Sunday, September 21, 2014

ቅድስት ዕሌኒ




 የቅድስት ዕሌኒ ባለቤቷ ተርቢኖስ ይባላል፤ በቅድስና ተፋቅረው ነበር የሚኖሩት፤ ተርቢኖስ የሚል ጽሁፍ ያለበት የአንገት ሀብል አሰርቶላት ነበር። ተርቢኖስ ነጋዴ ስለነበር ከጓደኞቹ ጋር በመርከብ ተሳፍረው እሩቅ አገር ሄደው  3 ዓመት በኃላ ይመለሳሉ ፤ ታዲያ መርከብ ላይ እንዲህ እያሉ ይጫወታሉ ፤ እኛስ በሰላም ወደ አገራችን ተመለስን ሚስቶቻችን ግን በሰላም ይጠብቁን ይሆን ሌላ ወንድ ወደውና ለምደው እንዳይጠብቁን አሉ፤ ተርቢኖስ ደግሞ የኔ ሚስት ዕሌኒ ከኔ ሌላ ማንንም አትወድም አትለምድም ይላቸዋል፤ ያንተ ሚስት ከሄዋን ሴቶች ትለያለችን እኔ ሄጄ ወድጃት ወዳኝ ለምጃት ለምዳኝ ብመጣ ምን ትሰጠኛለህ ይለዋል ንብረቴ ሁሉ ላንተ ይሁን ይለዋል በወረታቸው ተወራርደው ይሄዳል::
 የዕሌኒን ገረድ አስጠርቶ 20 ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ ሁለቱ ብቻ የሚተዋወቁበትን አንድ ነገር ስጪኝ ይላታል፤ እርሷም እሺ አንተ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እያልክ ለፍፍ ትለዋለች፤ እንዳለቸው እየዞረ ለፈፈ፤ ገረዷም ወደ ዕሌኒ ቀርባ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እየተባለ ነው ገላሽን ታጠቢ ሽቶም ተቀቢ ትላታለች፤ዕሌኒም የአንገት ሀብሏን አስቀምጣ ገላዋን ልትታጠብ ትገባለች ይህን ጊዜ ወስዳ ትሰጠዋለች፤ እርሱም ተርቢኖስ ጋር ሄዶ እየው እፍቅራኝ ውድ ስጦታ ሰጠቺኝ ብሎ ያሳየዋል፤ ሀብሉን ተመለከተው ተርቢኖስ የሚል ፅሁፍ አለበት አመነው፤ አያዘነ 3 ዓመት የደከመበትን ንብረት አስረክቦ እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ገባ::
ምን ሆነሃል አለችው ንብረቴን መአበል ወሰደቢኝ አላት፤አትዘን አንተም እኔም ብዙ ወዳጆች አሉን ተበድረን ትነግዳለህ ትለዋለች፤ እርሱም በአሽሙር ልክ ነሽ ያንቺ ወዳጆች ብዙ ናቸው እኔ ግን ወዳጅ የለኝም ደግሞም ባበደርኩበት አገር ተበድሬ በከበርኩበት አገር ተዋርጄ አልኖርም ወደ ሌላ አገር እሄዳለሁ ይላታል፤ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው ካንተ አልለይም ትለዋለች፤ በመርከብ ተሳፍረው ይሄዳሉ በህሩ መሀል ሲደርሱ ሀብሉን አውጥቶ ያሳያታል ስወድሽ ጠላሺኝ ሳምንሽ ካድሺኝ ይላታል፤ ልታስረዳው ሞከረች አላመናትም በሰጥን ውስጥ አድርጎ ስራሽ ያውጣሽ ብሎ ከባህር ጣላት::
 ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃት ሳጥኑ ተንሳፎ ሄዶ ባህር ዳርቻ ያርፋል አገሩ ሮም ነው ቆንስጣ የተባለ አገር ገዢ ሳጥኑን ሲከፍተው እጅግ የምታምር ሴት አገኘ፤የእየሱስ እናት ማርያም የምትባይው አንቺ ነሽን ይላታል፤እኔ የእርሷ ገረድ ነኝ እንጂ እርሷን አይደለውም፤ ጊዜ ያዋረደኝ ወቅት የጣለኝ ሴት ነኝ ትለዋለች፤ወደ ቤተመንግስቱ ይዟት ገባ፤ በክብር እስከ 6 ወር ጠበቃት ከዚያም አገባት በግብርም አወቃት፤መስከረም 12 ቆስጠንጢኖስ ተወለደ፤ በድብቅ የሃይማኖት ትምህርት አስተማረችው ምክንያቱም ባለቤቷ ጣኦት አምላኪ ነበርና፤ ልጇ  25 ዓመቱ በሮም ነገሰ ክርስትናንም ተቀበለ::
 ዕሌኒም የጌታን መስቀል ለማስወጣት እየሩሳሌም ሄደች ከብዙ ልፋት በኃላም መስከረም 16 ደመራ ደምራ መስቀሉን አገኘች፤መስከረም 17 ቁፋሮ ጀመረች  6 ወር ቁፋሮ በኃላ መጋቢት 10 መስቀሉ ወጣ፡፡ ብዙ ተአምራትም ተደርገዋል፤ ለእግዝያብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም ከመስቀሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
እሌኒ ቅድስት  80 ዓመቷ ጌታችን ተገልጾ ወዳጄ ዕሌኒ ወደ እኔ ልወስድሽ ነው አላት፤ ደነገጠች፤ ምነው ፈራሽ መኖር ትፈልጊያለሽ እንዴ ይላታል፤ እንዳመሰግንህ ትንሽ ብቆይ ትለዋለች፤ ስንት ዓመት ልጨምርልሽ ይላታል፤ ይህማ ባንተ ቸርነት መገባት ይሆን የለም ወይ ትለዋለች፤ 40 ዓመት ጨምሬልሻለሁ ይላታል  120 ዓመቷ ግንቦት 9 ቀን አረፈች ፡፡
የቅድስት ዕሌኒ በረከቷ ይደርብን - አሜን

Sunday, September 14, 2014

ለውጥ በሌለው ሕይወት አቆጣጠር - ዛሬ ስንት ዓመተ ምሕረት ነው ?

አንድ ሶርያዊ ክርስቲያን የሚከተለውን ደብዳቤ በ1983 . ጽፎ ነበር፡፡ ደብዳቤው እንዲህ ይነበባል፡-
«እስከ 1970 . (የተወለደው 1943 . ነው) «በቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት ሥጋ ወደሙ እቀበል ነበር፣ አሥራት አወጣ ነበር፣ ገዳማትን ለመርዳት የተቋቋመ ማኅበር አባል ሆኜ ሌት ተቀን እሠራ ነበር፣ ሁል ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ውስጥ የመለወጥ ስሜት ነበረኝ፣ ለመማር፣ ለመጾምና ለመጸለይ የነበረኝን ትጋት አስታውሰዋለሁ፡፡
ይሁን እንጂ በ1970 ዓ.ም መንፈሳዊ ሕይወቴ ባለበት ቆመ፡፡ እንኳን ከበፊት የተሻለ ምግባር ልፈጽም የነበረኝንም እየተውኩት መጣሁ፡፡ ድካምና መሰልቸት ሕይወቴን ተጫጫነው፡፡ ራዕይ አጣሁ፡፡ ከፊት ለፊቴ ምንም ነገር አይታየኝም፡፡ ግድግዳ ያለ ይመስለኛል፡፡ ቤተክርስቲያን በበለጠ ለማገልገል የነበረኝ ጉጉት ሁሉ ሞተ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም ደብዳቤ ዓመተ ምሕረቱን 1970 እያልኩ እጽፋለሁ፡፡ እስከ አሁን ድረስ (1983 ዓ.ም ማለቴ ነው) በኔ አቆጣጠር 1970 ዓ.ም ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ በኑሮዬ ውስጥ ምንም የተለወጠ፣ ያደገ ወይም የተስተካከለ ነገር የለምና፡፡ ብፁዕ አባታችን፡- እባክዎ ምክርዎን በመለገስ ወደ 1971 ዓ.ም ያሸጋግሩኝ;»
ሕይወት ካልተለወጠ፣ ካላደገ፣ ሃይማኖት ካልሰፋ፣ ምግባር ካልጸና ፣ ትናንት ያሸነፉንን ኃጢአቶች ዛሬ ካላሸነፍን፣ የደከመውን አበርትተን፣ የተሰበረውን ካልጠገንን፣ ዘመን ተለውጦ ዘመን ቢተካም፣ የምድርን ዕድሜ እንቆጥራለንን እንጂ እኛ እንደሆንን እንደቆምን ነን፡፡
አንዳንዶቻችን ያኔ ሕጻን ሆነን ሥጋ ወደሙ እንደተቀበልን፣ ሌሎቻችን በወጣትነት ለሰንበት ት/ቤትና ለጽዋ መርሐ ግብር በነበረን ትጋት ላይ ሌሎችም በማስተማር፣ ቤተክርስቲያንን በማሰራት፣በማስቀደስ በመጸለይና በመጾም፣ በነበረን የጥንት ምግባር አንዳንዶችም ወደ ምንኩስና (ምናኔ) ሲገቡ በነበራቸው የወጣኒነት ትጋት እዚያው ላይ ዓመተ ምሕረታችን ቆሟል፡፡
አዲስ አበባ አራት ኪሎ መሐል የአርበኞች ኃውልት አለ፡፡ እዚያ ኃውልት ጫፍ ላይ ሰዓት ተሰቅሏል፡፡ ሰዓቱ የሚያመለክተው አርበኞች አዲስ አበባ የገቡበትን ሰዓት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ቆሟል፡፡ የዛሬው ትውልድ ያንን ሰዓት ሲያየው ጀግኖች አባቶቹ ጠላትን ድል አድርገው ሀገሪቱን ነጻ ያወጡበትን ጊዜ ያስብበታል፡፡ ያ ሰዓት የጥንቲቱን ተግባር ብቻ እያመለከተ ቆሟል፡፡ የዛሬውን ትውልድ ጀግንነትና ዝና የሚያሳይ ሰዓት ግን የለም፡፡
 የብዙዎቻችን ሰዓት ቆሟል፡፡ በአንድ ወቅት የሠራነውን መልካም ስራ፣ የነበረን መንፈሳዊ ትጋት፣ የሃይማኖት ጥንካሬና ሰማይ ጥግ የደረሰ ዝና እያመለከተ ቆሟል፡፡ ዛሬ በአቡሻህር አቆጣጠር 2007 ዓ.ም ነው:: በእኛ አቆጣጠርስ ስንት ነው; ያ ሶርያዊ ክርስቲያን «በኔ አቆጣጠር 1970 ዓ.ም ነው» ብሏል፡፡ እርሱ የነበረበትን ዘመን ግን እስከ 1983 ዓ.ም ነበር፡፡
የዘመን መለወጫን በዓል አከበርነውም አላከበርነውም ዘመኑ መለወጡ አይቀሬ ነው፡፡ እያንዳንዷን ቀን ተጠቀምንም አልተጠቀምንም ጊዜው መሮጡ አይቀርም፡፡ እርሱ የራሱን ጊዜ ይቆጥራል፡፡ ይለወጣል፡፡ እኛስ;

 እስቲ ጊዜ ሰጥተን ራሳችንን እንመርምረው፡፡ በሃይማኖት እየጸኑ፣ በምግባር እየበረቱ፣ በትጋት እየጨመሩ፣ በመንፈሳዊ እውቀት እያበሩ፣ ሰማዕትነትን ይበልጥ እያፈኩ ካልሄዱ ዘመኑ ብቻውን ቢቀየር «እንኳን አደረሳችሁ» ያስብላልን;
የአክሱምንም አደባባይ የጎበኘ ሰው ሦስት ነገሮችን መታዘብ ይችላል፡፡ ተጠርቦ ተቀርጾ ሃውልት የሆነ ድንጋይ አለ፡፡ ሃውልት ለመሆን ተጠርቦ ቅርጽ ሳይወጣለት ልሙጥ ሆኖ የቀረ አለ፡፡ ለሀውልትነት ተመርጦ ሳይጠረብ ሳይቀረጽ የቀረ አለ፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞም እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ለሰማያዊ ዋጋ ተመርጠው በብዙ ፈተና ተጠርበውና ተቀርጸው ጉዞአቸውን የፈጸሙ አሉ፡፡ ተመርጠው ተጠርበው ግን ገና ቅርጽ መያዝ ሲቀራቸው ባሉበት የቀሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ተመርጠው ከመጡ በኋላ ከዚያ ያለፈ ተግባር ላይ ያልዋሉም አሉ፡፡ የእነዚህ የሦስቱም የዘመን አቆጣጠራቸው ይለያያል፡፡ አንዱ በደረሰበት ዓ.ም ሌሎቹ አልደረሱምና፡፡
