Friday, September 23, 2011

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ - የግማደ መስቀሉ መገኛ


ግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፤ በደላንታ፤ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ በትግራይ እንደ ደብረ ዳሞ በበጌምድር እንደዙር አምባ በመንዝ እንደ አፍቅራ ናት ፡፡

ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሐ አቋርጦ በሸሎን በመሻገር ፫ ሰዓት መንገድ አቀበት በመውጣት አንድ ቀን ሙሉ ተጉዞ ማታ ፲፪ ሰዓት ይገባል ፡፡ግሸን ማርያም በፊት ደብረ እግዚአብሔር ትባል ነበር ፡፡ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር  አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ነው፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዣን ዘመን መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብር ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን  የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች ፡፡

ከዚያም በ ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር፡፡ ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡


Sunday, September 11, 2011

ቅዱስ ድሜጥሮስ እና የዘመን አቆጣጠር

ዮሐንስ ወንጌላዊ ዘንስር

እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ 2004 ዓ.ም. በሰላም አደረሳችሁ- ዕንቁጣጣሽ
አዲሱ ዓመት የንስሐ ፤የቅድስና ፤ የደስታ ፤ የፍስሀ ፤ የፍቅር ያድርግልን


ድሜጥሮስ መስታወት ነው፡-በመስታወት ከዓይን ጉድፍ ከጥርስ እድፍ አይተው እንደሚያጸዱበት ሁሉ ባሕረ ሐሳብንም የተማረ ሰው ዓለም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እስከ ምጽአት ድረስ የሚሆነውን ቁጥር ያውቃልና፡፡ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ አንድም ሐሳብ ባሕር ይለዋል ዘመን ያለው ቁጥር ሲል ነው፡፡