Thursday, October 4, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 1

የጾም ትርጓሜ
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ - ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ አንድም ጾም ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ይህም ኃጢአቱን ለማስተሰረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥራም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ፍት.ነገ.ፍት. መ. አንቀጽ 15564፡፡ በዚህ መሠረት ጾም ማለት ከጥሉላተ መባልዕት /ሥጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል እንዲሁም የአልኮል መጠጦች/ መታቀብ ነው፡፡
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለፈቃደ ሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ ሰው ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት ስንቅ ነው፡፡ ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣ የጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው፣ የጸሎት ምክንያት /እናት/፣ የእንባ መገኛ ምንጭ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡ /ማር. ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/፡፡

የጾም ዓይነቶች
ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንረዳው ጾም በዓይነቱ በሁለት ሊከፈል ይችላል፡- የዐዋጅና የግል፡፡ የዐዋጅ ጾም በይፋ ለሕዝቡ ተነግሮ በአንድነት የሚጾም የትዕዛዝና የሕግ ጾም ነው፡፡ በ “በጽዮን መለከትን ንፉ፣ ጾምን ዐውጁ ጉባኤውንም ቀድሱ” /ኢዩ. 11214/፡፡ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ወቅታቸው /ወራቸውና ቀናቸው/ በየዓመቱ የሚታወቁ የዐዋጅ ወይም የሕግ አጽዋማት ነበሩ፡፡ አሉም፡፡ በብሉይ ኪዳን “ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- የአራተኛው ወር ጾም፣ የአምስተኛውም፣ የሰባተኛውም፣ የዐሥረኛውም፣ የሰባተኛውም፣ የዐሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሴትም በዓላት ይሆናል፡፡”  /ት .ዘካ. 8፣18፡19/
በሐዲስ ኪዳንም ፈሪሳውያን ከሳምንቱ ቀናት ውስጥ ሁለቱን /ሰኞንና ሐሙስን/ ወስነው እንደሚጾሙ  “ አንሰ እጸውም ሰኑየ መዋዕለ በኩሉ ሰናብት፣ እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማሁ” /ሉቃ. 18፣12/ የሚል አስረጅ ይገኛል፡፡ በግብረ ሐዋርያት መጽሐፉ ቅዱስ ሉቃስ ስለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጉዞ ሲጽፍ   “ብዙም ጊዜ ካለፈ በኋላ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበር” በማለት ያሰፈረው ቃል በዘመነ ሐዋርያት የተወሰነ የጾም ጊዜ መኖሩን ያረጋግጥልናል፡፡ / ግብ.ሐዋ. 279131-3፡፡
በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሁሉ እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ፣ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የዐዋጅ /የሕግ/ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህም ዐቢይ ጾም /ጾመ ዐርባ/፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ፍልሰታ /ጾመ ማርያም/፣ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/፣ ዶመ ድራረ ጥምቀት /ገሃድ ወይም ጋድ/፣ ጾመ ሰብአነነዌ፣ ጾመ ድኅነት /የረቡዕና ዓርብ ጾም ናቸው ፡፡
እንዲህ ወራት ተወስኖለት በቁጥር የተወሰነ በጊዜ የተገደበ ይሁን እንጂ የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ የሚረዳን የጽድቅ መሠረት፣ የገነት በር በአጠቃላይ የክርስቲያች ኑሮ ስለሆነ ከተዘረዘሩት የሕግ አጽዋማት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚጾሙ በገዳም፣ በበረሃ ያሉ መነኮሳትና ባሕታውያን አሉ፡፡ “ስለ ጽድቅ የሚራቡ፣ የሚጠሙም ብፁዓን ናቸው፣ እነርሱ ይፀግባሉና፡፡” /ማቴ. 56፤ ኢሳ 4117፣ 551/፡፡
አበው  “ቢቻላችሁስ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ፣ ለድኾችም ምጽዋት ስጡ” /ፍትሐ ነገስት .ፍ.መ. 15580/ በማለት እንዳዘዙት ጾምን ቢያዘወትሩ ለስርየተ አበሳ፣ ሥጋን ለመጎሰምና ለነፍስ ተግባር ለማሠልጠን ይመቻል፡፡  “ ሰው ይረባኛል ይመቅመኛል ብሎ አብዝቶ ከመጾሙ የተነሣ አንጦንስን መቃርስን እንዲሁም መላእክትን ይመስላል” ሲሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡
ይህም ወደ ሁለተኛው የጾም ዓይነት ማለት ወደ የግል ጾም ይወስደናል፡፡ የግል ጾም እግዚአብሔር ኃይሉንና ብርታቱን የሰጣቸው ምእመናን በግል /በስውር/ የሚጾሙት ነው፡፡ አንድ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር የሚፈልገው ነገር ሲኖር፣ ራሱን ለመግዛት ይችል ዘንድ እንዲሁም ንስሐ ገብቶ የንስሐ አባቱ ሲያዝለት በግሉ ይጾማል፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ የነበረ ሥርዓት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሊቀ ነቢያት ሙሴን /ዘጸ.24፣18/፣ ነቢዩ ዳንኤል /ት.ዳን. 9፣3/፣ ነህምያን / ነህ.9፣1-4/ በሐዲስ ኪዳንም ቅዱስ ጳውሎስንና ቅዱስ ጴጥሮስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ /ግብ.ሐዋ.10፣10፣ 2 ቆሮ. 6፣5፣11፣27/፡፡ የግል ጾም ከዐዋጅ ጾም ጋር አንድ መሆን አይገባውም፡፡ የግል ጾም የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡
የንስሐ ጾም ምእመናን ከመምህረ ንስሐቸው ጋር ተመካክረው ንስሐ ገብተው በአንቀጸ ንስሐ መሠረት ቀኖና ሲሰጣቸው የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ቀኖናውን የሚፈጽሙት ማንም ሳያውቅባቸው በስውር ይሆናል፡፡ አንዳንዶች በንስሐ አባቱ የታዘዘ ምእመን ሕጋዊ መመሪያ ተቀብሎ ስለሚጾም ራሱን መደበቅ አያስፈልገውም ቢሉም ጸዋሚው መጾሙን ምናልባት ከቅርብ ቤተሰቦቹ ውጭ ሌላ ሰው አያውቅበትም፣ ማሳወቅም የለበትም፣ ተሰውሮ ይጨርሰዋል እንጂ፡፡ በንስሐ አባቱ የተሰጠውን ቀኖና እስኪፈጽም ፈጣሪው የቀደመ ኃጢአቱን ይቅር እንዲለው ሥርየት እንዲሰጠው በእንባ ይማፀናል፡፡ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ መዝ.61-10፡፡ የግል ጾም በተለያዩ ምክንያት ( ለምሳሌ በወሊድ ፤ በሕመም ወዘተ) የአዋጅ አጽዋማትን መጾም ላልቻሉ በአዋጅ አጽዋማት ፈንታ በንስሐ አባት የሚሰጥ ትእዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የንስሐ ጾም የብይን ጾም ይባላል፡፡
የፈቃድ ጾም በሌላ አጠራር የትሩፋት ጾም  በመባል ይታወቃል፡፡ በዝግ ወይም በማኅበር ሊፈጸም ይችላል፡፡ እግዚአብሔርን በትጋት የሚያገለግሉ ምእመናን በግል ወይም በማኅበር፣ በገዳም የሚኖሩ አባቶች በአንድነት ስለሚከተሉት ምክንያቶችና ስለ መሰሏቸውም የፈቃደ ጾም ይጾማል፡፡
Ø በግልና በቤተሰባዊ ሕይወታሕይወታቸው የገጠማቸው ችግር ካለ እንዲወገድላቸው፣ በሚኖሩባት አገርና በቤተክርስቲያናቸው ዙሪያ ያላቸው እክል እንዲርቅላቸው፣
Ø ክቡር ዳዊት “ነፍሴን በጾም አስመረርካት” እንዳለ ራሳቸውን መግዛት ይችሉ ዘንድ ነፍስን በሥጋ ላይ ለማሠልጠን
Ø በጥቂት ሲለምኑት አብዝቶ የሚሰጥ እግዚአብሔር ምሥጢር እንዲገልጥላቸው /ዳን. 10፣14/
Ø የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ የቅዱሳንን መከራ እያሰቡ በረከታቸውን ለመሳተፍ፣ ከኃጢአት ለመንጻት የሚሉት ናቸው፡፡
የፈቃድ ጾም ቅድመ ዝግጅት
በስውር ለመጾም የሚያስብ ሰው ሊያደርገው የሚገባው ቅድመ ዝግጅት አለ፡፡ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ቢጀምረው ግን በመሐል አቋርጦ ሊተወው ይችላል ወይም ያሰበውን ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ዝግጅቱ በብዙ መልኩ ነው፣ ለአብነት ያህል፡-
·        ከንስሐ አባት ጋረ መመካከር ይገባል፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር የሚመራ በምክረ ካህን የሚኖርና የሚጓዝ ሰው ፈተና ቢገጥመው መከራ ቢደራረብበት እንዴት ማለፍ እንዳለበት ስለሚያውቅ አይረበሽም፣ ይታገሣል እንጂ፡፡ ስለዚህ በግሉ ጾም ለመያዝ የሚያስብ መጀመሪያ ከንስሐ አባቱ ጋር ቢነጋገር እጅግ የተሻለ ነው፡፡ አባቱ በጾሙ ወቅት እንዲያስቡት እንዲጸልዩለት ቢያደርግ ፈተናውን ተቋቁሞ ጾሙን መጨረስ ይችላል፡፡
