Friday, September 9, 2016

የዘመን አቆጣጠር ባሕረ ሐሳብ -ክፍል 1


1. ባሕረ ሐሳብ ማለት ምን ማለት ነው?

ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽም የሐሳብ ባሕር ማለት ነው፡፡ በዓላት እና አጽዋማትን ለማውጣት የመደመር፣ የመቀነስ፣ የማባዛት ስሌትን ብቻ ሳይሆን ሐሳበ ፀሐይን፣ ሐሳበ ወርኅን፣ ሐሳበ ከዋክብትን ሐሳበ ዐበቅቴን ወዘተ አጠቃሎ የያዘ እንደ ባሕር የሰፋ በመሆኑ የሐሳብ ባሕር ተብሏል፡፡ የዘመን አቈጣጠር ማለት ስለማሕበራዊ ኑሮ ጠቄሜታና የሃይማኖት ተግባሮች ለማከናወን በሚያገለግል መልኩ ተፈጥሮአዊውን የወቅቶች ክፍፍል እርስ በርሳቸው የማመቻቸት ዘዴ ነው፡፡
ማርቆስ ወንጌላዊ

ሐሳበ ዘመን የዘመን አቆጣጠር ማለት ሲሆን የሐሳበ ዘመን ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ወይም ዓመተ ዓለም ማለት ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም የባሕር አዝዋሪቱ፣ መንገዱን፣ ጥልቀቱና ስፋቱ ረዥምና ሰፊ እንደሆነ የባሕረ ሐሳብ ትምህርትም መንገዱን ስፋቱ ልዩ ልዩ በሆነ የአጽዋማትና የሱባዔያት ምሥጢር የተሰናዳ ስለሆነ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር /የጊዜ ቀመር/ አንድ ዓመት በውስጡ ዐሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ አራቱ ክፍላተ ዘመን የሚባሉት፡-

1-    ክረምት - ከሰኔ 26 ቀን - መስከረም 25 ቀን፣

2-     መፀው /መከር/ - ከመስከረም 26 ቀን - ታኅሣሥ 25 ቀን፣

3-    በጋ /ሐጋይ/ - ከታኅሣሥ 26 ቀን - መጋቢት 25 ቀን፣

4-    ጸደይ /በልግ/ - ከመጋቢት 25 ቀን - ሰኔ 25 ቀን ናቸው፡፡


ከክረምት በስተቀር እያንዳንዱ ወቅት በውስጡ ዘጠና ዘጠና ቀናት ይዟል፡፡ ክረምት ግን ለብቻው 95 ቀናትን የያዘ ነው፡፡


2. አራቱ ክፍላተ ዘመን

የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ጊዜ፣ ወር፣ ዘመን አላቸው፡፡ አንድን ዓመት በአራት ክፍለ ዘመን በመክፈል ድርሰቱን ውሱን አድርጎታል፡፡ ዘመኑም እንዲሁ በድርሰቱ የተወሰነ ሆኗል፡፡ እነዚህም ዘመናት ዘመነ መፀው ዘመነ ሐጋይ፣ ዘመነ ጸደይ፣ ዘመነ ክረምት በመባል ይታወቃሉ፡፡


2.1. ዘመነ መፀው

መፀው በሌላ አነጋገር ጥቢ ይባላል፡፡ እንደ ሌሊት ከብዶ የሚታየው ክረምት አልፎ መስከረም ከጠባ በኋላ 4ኛው ሳምንት ስለሚጀምር ነው ጥቢ የሚባል ተጨማሪ ስያሜ የተሰጠው፡፡

ዘመነ መፀው ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ የዕለቱ ቁጥርም 90 ይሆናል፡፡ ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ በመሆኑ ዘመነ ክረምትን በማስቀደም ፅጌንና መፀውን በማስተባበር ቅዱስ ያሬድ የሚከተለውን ብሏል፡፡ግሩም በሆነው ኃይልህ እንመካ ዘንድ አንተ ዘመናትን ሠራህ ክረምትን ለዝናባት መፀውን ለአበቦች ሰጠህድጓ ዘጽጌ ኩፋሌ 2 ኢዮ.2÷23 ኤር.524/

መፀው መሬት በክረምት የተሰጣትን ዘር አበርክታ፣ አብዝታ ለፍሬ የምታደርስበት የምርት ወቅት ነው፤ መፀው በአብዛኛው የአዝመራ መሰብሰቢያ ጊዜው ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን በዋናነት ሦስት ወራት ያገኛሉ፤ እነርሱም ጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ ናቸው፡፡ ይህ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር አበቦች በየሜዳው በየሸንተረሩና በየተራራው ፈክተው የሚታዩበት አዝርእት የሚያሸቱበትና ለፍሬ የሚበቁበትን ወራት ይዞ ይገኛል፡፡


2.2. ዘመነ ሐጋይ /በጋ/

ዘመነ ሐጋይ ይህ የበጋ ወቅት ነው፡፡ሐጋይ”…. በጋ ሆነ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ ይህም ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ ሐጋይ በጋ የጥርን፣ የየካቲትንና የመጋቢትን ወር ይይዛል፡፡
ዘመነ ሐጋይ የቃሉ ትርጓሜ ዘመነ ፀሐይ ማለት ሲሆን ሥርወ ቃሉም ኃገየከሚለው ግዕዝ የተገኘ ነው፡፡ ከአራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ እጅ ወይም አንድ አራተኛው ሐጋይ ይባላል፡፡ የሐጋይ ፍቺ በጋ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም መፀውም ጸደይም በእርሱ ስም በጋ ይባላሉ፡፡ዘጠኝ ወር በጋእንዲሉ፣ አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍት በሁለት ከፍለው ይናገራሉ፡፡ክረምትና በጋን አንተ ሠራህበበጋም በክረምትም እንዲህ ይሆናል” /መዝ.7517 ዘካ.1410 ዘፍ.1022/ እንዲል ኃጋይ ማለት መገኛ መክረሚያ በጋ፣ ፀደይ፣ ደረቅ ወቅት ነው፡፡

በዚህ ወቅት በመፀው ያሸተውና ያፈራው መኸር የሚታጨድበት፣ የሚሰበሰብበትና በየማሳው ከተከመረ በኋላ የሚበራይበት፣ በጎተራ የሚከተትበት በመሆኑየካቲትየሚለውን ወር ይዞ እናገኘዋለን፡፡ የግብርናው ኅብረተሰብ እህሉን በጎተራው ከትቶ ለተወሰነ ጊዜ የሚያርፍበት በመሆኑ የዓመት በዓላት እንደ ልደት፣ ጥምቀት ያሉት፣ ዘመነ መርዓዊ የሚባለው የጋብቻ ዘመን በዚህ ወቅት የተካተቱ ናቸው፡፡

2.3. ዘመነ ጸደይ /በልግ/

ዘመነ ጸደይ ማለት የቃሉ ትርጉም ዘመን በልግ ማለት ነው፡፡ ጸደይ በበጋና በክረምት መካከል የሚገኝ በውስጡ የሚያዝያን፣ የግንቦትንና የሰኔ ወራትን የያዘ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም ጸደይ የሌሎች ወቅቶችን ባሕርያት አሳምሮ የያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል የበልግ አዝመራ የሚታጨድበት የሚወቃበትና የሚዘራበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለክረምት የሚዘራ ማሳ የሚታረስበት /ለዘር ዝግጁ የሚሆንበትን ጊዜ ነው፡፡ በአብዛኛው ግን ዘመነ በልግ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ በድጓውይሁብ ዝናመ ተወንየበልግ ዝናምን ይሰጣል እንዳለው የበልግ ወቅት ነው፡፡ ይህም ወቅት በልግ አብቃይ በሆነው የሀገራችን ክፍል የበልግ አዝመራ የሚዘራበት፣ በልግ አብቃይ ባልሆነው ክፍል ደግሞ መሬት ለክረምቱ የዙር ጊዜ የሚያዘጋጅበት ነው፡፡አንድ ሰኔ የነቀለውን ሁለት ሰኔ አይተካውምእንደሚባለው የግብርናው ኅብረተሰብ ቀጣይ የግብርና ሥራውን በትጋት የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡

2.4. ዘመነ ክረምት

ዘመነ ክረምት ማለት ዘመነ ውሃ ማለት ነውና በዚህ ዘመን ውኃ ይሰለጥናል፡፡ ውሃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፣ ቢሆንም በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ይኖራል፡፡
ክረምት በውስጡ አራት ወራትን /ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ጳጉሜንና መስከረም/ የያዘ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድያረሁ ክረምተ በበዓመት፣ ይሰምዑ ቃሎ ደመናት፣ በየዓመቱ ክረምትን ያገባል፤ ደመናትም ቃሉን ይሰሙታልሲል በድጓው እንደነገረን የዘመናት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር በየዓመቱ አዙሮ የሚያመጣልን ወቅት ነው፡፡ ደመናትም ለቃሉ ትእዛዝ ተገዢዎች በመሆን ዝናመ ምሕረቱን ጠለ በረከቱን የሚያወርዱበት ጊዜ ነው፡፡ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለውን ጊዜ ይይዛል፡፡


3. ዓመተ ወንጌላውያን

የሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም የዮሐንስ፣ የማቴዎስና፣ የማርቆስ ዘመናት እያንዳንዳቸው ከመስከረም 1 ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 5 ድረስ 365 ቀን ከስድስት ሰዓት ነው፡፡ ዘመነ ሉቃስ ግን ከመስከረም 1 እስከ ጳጉሜን 6 ቀን በመሆኑ 366 ቀናት ይኖሩታል፡፡

4. ወራት

በግዕዝ ቋንቋወርሃየምንለው ቃል በአማርኛ ወር እንለዋለን ይህም ወደ ብዙ ቁጥር ሲለወጥ ወራት ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው 12 ወራት፣ 5 ወይም በየአራት ዓመት 6 ቀናት የሆነች ጳጉሜን ያሉ ሲሆን በአውሮፓውያን አቈጣጠር ግን የየወሩ የቀናት ቁጥር ለየት ይላል፡፡


