Thursday, July 7, 2011

አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ

አባ ሙሴ ጸሊም በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አስቀድሞ በውንብድና ኑሮ ሕይወቱን ይገፋ ነበር፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል፡፡እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ ፤ በሥራውም ኃይለኛ ነበር፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ፤ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ፡፡ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር ፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም  ኢትዮጵያዊ

በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ፤ ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው፡፡  ያንጊዜም ተነሳ ሰይፉንም ታጥቆ ወደአስቄጥስ ገዳም ሄደ ፤ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው ፤ አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው ፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደአባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው፡፡ እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሰህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ
የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኮሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙ እና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ፡፡፡፡በኋላም በገዳመ አስቄጥስ የገዳሙ አበምኔት የነበረው የአባ ኤስድሮስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በአባ መቃርዮስ ምክር ወደ ጴጥራ ሂዶ በተባሕትዎ መኖር ቀጠለ፡፡ ከገድሉ ብዛት የተነሳ አረጋውያን መነኮሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውሃ መቅጃዎቹን ወስዶ ውሃ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር፡፡ ውሃው ከእነርሱ ሩቅ ነበርና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም በበአቱ እያለ የፈቲው ፆር ያሠቃየው ነበር፡፡ ፈተናውን ተቋቁሞ በበአቱ መቀመጥ ስላልቻለ ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ኤስድሮስ ዘንድ ሄደና ‹በበኣቴ መቀመጥ አልቻልኩም› አለው፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደ በኣቱ ተመልሶ በዚያው እንዲጸና መከረው፡፡ ሙሴ ግን ‹ፈጽሞ አልችልም› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ሙሴን ይዞት ከገዳሙ ቅጥር ውጭ አወጣው ከዚያም ወደ ምዕራብ አዞረውና ‹ተመልከት› አለው፡፡ በዚያ አቅጣጫ የአጋንንት መንጋ ለወረራ ሲዘጋጁና ሲንጫጩ አሳየው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ምሥራቅ እንዲመለከት አደረገውና እልፍ አእላፍ መላእክት ብርሃን ተጐናጽፈው አሳየው፡፡ ከዚያም ‹እነዚህ የብርሃን መላእክት ቅዱሳንን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ ናቸው እነዚህ ርኩሳን አጋንንት ደግሞ ቅዱሳንን ለመፈተን የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የብርሃን መላእክት ኃይል ከአጋንንት ኃይል ይበልጣሉና ጸንተህ ተጋደል› ሲል መከረው አባ ሙሴም ወደ በኣቱ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በገዳመ አስቄጥስ እያለ ከገዳማውያን አንዱ ጥፋት ሠራና ማኅበሩ ለፍርድ  ተሰበሰበ፡፡ አባ ሙሴ ግን በጉባኤው ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ካህኑ ተልኰ ‹ና. ሁላችንም አንተን እየጠበቅን ነው› አለው፡፡ አባ ሙሴም በሚያፈስስ ከረጢት አሸዋ ሞልቶ ያንንም በጀርባው ተሸክሞ ከኋላው እያፈሰሰ ወደ ጉባኤው አመራ፡፡ ጉባኤተኞቹ ተገርመው ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹የእኔ ኃጢአቶች በኋላየ እንደዚህ አሸዋ በዝተው ይፈሳሉ፤ ነገር ግን ላያቸው አልቻልኩም ዛሬ ግን በሌላው ላይ ለመፍረድ መጥቻለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ዝም አሉ፡፡ ያን ወንድምም በይቅርታ አለፉት፡፡
በሌላ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ያሉ መነኰሳት ተሰበሰቡና የአባ ሙሴን ትዕግሥት ለመፈተን ሲሉ “ይህ ጥቁር መነኩሴ ለምን እዚህ መጣ “ ብለው ተናገሩት፡፡ እርሱም ዝም አለ፡፡ ጉባኤው ሲበተን “አባ ክፉ ስንናገርህ ምንም ሐዘን አልተሰማህም ነበርን ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ተሰምቶኛል፣ ነገር ግን እንዳልናገረው አንደበቴን ተቆጣጠርኩት” አላቸው፡፡
በአንድ ወቅት በገዳመ አስቄጥስ ጾም ታወጀ፡፡ በዚያ ሳምንት አባ ሙሴን ለማየት ከግብጽ ወንድሞች መጡ፡፡ አባ ሙሴም በእንግድነት ተቀበላቸውና ምግብ ያበስልላቸው ጀመር፡፡ የእሳቱን ጢስ የተመለከቱ ጐረቤቶቹ “አባ ሙሴ ትእዛዝ አፍርሶ ምግብ ያበስላል” ብለው ለገዳሙ ሓላፊዎች ተናገሩ፡፡ ሓላፊዎቹም ‹አሁን ተውት ሲመጣ እኛው ራሳችን እናናግረዋለን› አሏቸው፡፡ ሓላፊዎቹም አባ ሙሴን ጠርተው ለምን ምግብን እንዳበሰለ ተረዱ፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ማኅበሩ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በአደባባይ ‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡
አንድ ጊዜ የአካባቢው ገዥ ስለ አባ ሙሴ ዝና ሰምቶ ያየው ዘንድ ወደ ገዳመ አስቄጥስ መጣ፡፡ ይህን የሰማው አባ ሙሴ ሸሽቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡ በመንገድም ላይ የገዥው መልእክተኞች አገኙትና ‹እባክህ አባ ሙሴ የት እንዳለ በኣቱን አሳየን› አሉት፡፡ ‹ከርሱ ምን ትሻላችሁ፤ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው› አላቸው፡፡ ይህን የሰማው የአካባቢው ገዥ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጣና የሆነውን ሁሉ ለአገልጋዮች ነገራቸው፡፡ ‹ብዙ ሰዎች ስለ አባ ሙሴ ሲያወሩ ሰምቼ ለማግኘት መጥቼ ነበር፤ በመንገድ ላይ ያገኘነው አንድ አረጋዊ ሰው ግን የአባ ሙሴ በኣት የት እንደሆነ ስንጠይቀው ከርሱ ምን ትሻላችሁ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው አለን› ብሎ ነገራቸው፡፡ አገልጋዮቹም በጣም ተናደዱና ‹ምን ዓይነት አረጋዊ ሰው ነው ስለ ቅዱሱ ይህን የሚናገር› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ትልቅ፣ ጠቆር ያለ፣ አሮጌ ልብስ የለበሰ ነው› አላቸው፡፡ አገልጋዮቹም ተገርመው ‹ይህማ ራሱ አባ ሙሴ ነው፤ ይህን ያለህ ሊያገኝህ ስላልፈለገ ነው› አሉት፡፡ የአካባቢው ገዥም ከአባ ሙሴ ሁኔታ ከንቱ ውዳሴን ስለ መሸሽ ትልቅ ትምህርት ተምሮ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በኣት ሠርቶ ወደ ጴጥራ ሲሄድ በአካባቢው ውኃ ስላልነበረ ተጨንቆ ነበር፡፡ አንድ ድምፅ ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› አለው፡፡ ስለዚህም በዚያ መኖር ጀመረ፡፡ አንድ ቀን በጴጥራ እያለ አበው ሊጐበኙት መጡ፡፡ የነበረችው ውኃ ጥቂት ነበረችና በርሷ ምግባቸውን አበሰለ፡፡ የሚያጠጣቸው ግን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ እየወጣ ውኃ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር፡፡ በመጨረሻ ዝናብ ዘነበና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ሁሉ ሞላቸው፡፡ እነዚያ አባቶችም ‹ትወጣና ትገባ የነበረው ለምን እንደሆነ እባክህ ንገረን› አሉት፡፡ ‹እናንተ በእንግድነት ስትመጡ ውኃ አልነበረኝም፣ ስለዚህ ያንተን አገልጋዮች ወደ እኔ ልከሃቸዋል፣ ነገር ግን ውኃ የለኝም፣ ስለዚህ እባክህ ውኃ ስጠኝ እያልኩ እግዚአብሔርን ለመለመን ነበር› አላቸው፡፡

 አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ሙሴም ‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት፡፡› አለው፡፡ ‹ሌላ አይጠበቅበትምን?› ሲል ያ ወንድም ጠየቀው፡፡ ‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ሓላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብጽን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም› አለና መለሰለት፡፡ ያም ወንድም ‹ምን ማለት ነው?› አለው፡፡ ‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ‹ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡› በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሓሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው፡፡
አንድ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ወንድሞች አብረውት እያሉ አባ ሙሴ ‹ተመልከቱ በርበሮች ገዳማችንን ሊያጠፉ እየመጡ ነው፡፡ ተነሡና ሽሹ› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ‹አባ አንተስ አትሸሽምን?› ሲሉ ጠየቁት፡፡ አባ ሙሴም ‹እኔማ ይህችን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ፡፡ ጌታ በወንጌል ‹ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ› ያለው ቃል (ማቴ. 25.52) ይፈጸማል፡፡› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹እኛም አንሸሽም፣ አብረን እንሞታለን እንጂ› አሉት፡፡ አባ ሙሴም ‹ያ ለእኔ ረብ የለውም፤ ሁሉም ሰው ለየራሱ ይወስን› ብሉ መለሰላቸው፡፡ በዚያ ለነበሩት ሰባት ወንድሞች ‹በርበሮች ወደ ገዳሙ ደጅ እየደረሱ ነው› ብሎ ነገራቸው፡፡ ወዲያውም በርበሮቹ ደርሰው ገዳማውያኑን በሰይፍ መቷቸው፡፡ ከሰባቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሸሸና በተቆለለው ሰሌን ውስጥ ተደበቀ፤ ወዲያውም ሰባት አክሊላት ሲወርዱላቸው ተመለከተ፡፡
የአባ ሙሴ ጸሊም በረከት ይደርብን አሜን
ዋቢ   ስንክሳር ሠኔ 24
በበረሓው ጉያ ውስጥ

39 comments:

  1. መሌ፣ እውነትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ እየጀመረ ነው፡፡ ምክንያቱም ትንሣኤ ከሃሳብ ትንሣኤ ነውና የሚጀምረው፡፡ ዕውቀት መብዛት፣ አማራጭ መብዛት፣ ምሁራን መብዛት አለባቸው፡፡ በተለይ ከዕውቀት አምባ ጎንደር ሆነህ ትጽፋለህና ታድለሃል፡፡

    ReplyDelete
  2. SELAME EGZIABHER KE HULACHEN GARE YEHUNE WENDEMACHEN TERU JEMER NEW BERETA...... EBAKHE SENKSARU GEN YEKETEL PLSSSS YE KIDUSANE AMELAKE BERETATE YEHUNEHE ,KE HAGERI SWIZERLANDE ..

    ReplyDelete
  3. ውድ ወንድማችን እግዚአብሔር ይባርክህ። በርታ!! ዛሬ ለቤተክርስቲያናችን የሚያስፈልገው ስለ ጌታችን እና ስለ ቅዱሳኖቿ የሚናገሩ አንደበቶች ናቸውና ከሊቃውንቱ ጠጋ ብለህ ለትውልዱ የሚያስፈልገውን ወርወር አድርግ። ዛሬ ውዥንብርን ተከትሎ መጯጯኹ መፍትሔ የለውም የሰው ልጅ ከዚህ ዘመን ሊያመልጥ የሚችለው ተገቢውን የቤተክርስቲያን ትምህርት ሲያውቅ ነውና ልንታነጽበት የምንችልበትን የቅዱሳኑን ገድልና ትሩፋት ታስነብበን ዘንድ ተስፋ እናደርጋለንለ።

    ReplyDelete
  4. በእርግጥ የአባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ ታሪክ - ዕፁብ ድንቅ የሆነ ቅዱስ ታሪክ ነው።። ዲያቆን ማለት ትርጉሙ አገልጋይ ማለት መሆኑን ሰምቻለው፤ በርግጥ አገልግሎትህን የእምየ ማርያም ልጅ ቸሩ መድኃኔዓለም ይባርክልህ ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው። ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› ……

    ልጃም

    ReplyDelete
  5. Egziabher yisteline wondimachin Dingel yasbikewun kefitsame tadrselike. Egnanime libonachinen abrto le hiywotachin mintekem yadrigen amen.

    ReplyDelete
  6. Thanks Dn Melaku for sharing...we need more from the place where you are!!! You are replacing [Babatoche eger] and following your fathers and am really happy to see the fruit of Leke Lekawont Menkere Mekonen Ze-Gondar. God Bless you and Gondar. May God keep Gondar-the source of our church teaching schools!!!

    Amen

    ReplyDelete
  7. ወንድም መላኩ በጣም ደስ ይላል በርታ የእግዚአብሔር እርዳታ ሁሌም ከአንተ ጋር ይሁን
    ፍቅርተ

    ReplyDelete
  8. Brother we are proud of you !! we except from you a lot !! God bless you ! long live

    ReplyDelete
  9. It is very attractive

    ReplyDelete
  10. betam desyilal

    ReplyDelete
  11. Diakon,
    Egziabher Yistilin!
    Kale Hiwot Yasemah!

    ReplyDelete
  12. I learned something I did not know before, thank you very much and God bless!

    ReplyDelete
  13. Kale Hiwot yasemalen.

    ReplyDelete
  14. ኦሆ አሁነ ዲያቆን መላኩ አፎኑ ሃለዎትከ? በከመ ረኢኩ ግብረከ አንሰ ተፈሳህኩ ብከ ። በዚህ ዘመን ስለ ክዱሳን የሚያስተምር ጠፍቶአልና በርታ

    ReplyDelete
  15. LET GOD BE WITH YOU. THANK YOU

    ReplyDelete
  16. oh my God I like this blog, that is so nice please continue on it. It is touchy to read our saint Fathers and will make us regret our sins.
    May God be with you.

    ReplyDelete
  17. IF you could please include interviews with our Fathers(gedamat)yalu ,we miss their voices,pictures, videos and blessings.
    I wish to see and support if our church would have network and we will be able to follow every cermony online and even when there is damage.
    I mean if there could be some computer technology
    which could do this. Give information about the church,history of each church,problems, expiriences and so on .

    I think we need to do a coordinated work.

    God bless our CHURCH and all of us.

    ReplyDelete
  18. kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete
  19. በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡

    ReplyDelete
  20. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዲን መልአኩ የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ታርክ መስማት ካቆምን እኮ ብዙ ጊዜያችን ሆኖል&ይህ ግን
    በጣም ጥሩና ለወደፊት ብዙ ለመስራት አመላካች ጅምር ነው::እስኪ አምላክ ብርታቱ ይስጥህና የሌሎች ኢትዮጵያዉያን ቅዱሳን(የነ ቅዱስ ያሬድ'ላሊበላ'ነአኩቶለአብ 'ሳሙኤል'መስቀል ክብራ'ክርስቶስሠምራ 'ተ/ሃይማኖት እና ሌሎች በስም እንካን የማናውቃቸው ቅዱሳን)ሕይወት በተለይ የሰሩት ሥራና ያስተማሩት ትምህርት አምላክ ባሰቻለህ መጠን አስነብበን(ኩሎ እክል በዘውእቱ አክሀለኒ ክርስቶስ እንዲል)::I am saying this because we are too late to announce Ethiopian saints to the world; I see the bibliography of pope Shenoda the 3rd in the Coptic site ; I admire them and I criticize my self by saying why there is no written bibliography of Ethiopian saints in the internet .even am not sure whether there is official site of EOTC that tells us about Ethiopian saints. This is what makes me sad &others too.
    Pls pls pls make a bibliography of Ethiopian saints in collaboration of other bloggers like dn Daniel kibret and dn Efrem eshete as much as you have the knowledge
    Msy God bless you all and eotc

    ReplyDelete
  21. ---‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡----
    «የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።» ዕብ ፲፫፡፯
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን። የአባታችን በረከታቸው ይደርብን።
    ዲ/ን አብርሃም ጤናው--ጎንደር

    ReplyDelete
    Replies
    1. የእግዚአብሄርን ቃል የተናገሯችሁን አስቡ ፡፡ ቃለሕይወት ያሰማልን የአባታችን በረከታቸው የደርብን፡፡

      Delete
  22. D.Melaku God bless you. Continue such education about ancient /kidusan/ fathers.

    ReplyDelete
  23. D.MELAKU EGZIABEHRE YESTELEN YAGELGELOT ZEMENEHEN YABZALEH EGNAM SEMTEN LEMETEKEM YABKAN

    ReplyDelete
  24. ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ::የተበተነውን የሚሰበስብ፡ የተራበውን የሚያበላ፡ የተጠማውን የሚያጠጣ፡ የጎበጠውን የሚያቀና፡የተበላሸውን የሚያሳምር፡የጠበበውን የሚያሰፋ ጊታ እየሱስ ክርስቶስ ለበተክርስትያናችን መልካሙን ገድል የሚጋደሉ አባቶች ያምጣላት።ለኛም ለምእመናት ተምረን ብሎም ሰምተን የምንድንበት ግዚ እሩቅ አይሁን:: አሚን::
    እግዚአብሒር ይባርክህ::

    ReplyDelete
    Replies
    1. Amen weamen leyikun leyikun ! Lewendimachin Dn Melaku Egziabher Amlak rejim edme ena tena endihum kef yale ewketun chemiro yistilin. Amen.

      Delete
  25. የአባታችን በረከታቸው ይደርብን።

    ReplyDelete
  26. በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡
    የሚለው አባባል እጅግ አንጀቴን አርሶታል፣....ቀላል ለቅሶ አለብኝ!
    እግዜር ይስጣችሁ

    ReplyDelete
  27. egzer tenawun yadilih. berta!

    ReplyDelete
  28. Yabatachn tselimu muse bereket yderbne. Kalehiwot yasemalen. Amen!!

    ReplyDelete
  29. kalehiwot yasemalen wondime!

    ReplyDelete
  30. qalehywet yasemaln !

    ReplyDelete
  31. kale hiyiwot yasemalin ke abatachin ke musie tselim bereket yasatifen

    ReplyDelete
  32. u are luck bro mechereshahin amlak yasamirilin ke abatachin bereket ayleyen

    ReplyDelete
  33. Amen, May the blessing and prayer of Abba. "Mussie Tselim" be with us all. And thank you for sharing it.
    But, I saw a story about Saint. Mosses, The Ethiopian, that's a bit different in the beginning. It says as a young man, Mosses committed a horrendous crime and flee to the desert, and he came across the Monastery. He saw how the monks live there and was fascinated by them, so he decided to stay with them and learn...
    This is a bit different, but nevertheless the story is the same.

    May the Blessing of Abba Mussie Tselim be with all of us!!!, Amen.

    ReplyDelete
  34. Amen, May the blessing and prayer of Abba. "Mussie Tselim" be with us all. And thank you for sharing it.
    But, I saw a story about Saint. Mosses, The Ethiopian, that's a bit different in the beginning. It says as a young man, Mosses committed a horrendous crime and flee to the desert, and he came across the Monastery. He saw how the monks live there and was fascinated by them, so he decided to stay with them and learn...
    This is a bit different, but nevertheless the story is the same.

    May the Blessing of Abba Mussie Tselim be with all of us!!!, Amen.

    ReplyDelete