በወንጌል ታሪኩ የተጠቀሰው የጠፋው ልጅ አባት ልጁ ከጠፋበት ሀገር ሲመለስ «ይህ ልጄ ሞቶ ነበር ህያው ሆኗል» ብሎ ነበር የተናገረው፡፡ ያ ልጅ እኮ ይንቀሳቀሳል፣ ይበላል፣ ይጠጣል ግን ሞቷል ተባለ ለምን; የሱ የዘመን አቆጣጠር ከአባቱ ቤት ሲጠፋ መቁጠሩን አቁሞ ነበርና፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞ የነበረው ለውጥ ስላቆመ ሞተ ተባለ፡፡ ትልቁ ጥያቄ ማን ተለወጠ ነው፡፡ ዘመን ተለወጠ; ሰው ተለወጠ; ወይስ ሁለቱም ተለወጡ; ዘመን ይለወጣል፡፡ አይቀሬ ነው፡፡ የስነ ፍጥረት ስርዓት ሁሉ የእግዚአብሔርን ህግ ሳያፋልስ ይኖራልና፡፡ አስቸጋሪው ነገር እርሱ አይደለም፡፡ እስከ ዘመነ ምጽዓት ዘመን ይመጣል፣ ያልፋል፣ በሌላ ይተካል፡፡ ሰው ተለወጠ; ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ግን ከባድ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ከባድ ያደረገው በሰው ኑሮ ውስጥ ሦስት ዓይነት ለውጥ ስላለ ነው፡፡ በመንፈስ መለወጥ፣ በአካል መለወጥ፣ በባሕላዊም ይሁን በዘመናዊ መንገድ በሚገኝ እውቀት የሰው እውቀት ይለወጣል፣ ያድጋል፣ ይሰፋል፣ ይጎለምሳል፡፡ ወደደም ጠላም የሰው አካል የተፈጥሮውን ሂደት ጠብቆ ይለወጣል፣ ጽንሱ ይወለዳል፣ ሕጻኑ ያድጋል ወጣት ይሆናል፣ ወጣቱ ይጎለምሳል፣ ጎልማሳው ያረጃል፣ አካላዊ ጸባዩም በዚያው ልክ ይለወጣል፡፡
ትልቁ ፈተና መንፈሳዊ ለውጡስ የሚለው ላይ ሲደርስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ለውጥ ከነዚህ ከሁለቱ ለውጦች የተለየ ነው፡፡ ተጋድሎ ከሥጋና ደም ጋር አይደለምና፡፡ የሰውየውን ታላቅ ጥረት፣ ሰማዕትነት እና የሃይማኖትን ጽናት የግድ ይላል፡፡ በዚህም የተነሳ በእውቀት ጎልምሰው፣ በዕድሜ አርጅተው፣ በመንፈሳዊ ለውጥ ግን ገና ሕጻናት የሆኑ ወይም ደግሞ በሕጸንነት እድሜ ላይ የጊዜ መቁጠሪያ ሰዓታቸውን ያቆሙ ብዙ ናቸው፡፡
ሌላው ቀርቶ ስለ መንፈሳዊ ሕይወትና ስለ ሃይማኖት እጅግ ብዙ የተማሩ በእውቀት ለሌሎች ሊተርፉ የሚችሉ ሌሎችን አስተምረው ለፍሬ ያበቁ እንŸDን በመንፈሳዊ ሕይወት ለውጣቸው ገና ወጣኒያን ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡
ስለዚህም ሌላ የዘመን መለወጫ ከማክበራችን. አዲስ አመት ገባ እያልን ዶሮና በግ ከማረዳችን. እንደ ምዕራባውያውኑ ወደ ኋላሩ (Count down) ከመቁጠራችን በፊት ለቀጣዩ ጥያቄ መልስ እንፈልግ፡፡
ለውጥ በሌለው ሕይወት አቆጣጠር - ዛሬ ስንት ዓመተ ምሕረት ነው ?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር