Tuesday, March 19, 2013

ምኩራብ (የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)



አዲስ አበባ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ) 

ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡ 

ትርጉም: ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው) ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ። 

Friday, March 8, 2013

ዐቢይ ጾም


በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሕልና ትውፊት  እና ሥርዓት መሠረት በዘንድሮው ዓመት በመጪው ሰኞ መጋቢት 2 2005 ( 11  ማርች 2013 ) የሚጀመረው የጾም ወራት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው፣ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡


   ይህ ታላቅ የሆነው የጾማችን ወራት በተለያየ ስያሜ  ይጠራል፡፡
1. ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡

ሌሎች አጽዋማት ከቅዱሳን አበው የወረስናቸው የኑሮአቸው ፍሬዎች (ዕብ.13፤7) ሲሆኑ ይኼኛው ግን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ (ታላቅ) ይባላል፡፡ የጌታ ጾም ስለሆነ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሡበት፣ ድል የሚነሡበት ጾም ስለሆነም ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