የወራቱ ስም
የግዕዝ መገኛው
አማርኛው ትርጉም
1
መስከረም
ከረመ
ከረመ/ ይጠብቃል/
2
ጥቅምት
ጠቀመ
ጠቀመ/ ይጠብቃል/
3
ህዳር
ኀደረ
አደረ
4
ታኅሣሥ
ኀሠሠ
ፈለገ
5
ጥር
ጠየረ
መጠቀ/ወደ ላይ ተመረመረ
6
የካቲት
ከተተ
ሰበሰበ
7
መጋቢት
መገበ
መገበ/ ይጠብቃል/
8
ሚያዝያ
መሐዘ
ተጐዳን
9
ግንቦት
ገነባ
ገነባ
10
ሰኔ
ሠነየ
አማረ
11
ሐምሌ
ሐምለ
ለመለመ
12
ነሐሴ
ነሐሰ
ሠራ

5.ሳምንት

ሳምንትሰመነስምንት አደረገ ከሚለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ በሕገ ዑደት መሠረት ዕለት ከተነሣበት ማለትም ከእሑድ እስከ እሑድ ያለው ጊዜ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ ያሉት ቀናት እያንዳንዳቸው 24 ሰዓት ያላቸው ናቸው፡፡ እሑድ ማለትአሐደአንድ አደረገ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ስለሆነ ትርጉሙ አንድ ማለት ነው፡፡ ሰኞ ሁለተኛ ማክሰኞ /ማግስት/ ሦስተኛ፣ ረቡዕ አራተኛ፣ ሐሙስ አምስተኛ፣ ዓርብ ስድስተኛ ፣ቅዳሜ ሰባተኛ ቀን ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን በስድስት ቀናት /ከእሑድ - ዐርብ/ ፈጥሮ ያረፈባትና ሰዎችም እንዲያርፉበት ያዘዛት ሰባተኛዋ ቀን በግዕዝ ቀዳሚት ሰንበት ተብላ ትጠራለች፡፡

6. የዕለታት ስያሜ

1. እሑድ አሐደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አንድ አደረገ /የመጀመሪያ ሆነ/ ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ፍጥረታት መፈጠር ስለጀመሩ እሑድ ተብሏል፡፡

2. ሠኑይ /ሰኞ/ ሠነየ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሁለት አደረገ ማለት ነው፡፡ ለሥነ ፍጥረት ሁለተኛ ስለሆነ ሰኑይ/ ሰኞ/ ተብሏል፡፡

3. ሠሉስ/ማክሰኞ/ ሠለሰ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ሦስት አደረገ ማለት ነው፡፡ ማክሰኞ የሚለው የሰኞ ማግስት ማለት ነው፡፡

4. ረቡዕ ረብዐ /አራት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ ፍጥረት አራተኛ ቀን ማለት ነው፡፡

5. ሐሙስ፡ ሐመሰ /አምስት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ ፍጥረት አምስተኛ ቀን ማለት ነው፡፡

6. ዓርብ ዓረበ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ተካተተ ማለት ነው፡፡ ፍጥረታት እሑድ መፈጠር ጀምረው አርብ ስለተካተቱ /ተፈጥረው ስለተፈፀሙ/ አርብ ተብሏል፡፡

7. ቅዳሜ፡ ቀዳሚት ማለት ሲሆን ሰንበተ ክርስቲያን ከሆነችው ከዕለተ እሑድ ቀድማ ስለምትገኝ ቀዳሚት ሰንበት /ቅዳሜ/ ተብላለች፡፡

7.2006 ዓ.ም. የአጽዋማትና የበአላት ማውጫ


ማጠቃለያ
አሁን ያለውን የዘመን አቆጣጠር አስልተን እንድንቆጥር ያደረገው የባሕረ ሐሳብ ደራሲ የሆነው የእስክንድርያ 12 ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው፡፡ ይሄ አባት በደረሰልን የቁጥር ቀመር መሠረት በዓላትን አጽዋማትን መቼ እንደሚውሉ እያሰላን እንጠቀማለን አሁንም የአቡሻህር መምህራን ከመቁጠርያቸው ጀምሮ እስከ አቆጣጠራቸው እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ መነሻውም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ስሌቱን እያስፋፉት ይገኛል፡፡

ክፍል 2 ይቀጥላል - ይቆየን
አዲሱን ዓመት የሰላም ፤ የፍቅር ፤ የብልጽግና ፤ የንስሐ  ያድርግልን

ዋቢ ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

7 comments:

  1. Sinkesar come back again I am very Happy Thank you very much ዲያቆን መልአኩ እዘዘው

    ReplyDelete
  2. እንኮን አደረሰኅ ፤ መጭው ዘመን የሰላም የጤና እንዲሆንልሕ ኦመኛለሑ። በርታ!

    ReplyDelete
  3. kalwehiwot yasemalen.thank you again




    ReplyDelete
  4. በእውነት ቃለ ህይወት ያሰማልን 🌻🌻🌻🌻🌻

    ReplyDelete