከ150 በላይ ሊቃነ ጳጳሳት አሏት፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ፕትርክናው ማእከላዊ አስተዳደር በሚመሩ 54 ያኽል አኅጉረ ስብከት በሊቃነ ጳጳስነት ተመድበው ያገለግላሉ፡፡ ከእነዚህ አኅጉረ ስብከት 15 የሚሆኑት ከግብጽ ውጪ በተለያዩ ክፍላተ ዓለም ተቋቁመው በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

Tuesday, August 28, 2012

ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ



“ዘይሁብ መርሐ ርቱዐ ለቤተ ክርስቲያን - 
ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ”
በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

ቤተ ክርስቲያን የምንላት ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹምና ከማይነገር ፍቅሩ የተነሣ ሰው እስከ መሆን፣ ሰው ሆኖም በዚህ ዓለም ከኃጢአት በስተቀር እንደ ሰው መኖርን፣ ከዚያም በቀራንዮ ቅዱስ ሥጋውን እስኪቆርስላትና ክቡር ደሙን እስኪያፈስላት ድረስ የደረሰላትና የመሠረታት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ "ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት" የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል መሠረትነት በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት በምእመናን አካልነት የተመሠረተች ጉባኤ ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስንል የዚህ ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን (ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣ ...) እና ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ በሰማይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ) የዚህ ዓለም ጣጣቸውን ጨርሰው የሄዱ፣ ድል አድርገው የድል አክሊላቸውን ለመቀበል እርሱ የወሰነውን ጊዜ የሚጠባበቁ ቅዱሳን ኅብረት ስለሆነች አትናወጽም፤ ስለሆነም ሊቃውንት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን (Church Triumphant) ይሏታል፡፡ ገና በዚህ ዓለም በጉዞና በፈተና ላይ ያለችውን የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችውን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ደግሞ ገና በተጋድሎ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን (Church Militant) ይሏታል፡፡

Monday, August 20, 2012

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ


Click For PDFልደትና ትምህርት 
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 25 ቀን 1928 .. በዘመነ ዮሐንስ በዓድዋ ከተማ በመደራ አባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከካህን ቤተሰብ፣ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወ/ አራደች ተድላ ሲወለዱ ገብረ መድኅን የተባሉት አቡነ ጳውሎስ፣ በጥንታዊው አባ ገሪማ ገዳምና በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

በወቅቱ ሁለተኛው ፓትርያርክ በነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካይነት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተልከው ከሩሲያው የቅዱስ ቭላድሚር ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ በኦርየንታልና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የነገረ መለኮት ይትበሐል (ትምህርት) 1954 . ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም በየል ዩኒቨርሲቲ በኦሪየንታል፣ በምሥራቅና በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው የነገረ መለኮት ትምህርት አመለካከትና ልዩነት ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ ዲግሪን 1958 . ሲያገኙ፣ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማስተርስ ኦፍ ቴኦሎጂ ዲግሪን 1964 .. ተቀብለዋል፡፡

Friday, August 10, 2012

ፅንሰታ ለማርያም

እንኳን ለፅንሰታ ለማርያም በዓል ነሐሴ 7 በሰላም አደረሳችሁ
ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ 
አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ

ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ፤ 
በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም
ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር: እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ:፡ እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸውባለጸጎች ነበሩ::ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅአልነበራቸውምና መካን ነበሩ: