Friday, July 15, 2011

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ


ትውልዱ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዘሩ ከዕብራውያን ከብንያም ነገድ ሲሆን የተወለደውም በጠርሴስ ከተማ ነው፡፡ድንኳን መስፋትን የተማረው በዚያ ነው። የሐዋ ፲፫፥፫ ጠርሴስ በንግድም የታወቀች የኪልቂያ ዋና ከተማ ናት፡፡ በከተማዋ እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚገመት ከየሀገሩ የተሰባሰቡ ሕዝቦች ነበሩባት፡፡ ሮማውያን በሥራቸው ለሚተዳደሩት ሕዝቦች ሮማዊ ዜግነት ይሰጡ ስለነበር የቅዱስ ጳውሎስ አባት በዜግነት ሮማዊ ነበር፡፡ ይህም ለቅዱስ ጳውሎስ ተላልፎለታል፡፡ አባቱ የሮም ዜግነት ይኑረው እንጂ፡- ከብንያም ወገን የሆነ ፈሪሳዊ ነበረ። የሐዋ ፳፫፥፮። በፊልጵስዩስ መልእክቱ፡- «በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁኝ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ፊል ፫፥፭። ከታላቁ መምህር ከገማልያል እግር ስር ሆኖ ሕገ ኦሪትን እና የአይሁድን ወግ ጠንቅቆ ተምሯል። የሐዋ ፳፪፥፫።

ቅዱስ ጳውሎስ በ15 ዓመት ዕድሜው ወደ ትውልድ ሀገሩ በመመለስ በኢየሩሳሌም ከነበረው የታወቀው የገማልያል ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በዚያም የአይሁድን ሕግና ሥርዓት እየተማረ እስከ 30 ዓመቱ ቆየ፡፡ ገማልያል ፈሪሳዊ ስለነበር ጳውሎስም ይህን ተቀብሎታል፡፡ በ30 ዓመቱ የአይሁድ ሸንጐ (ሳን ኽርይን) አካል ሆኖ ተቆጠረ፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ጥሪ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን ቅዱስ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ስለነበረ ሁኔታዎቹን ሁሉ ያውቃል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ አባልነት ለሁለት ዓመታት በሠራበት ወቅት ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ ፈሪሳዊ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማናቸውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር፡፡ እንዲያውም ሊቀዲያቆናት እስጢፋኖስ በማስተማሩ ምክንያት ተከሶ ለአይሁድ ሸንጎ በቀረበ ጊዜ የተከራከረው እርሱ ነበር፡፡ በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ሲያርፍም የወጋሪዎችን ልብስ ይጠብቅ የነበረው እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ ‹በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች፡፡› በማለት ተናግሯል፡፡
በ32 ዓመት ዕድሜው ከኢየሩሳሌም 223 ኪ.ሜ ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ሲሰማ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀርቦ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላ ጭፍሮችን አስከትሎ ወደ ደማስቆ አመራ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ከተማዋ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ነበር ከሰማይ የወረደው ብርሃን አካባቢውን ያለበሰውና ‹ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?› የሚለውን ድምፅ የሰማው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ‹ጌታ ሆይ ማን ነህ?› ብሎ ጠየቀ፡፡ ‹አንተ የምትሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስበኻል› ሲል መድኃኒታችን ተናገረው፡፡ ያን ጊዜም በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ ‹ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?› ሲል ጠየቀ፡፡ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባ ተነገረው፡፡ የሐዋ. 9.1፡፡
የሐዋርያው ዓይኖች ለማየት አይቻሉም፡፡ እየተመራ ወደ ደማስቆ ገባ፡፡ ለሦስት ቀናት ያህልም እህል ሳይቀምስ ቆየ፡፡ በዚያች ዕለት እግዚአብሔር አምላክ በደማስቆ ለሚገኘው እና ሐናንያ ለተባለው አባት በራእይ ተገለጠለት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ያለበትን አድራሻ ነገረውና ሄዶ እንዲያጠምቀው አዘዘው፡፡ ሐናንያ አስቀድሞ የቅዱስ ጳውሎስን ማንነት ያውቃል፡፡ አብዛኞቹ በደማስቆ የሚገኙት ክርስቲያኖች ከኢየሩሳሌም በስደት የመጡ ናቸው፡፡ ያን ስደት ያስነሣው ደግሞ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የደረሰው መከራ ነው፡፡ በዚህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ደግሞ ዋናው ተዋናይ ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር፡፡
ይህን የሚያውቀው ሐናንያ በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ጋር መከራከር ጀምሮ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አያውቀው ይመስል ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ማስረዳት ጀመረ፡፡ በመጨረሻ ግን ‹ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእሥራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና› በማለት እግዚአብሔር ሐናንያን ላከው፡፡
ሐናንያ ቅዱስ ጳውሎስን ካጠመቀውና ካስተማረውም በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዓረብ ሀገር መሄዱን ራሱ ተናግሮአል፡፡ ገላ 1.17፡፡
የስሙ ትርጓሜ
ቅዱስ ጳውሎስ የስሙ ትርጓሜ ብርሃን ማለት ነው፥ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ ሀገረ ገዥ የገዛ ስሙን ሰጥቶት ነው፥ የቀደመ ስሙ ሳውል ነበር። ይህ ሀገረ ገዥ አስተዋይ ሰው ስለነበር፡- የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ወድዶ፥ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ አስጠራቸው። ኤልማስ የተባለው ጠንቋይ ግን አገረ ገዥውን ከማመን ለማጣመም ፈልጐ ተቃወማቸው። ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስ ባደረበት ሰውነት ሆኖ፡- «አንተ ተንኰል ሁሉ፥ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታ መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? እነሆ የጌታ እጅ (ሥልጣን) በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ፥ እስከጊዜውም ፀሐይን አታይም፤» አለው። ያንጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዥው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።  የጠንቋዩን ዓይነ ሥጋ በተአምራት ሲያጠፋበት፥ የእርሱን ደግሞ ዓይነ ኅሊናውን ሲያበራለት አይቶ ጳውሎስ (ብርሃን) የሚለው ስም ለአንተ ይገባሃል አለው። የሐዋ ፲፫፥፮።
          ጳውሎስ ማለት ንዋይ ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ) ማለትም ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጳውሎስ ለሐናንያ በመሰከረለት ጊዜ፡- «ይህ በአሕዛብም፥ በነገሥታትም፥ በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤» ብሎታል። የሐዋ ፱፥፲፭። ምርጥ ዕቃ የተባለው መዶሻ ነው። እርሱም ሰባት የማዕድን አይነቶችን ቀጥቅጦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስም እግዚአብሔርን እና ሰውን፥ሰውን እና መላእክትን፥ ሕዝብን እና አሕዛብን፥ ነፍስን እና ሥጋን አስታርቆ አንድ ያደርጋል። አንድም ምርጥ ዕቃ የተባሉ ወርቅና ብር ናቸው። ወርቅና ብር ለንዋያት ሁሉ ጌጥ እንደሆኑ፡- እርሱም የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ነው። አንድም፡- ጳውሎስ ማለት፡- አመስጋኝ፥ ደስታ፥ ምዑዝ ነገር የሚናገር፥ ልሳነ ክርስቶስ፥ ሰላም፥ ፍቅር ማለት ነው።
ከተመለሰ በኋላ
ለ3 ዓመታት በዓረቢያ በረሃ ከቆየ በኋላ ወደ ደማስቆ ከተማ ተመለሰ፡፡ በዚያም በነበሩ አይሁድ መካከል በፊት ያሳድደው የነበረውነን ኢየሱስ ክርስቶስን መስበክ ጀመረ፡፡ ከዚያ በፊት በፈሪሳዊነቱ ለአይሁድ ሕግ በነበረው ቅንዓት የሚታወቀው ጳውሎስ ዛሬ ወንጌል ሲሰብክ በማየታቸው አይሁድ ተነሡበት፡፡ በዚህም የተነሣ የደማስቆ ክርስቲያኖች በቅርጫት አውርደው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የገጠመው ሁለት ችግር ነበር፡፡
1-       አይሁድ ጳውሎስን እንደሚያውቁት እና እንደለመዱት ሆኖ ስላላገኙት ሊገድሉት ተነሡ፡፡
2-     ክርስቲያኖች የቅዱስ ጳውሎስን መመለስ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ ግን በርናባስ ወደ ሐዋርያት ዘንድ ወስዶ የጳውሎስን መመለስ በመተረክ እንዲያምኑት አደረጋቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ በኢየሩሳሌም በድፍረት በማስተማሩ አይሁድ ስለተቃወሙት ከተማዋን ትቶ በቂሳርያ በኩል ወደ ትውልድ ሀገሩ ጠርሴስ ተመለሰ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ ከተማ ለዘጠኝ ዓመታት ቆይቷል፡፡ ከኢየሩሳሌም ውጭ የአሕዛብ ከተማ በነበረችው በአንጾኪያ የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፋ፡፡ ከኢየሩሳሌም የተሰደዱት ክርስቲያኖች የአንጾኪያን ሕዝብ ተግተው በማስተማራቸው ዝናው እስከ ኢየሩሳሌም ደረሰ፡፡ በዚህም ምክንያት በኢየሩሳሌም የነበሩት አበው በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላኩት፡፡ በርናባስ የግሪክ ቋንቋ ችሎታ ያለውን፣ ከማንኛውም ሰው ጋር መግባባት የሚችለውን፣ ደግሞም እግዚአብሔር ለአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠውን ቅዱስ ጳውሎስን ከጠርሴስ በማምጣት በአንጾኪያ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡
በገላትያ መልእክቱ ምዕራፍ 2 ላይ ራሱ እንደገለጠው ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ከአንጾኪያ ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ርዳታ ይዞ ወጣ፡፡ በዚህም በአይሁድ በአሕዛብ መካከል የነበረውን መለያየት ክርስትና አንድ እንዳደረገው አስመስክሮአል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ 4 ሐዋርያዊ ጉዞዎች... !ይቆየን
 የአባታችን የቅዱስ  ጳውሎስ ጸሎትና በረከ በሁላችን ይደርብን አሜን         

ዋቢ፡-
·        መጽሐፍ ቅዱስ
·        ዜና ሐዋርያት
·        ቤተክርስቲያንህን ዕወቅ
·         ትንሳኤ መጽሔት

20 comments:

  1. አሜን!!! ቃለህይወት ያሰማልን እረጅም የአገልግሎት ዘመን ይስጥልን፡፡

    ReplyDelete
  2. Amen! qale hiwoten yasemalen

    ReplyDelete
  3. +++

    Amen Qale Hiwoten Yasemalen. Qedusan Sealatu Gen Ye Betkirstiyanachin Bihonu Yemertale. Enzihe Yegna Ayedelumena.

    WeletGiyorgis
    Ke Germany

    ReplyDelete
  4. .....Waiting for the next part

    ReplyDelete
  5. selam melaku kenebabu
    behala teyake benore
    lemanebebe yegefafale
    ena asebebet.

    ReplyDelete
  6. አቤት እንዴት ደስ ይላል!!! ቅዱስ አውግስጢኖስ ‹በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች› በማለት ተናግሯል ….. ማነው ቅዱስ አውግስጢኖስ ማነውስ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወዘተ እያልን እንድንጠይቅና ስለነሱም ታሪክ እንድናውቅ፣ ከእነሱም እንድንማር ይገፋፋናልና … ግሩም አቀራረብ ነው። ቀጣዩን ክፍል በጉጉት ከሚጠብቁት ነኝ። በርታ!!!

    ReplyDelete
  7. go melaku go!!!!!

    ReplyDelete
  8. It is very nice.your side makes me confident person.please try a lot.i pray GOD helps you.(..... Habtamu Nigussie from Abnet.

    ReplyDelete
  9. ቅዱስ አውግስጢኖስ ‹በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች፡፡›

    አምላከ ቅዱሳን እኛንም ከጥፋት ይመልሰን ፡፡ አሜን !!!!!!!

    ReplyDelete
  10. God bless you............berather

    ReplyDelete
  11. hey bra keep through

    ReplyDelete
  12. keep through ma dear beloved bra

    ReplyDelete
  13. Egziabher yabertalin! Kale hiwot yasemalign! Amen....looking for more 2 come

    ReplyDelete
  14. then speak the lord to paulin the night by a vision be not afaird but speak and hold not thy peace.
    fori am with thee and no man shall set on thee to hurt for i have much people in this city.
    ARC 18;9-10
    KALLE HIWET YASEMALIN AGELIGLOTHN YIBARKILH

    ReplyDelete
  15. kale hiwet yasemalen

    ReplyDelete
  16. tebarek. bereketu yiderbin!!

    ReplyDelete
  17. +++ kale hiwtoe yasemalen! menegestune yaweresulen Egeziabehre Amen

    ReplyDelete
  18. አሜን!!! ቃለህይወት ያሰማልን እረጅም የአገልግሎት ዘመን ይስጥልን፡፡

    ReplyDelete
  19. ‹ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእሥራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና› በማለት እግዚአብሔር ሐናንያን ላከው፡፡

    ቃለህይወት ያሰማልን!

    ReplyDelete