·        ጸዋሚው ለንስሐ አባቱ እንዲሁም ግድ ማወቅ ላለባቸው ቤተሰዎች ብቻ ካልሆነ ላገኘው ሰው ሁሉ ሱባኤ ልጀምር ስለሆነ አትርሱኝ እያለ መንገርና ጾሙን ማወጅ የለበትም፡፡ ውዳሴ ከንቱ ሊያመጣበት ይችላልና፣ ለሰው ሁሉ ሲነግር የሰማ ጠላት ዲያብሎስም እንቅፋት ያበዛበታል ፈተና ያከብድበታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ይህን በተመለከተ ሲናገር  “. . .  ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፣ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል፡፡” ብሏል፡፡ ማቴ 6፡18፡፡ ስለዚህ በግሉ የሚጾም ሰው ለማንም ሳይነግር /ሳያውጅ/ መጾም ይገባዋል፡፡ ቆሎ ዘግኖ ወይም በሶ ብቻ በመብላት መጾሙን፣ አብዝቶ መስገድ መጸለዩን መናገር የለበትም፡፡ ቢናገር ግን ድካሙን ሁሉ ከንቱ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ በምድር ያገኘው የሰዎች ወዳሴ እግዚአብሔር ያዘጋጀትን ጸጋና ረድኤት ያስቀርበታልና፡፡
·        በፈቃዱ ሱባኤ መያዝ /መጾምና መጸለይ/ የሚፈልግ ሰው ዐቅሙን የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ የጾሙን ጊዜ መወሰን ያለበት ያለውን ጥንካሬ፣ ልምዱንና ጽናቱን ገምግሞ ሊሆን ይገባል፡፡ ጀማሪ ክርስቲያን  “በዋሻ ዘግቼ በቀን አንድ ጊዜ ጥሬ ቆርጥሜ መቶ ሃምሳ መዝሙረ ደግሜ” እጾማለሁ ቢል ከዐቅሙ በላይ ሆኖበት፣ ጥብዓት ጎድሎት፣ ትዕግሥት አንሶት ሊያቋርጠው ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደ ዐቅሙ መጾም መጸለይ ይገባዋል፡፡
·        ጸዋሚው የታወቀ ዓላማ ሊኖረው በሚያሳልፋቸው የጾም ዕለታት እግዚአብሔር አምላኩ እንዲያደርግለት የሚጠይቀውን ጥያቄ ጠንቅቆ ማወቅና ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ ብዙ መነኮሳት፣ ባሕታውያንና ምእመናን በፈቃድ የሚጾሟቸው የታወቁ ጊዜያት አሉ፡፡ እኒህም የጽጌ ጾም /ጾመ ጽጌ/ ና በጳጉሜን ወር የሚጾመው “ጾመ ዮዲት” ናቸው፡፡
ሀ/   “ጾመ ጽጌ”
ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ያለው አንድ ወር ከዐሥር ቀን ወይም 40 ቀን ወርኃ ጽጌ፣ ዘመነ ጸጌ፣ ተብሎ ይጠራል፡፡ በነዚህም ቀናት በየቤተክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩት መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቆመው ማኅሌት በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐት እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋክብት ምድር በጽጌያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡
ወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሰዊ አገልግሎት መነሻው    “መልአኩ ሕፃኑንና እናቱን ወደ ግብፅ ይዘሃቸው ሽሽ፣ የሕፃኑን ነፍስ ሊገድሉት ይፈልጋሉና” ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሠረተ ዮሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ /ራእይ.12፣6/ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው፡፡ /ማቴ. 213-23፣ ት.ኢሳ.191፣ እንባቆም 36-7፣ መዝ.833/፡፡
ይህንንም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ አባ ጽጌ ብርሃን ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመለሰ በሚያስረዳው ድርሰታቸው እንዲህ በማለት ገልጸውለታል፡፡  “ አፈወ ሮማን ማርያም ጽጌ ቀናንሞ ወአበሜ፣ እስከ ተጸምሐየየ በጾም ዘመልክዕኪ ጊዜ ድክታሜ፣ እምተመነይኩ ተሳትፎ ከመ አኅትኪ ሰሎሜ፣ ወፍሥሓኪ ዘአልቦ ፍጻሜ”፡፡ ሲተረጎምም የሮማን ሽቱ የቀናንሞ አበባ የምትሆኚ ማርያም ሆይ፣ በርሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪጠወልግ ድረስ በስደትና በልቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሰሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህ ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር፡፡
እንዲሁም አባ አርክ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን ፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት   ‘ሰቆቃወ ድንግል” በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፣ ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሸሽ ጊዜ የደረሰብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንደ ጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር”፡፡ ይቀጥላል - ይቆየን !
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያሳትፈን

10 comments:

 1. Amen!!! Egziabher yitebikih! Kale Hiwot yasemalin! Betam yemiasdest yemiaregaga birtat yemihon melikt new! Tibebun ena mastewalun yabzalih!!!

  ReplyDelete
 2. አሜን!!! ቃለ ህይወት ያስማልን!!! በርታ ዲን መላኩ ክፍል ሁለትን በናፍቆት እጠብቃለሁ፡፡

  ReplyDelete
 3. kalehiywot yasemalin!

  ReplyDelete
 4. kale hiwet yasemalin Diakon ..dink xihuf new

  ReplyDelete
 5. Kalehiwet yasemalein

  ReplyDelete
 6. አሜን!!! ቃለ ህይወት ያስማልን!!! በርታ ዲን መላኩ ክፍል ሁለትን በናፍቆት እጠብቃለሁ፡፡

  ReplyDelete
 7. ሰቆቃወ ድንግልን ማን እንደደረሰው አስቤም አላውቅም ነበር ተባረክ ፣ አርከ ስሉስ ነው? ወይስ አርክ ስሉስ ግን?
  መልእክቶችህ ሁሉ ያስደስቱኛል ጽናዕ ወተዓገስ፣
  በረከተ እስጢፋኖስ ይህድር በላዕሌከ

  ReplyDelete
 8. አሜን!!! ቃለ ህይወት ያስማልን!!! በርታ ዲን መላኩ ክፍል ሁለትን በናፍቆት እጠብቃለሁ፡፡
  Reply

  ReplyDelete