Friday, December 30, 2011

በዓለ ልደቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት


አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ  ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ . ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ ማለት ነው፡፡ አባታቸውየቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲያስተምሯቸው አካባበቢያቸው ደግሞ በዘመኑ የነበሩ ልጆች ይማሩ የነበረውን ፈረስ መጋለን፣ ቀስት መወርወርን፣ እርሻን እና አደንን አስተምረዋቸዋል፡፡
ደብረሊባኖስ ገዳም     
በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለክህነት መጠራት በዚህ ዓለም ትዳር መሥርቶ፣ የዓለሙንም ሥራ ሠርቶ መኖር አያስፈልግም ከሚልፍልስፍና የመነጨ አይደለም፡፡ 8ኛው መክዘ ጀምሮ በሀገሪቱ የመንፈስ መቀዛቀዝ ይስተዋል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ነው የተክለሃይማኖት የጥሪ ምክንያት፡፡

Wednesday, December 28, 2011

ቅዱስ ገብርኤል



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በተረዳኢነቱና በአማላጅነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ ይወደዳል፡፡ ምክንያቱም ያዘኑትን ለማጽናናት የምሥራች ለመንገር ከእግዚአብሔር ወደ ምእመናን ይላካልና፡፡
ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል ጌታና አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱሳን ሰማእታት ገድላቸውን እንዲፈጽሙ እሳቱንና ስለቱን ተሳቀው ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ይረዳቸዋል፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የቅዱሳን መላእክትን ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላቸውን በፀሎትና በምሥጋና ታከበራለች፤ በተለይ ታህሣሥ 19 ቀን የሚከበርበት ምክንያት ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሠለሥቱ ደቁቅን ከዕቶነ እሳት ( ከነደደ እሳት ) ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡

Tuesday, December 27, 2011

ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ


የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን



የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ስቴ ወረዳ የሚገኝ ነው ፡፡

በዐጼ አድያም ሰገድ ኡያሱ ዘመነ መንግሥት የተተከለዉ ጥንታዊዉና ታሪካዊዉ ደብረ ሃማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በሦስት ታላላቅ ጉባኤያቱ የታወቀ ነበር፡፡
1. በብሉይና ሐዲስ ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ
2. በቅኔ ቤተ ጉባኤ
3. በድጓ ቤተ ጉባኤ
በሦስቱም አብያተ ጉባኤያት ታላላቅ ሊቃዉንትን ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲያበረክት የቆየዉ ይህ ታሪካዊ ቦታ እስከ 1950ዎቹ ሦስቱም ጉባኤያት የነበሩት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን የቅኔ ጉባኤ ቤቱ ታጥፎ የትርጓሜ መጻሕፍቱና የድጓ ጉባኤዎቹ ግን አሁንም ሳይታጎሉ የሚሰጥበት ቦታ ነዉ፡፡

Friday, December 23, 2011

አቡነ ዮሐንስ ዘጎንድ ተክለሃይማኖት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የጎንድ ተክለሃይማኖት የአንድነት ገዳም አባቶች ለሥራ ጉዳይ ወደጎንደር ከተማ መጥተው ስለነበር ሥራቸውን አጠቃለው ወደገዳማቸው ሲመለሱ በነበረን ቀጠሮ መሠረት አብሬአቸው ወደጎንድ ተክለሃይማኖት ገዳም መንገድ ጀመርን ፡፡
ወደማክሰኝት ከተማ የሚወስደውን ሚኒባስ በመያዝ የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረሥላሴ ፤ የገዳሙ አፈ መምህር አባ ገብረመድኅን እንዲሁም የገዳሙ ተወካይ አባ በትረስላሴ በጋራ በመሆን አርባ ኪሜ ከጎንደር ከተማ ርቀት የሚገኘውን የማክሰኝት ከተማ ስለገዳሙ እየተነጋገርን ደረስን ፡፡
ማክሰኝት ከተማ በሚገኘው የገዳሙ የእንግዳ ማረፊያ ቤት የሚቀጥለውን መኪና እስክናገኝ ዕረፍት ልናደርግ ስንገባ የገዳሙ አባቶችን መምጣት የተመለከቱት የአካባቢው ምዕመናን ከቤታችን ካልገባችሁ እያሉ ልመናቸውን አበዙት ፡፡ በመጨረሻም የሚበላ እና የሚጠጣ በመያዝ ወደገዳሙ የእንግዳ ማረፊያ ቤት ይዘው መጥተው በሚገባ አስተናገዱን ፡፡ የምዕመናኑ ለአባቶች ያላቸው ፍቅር እና ደጋግመው ሁሉም ማለት ይቻላል እንዲያው ለረድኤቱ ብለን ነው የሚሉት  ንግግራቸው ያላቸውን ፍቅር ይገልጻል ፡፡

Monday, December 12, 2011

በዓታ ለማርያም


እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና እም ሊባኖስ ትወጽዕ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡
ከዚህ በኋላ እመቤታችን መዋዕለ ጥብ እስክታደርስ ድረስ በአባት እናቷ ቤት 3 ዓመት ተቀመጠች፡፡ ከመዝ ነበረት ውስተ ቤተ አቡሃ ወእማ 3ተ ዓመተ እንዘ ትጠቡ ሐሊበ እማ (እንዳለ በነገረ ማርያም፡፡)
ኢያቄምና ሐናም ልጃቸውን ሲያሰሳድጉና ስላደረገላቸውም ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው ሲያመሰግኑት ሦስት ዓመት ኖሩ። በጾም፤ በጸሎት ተወስነው ለድሆችና ለጦም አደሮች ምፅዋት እየሰጡ በጐ ሥራ መሥራትን አበዙ።
      ልጃቸውንም ድንግል ማርያምን በንጽሕና ሲያሳድጉ ሦስት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሐና ባሏን ኢያቄምንወንድሜ  ሆይ ልጃችንን ለቤተ እግዚአብሔር ብፅዐት አድርገን እንስጥ። ልጃችን ቤተ እግዚአብሔርን ልታገለግል እንጂ በዚህ ዓለም እኛን ልታገለግል እንዳልተሳልን አስብ አለችው።ኢያቄምም ይህን ነገር ከሚስቱ በሰማ ጊዜ ደስ አለው።