Saturday, November 22, 2014

ጾመ ነቢያት



“መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።” ፩ቆሮ.፰፡፰ 

ዳግመኛም ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፡ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሰለጥንብኝም መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው” ብሏል።
‘አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፡፡’’ ኢዩ.፪፡፲፪ 

‘በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ፡፡ ጉባኤውንም አውጁ፡፡’’ ኢዩ.፪፡፲፭ 

ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ማለት ነው፡፡ ወይም ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጉመዠውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና አለው፡፡ ከጥንት ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ ዘጸ.፴፬፡፳፰ 

Sunday, September 21, 2014

ቅድስት ዕሌኒ




 የቅድስት ዕሌኒ ባለቤቷ ተርቢኖስ ይባላል፤ በቅድስና ተፋቅረው ነበር የሚኖሩት፤ ተርቢኖስ የሚል ጽሁፍ ያለበት የአንገት ሀብል አሰርቶላት ነበር። ተርቢኖስ ነጋዴ ስለነበር ከጓደኞቹ ጋር በመርከብ ተሳፍረው እሩቅ አገር ሄደው  3 ዓመት በኃላ ይመለሳሉ ፤ ታዲያ መርከብ ላይ እንዲህ እያሉ ይጫወታሉ ፤ እኛስ በሰላም ወደ አገራችን ተመለስን ሚስቶቻችን ግን በሰላም ይጠብቁን ይሆን ሌላ ወንድ ወደውና ለምደው እንዳይጠብቁን አሉ፤ ተርቢኖስ ደግሞ የኔ ሚስት ዕሌኒ ከኔ ሌላ ማንንም አትወድም አትለምድም ይላቸዋል፤ ያንተ ሚስት ከሄዋን ሴቶች ትለያለችን እኔ ሄጄ ወድጃት ወዳኝ ለምጃት ለምዳኝ ብመጣ ምን ትሰጠኛለህ ይለዋል ንብረቴ ሁሉ ላንተ ይሁን ይለዋል በወረታቸው ተወራርደው ይሄዳል::
 የዕሌኒን ገረድ አስጠርቶ 20 ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ ሁለቱ ብቻ የሚተዋወቁበትን አንድ ነገር ስጪኝ ይላታል፤ እርሷም እሺ አንተ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እያልክ ለፍፍ ትለዋለች፤ እንዳለቸው እየዞረ ለፈፈ፤ ገረዷም ወደ ዕሌኒ ቀርባ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እየተባለ ነው ገላሽን ታጠቢ ሽቶም ተቀቢ ትላታለች፤ዕሌኒም የአንገት ሀብሏን አስቀምጣ ገላዋን ልትታጠብ ትገባለች ይህን ጊዜ ወስዳ ትሰጠዋለች፤ እርሱም ተርቢኖስ ጋር ሄዶ እየው እፍቅራኝ ውድ ስጦታ ሰጠቺኝ ብሎ ያሳየዋል፤ ሀብሉን ተመለከተው ተርቢኖስ የሚል ፅሁፍ አለበት አመነው፤ አያዘነ 3 ዓመት የደከመበትን ንብረት አስረክቦ እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ገባ::
ምን ሆነሃል አለችው ንብረቴን መአበል ወሰደቢኝ አላት፤አትዘን አንተም እኔም ብዙ ወዳጆች አሉን ተበድረን ትነግዳለህ ትለዋለች፤ እርሱም በአሽሙር ልክ ነሽ ያንቺ ወዳጆች ብዙ ናቸው እኔ ግን ወዳጅ የለኝም ደግሞም ባበደርኩበት አገር ተበድሬ በከበርኩበት አገር ተዋርጄ አልኖርም ወደ ሌላ አገር እሄዳለሁ ይላታል፤ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው ካንተ አልለይም ትለዋለች፤ በመርከብ ተሳፍረው ይሄዳሉ በህሩ መሀል ሲደርሱ ሀብሉን አውጥቶ ያሳያታል ስወድሽ ጠላሺኝ ሳምንሽ ካድሺኝ ይላታል፤ ልታስረዳው ሞከረች አላመናትም በሰጥን ውስጥ አድርጎ ስራሽ ያውጣሽ ብሎ ከባህር ጣላት::
 ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃት ሳጥኑ ተንሳፎ ሄዶ ባህር ዳርቻ ያርፋል አገሩ ሮም ነው ቆንስጣ የተባለ አገር ገዢ ሳጥኑን ሲከፍተው እጅግ የምታምር ሴት አገኘ፤የእየሱስ እናት ማርያም የምትባይው አንቺ ነሽን ይላታል፤እኔ የእርሷ ገረድ ነኝ እንጂ እርሷን አይደለውም፤ ጊዜ ያዋረደኝ ወቅት የጣለኝ ሴት ነኝ ትለዋለች፤ወደ ቤተመንግስቱ ይዟት ገባ፤ በክብር እስከ 6 ወር ጠበቃት ከዚያም አገባት በግብርም አወቃት፤መስከረም 12 ቆስጠንጢኖስ ተወለደ፤ በድብቅ የሃይማኖት ትምህርት አስተማረችው ምክንያቱም ባለቤቷ ጣኦት አምላኪ ነበርና፤ ልጇ  25 ዓመቱ በሮም ነገሰ ክርስትናንም ተቀበለ::
 ዕሌኒም የጌታን መስቀል ለማስወጣት እየሩሳሌም ሄደች ከብዙ ልፋት በኃላም መስከረም 16 ደመራ ደምራ መስቀሉን አገኘች፤መስከረም 17 ቁፋሮ ጀመረች  6 ወር ቁፋሮ በኃላ መጋቢት 10 መስቀሉ ወጣ፡፡ ብዙ ተአምራትም ተደርገዋል፤ ለእግዝያብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም ከመስቀሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
እሌኒ ቅድስት  80 ዓመቷ ጌታችን ተገልጾ ወዳጄ ዕሌኒ ወደ እኔ ልወስድሽ ነው አላት፤ ደነገጠች፤ ምነው ፈራሽ መኖር ትፈልጊያለሽ እንዴ ይላታል፤ እንዳመሰግንህ ትንሽ ብቆይ ትለዋለች፤ ስንት ዓመት ልጨምርልሽ ይላታል፤ ይህማ ባንተ ቸርነት መገባት ይሆን የለም ወይ ትለዋለች፤ 40 ዓመት ጨምሬልሻለሁ ይላታል  120 ዓመቷ ግንቦት 9 ቀን አረፈች ፡፡
የቅድስት ዕሌኒ በረከቷ ይደርብን - አሜን