Thursday, May 10, 2012

የቅዱሳን መሰወር (ኅብአተ ቅዱሳን) -ክፍል 2ነቢዩ ኤልያስ
፬. ብሔረ ብፁዓን

ከኻያው ዓለማት ውስጥ የኾነች /ከመሬት ወገን የምትመደብ/ ስውር ምድር ብሔረ ብፁዓን ናት። እንደ ገድለ ዞሲማስ አገላለጽና ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት፥ በዚህች ቦታ ተሰውረው የሚኖሩ ሰዎች ራሳቸውን ለፈቃደ እግዚአብሔር ያስገዙ ናቸው። በውስጧም ቅዱስ ጋብቻን መፈጸም የሚችሉና ዘርን ለማሰቀረትና ለመተካት ልጅን መውለድ ይችላሉ። ለኃጥአን ያልተፈቀደች የማትገባም ቦታ ናት።

፭. ደብር ቅዱስ

ከምድር ወገን ሆና የተለየች ሥፍራ ናት። አዳም በበደለና ከገነት በወጣ ጊዜ ገነትን በማየት ይጸጸት ዘንድ በዚህች ሥፍራ አኑሮታል። መጽሐፍ ቅዱስ /ብሉይ ኪዳን/ ይህችን ቦታ «ደብር ቀዱስ፣ ከፍ የለች ሥፍራ» በማለት ይጠራታል። /ሄኖክ ፬፥፸፩/። አዳም ከአቤል ሞት በኋላ የተወለደለት ሴት ከነልጆቹ ይኖር እንደ ነበርና በኋላም በኖኅ ዘመን የቃየንን ሴቶች ልጆች በማየት ስተው መውረዳቸውን በዘፍጥረት ትርጓሜ እንረዳለን። «የእግዚአብሔር ልጆችም /በደብር ቅዱስ የሚኖሩ የሴት ልጆች/ የሰውን ሴት ልጆች /የቃየንን ልጆች/ መልካሞች እንደሆኑ አዩ፤ ከመረጧቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።» /ዘፍ. ፮፥፪/ ይላል።

እነዚህ የቃየንን ሴቶች ልጆች በኃጢአት ተመኝተው ቅዱስ ሥፍራቸውን ጥለው በመውረድ የወለዷቸው ልጆች ኃያላን ነፍስ ገዳዮች፥ ለእግዚአብሔር የማይታዘዙ ሆኑ። እግዚአብሔር ምድርን በእነርሱ ምክንያት አጠፋት።
ጻድቁ ሄኖክም ስለ እነርሱ መሳትና ስለ ደብር ቅዱስ ቅድስና እንዲህ ይላል «ከፍ ያለ ደብር ቅዱስን ዘላዓለም ጸንቶ የሚኖር መንግሥተ ሰማያትን ስለምን ተዋችሁት» /ሄኖክ ፬፥፳፩/፤ «ቀድሞ የንጽሕና መሠረት የነበሩ እነዚህም በዚህ ዓለም ክፉ ልጆች ይሆናሉ። ክፉ ልጆች ይባላሉ» /ሄኖክ ፬፥፹፫/ ብሏቸዋል። በተጨማሪም መልካም ሥራን በመልካም ቦታ እንዲሁም ጸሎትን መጸለይ የተዉትን የሴት ልጆች እንዲህ ይላቸዋል «እናንተ ለሰው ልተለምኑ ይገባችሁ ነበር። ሰው ግን ለእናንተ ሊለምንላችሁ አይገባችሁም ነበር» በማለት የሴት ልጆች ሳይስቱ በደብር ቅዱስ ቢቆዩ ኖሮ ለሰው ልጆች እየጸለዩ እነደሚኖሩ ገልጿል። ነቢዩ ሄኖክ በብሔረ ብፁዓን ይኖሩ የነበሩትን ከብሔረ ሕያዋን ሄዶ የነገራቸው፥ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚራራ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ጥፋት አይወድምና የሴት ልጆች ከነበሩበት ቦታ የሚያስወጣ ምኞት ተጸናውቷቸው በነበረ ጊዜ ምን አልባት ይመለሱ እንደሆን ያሰተምራቸውና ይመክራቸው ዘንድ ነው ። እግዚአብሔር ትእዛዙን ለነቢዩ ሄኖክ የገለጸለት በቅዱሳን መላእክት በኩል ነበር። /ሄኖክ ፬፥፮-፯፣፳፮/።

፮. ብሔረ ሕያዋን 

በዚህ ቦታ የሚኖሩ ቅዱሳን ሰዎች በዘመናቸው መልካም ሥራን በማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ሰዎች ናቸው። ከእነዚህም በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚታወቁት መካከል ዋነኛዎቹ ነቢዩ ሄኖክና ነቢዩ ኤልያስ ናቸው። ስለነቢዩ ሄኖክ በመጽሐፈ ሲራክ ላይ «ሄኖክ እግዚአበሔርን ደስ አሰኘው፤ እግዚአብሔርም እርሱን ከሞት ሰወረው፤ ንስሃ ለሚገቡ ሰዎች አብነት ሆነ» ተብሏል /ሲራክ ፵፬፥፲፮/። በተሰወረ ጊዜም ከሰው ልጆች ያወቀ የለም። እርሱም በብሔረ ሕያዋን ለመግባት የመጀመሪያው ሰው ነበር። መጽሐፍ «ከነገር ሁሉ አስቀድሞ ሄኖክ ተሰወረ፤ ከሰውም ልጆች በተሰወረበት ቦታ ሳለ የሚያውቀው አልነበረም። ይሙት ይዳንም የሚያውቅ የለም» /ሄኖክ ፬፥፩-፪/ እንዲል /ዕብ. ፲፩፥፭-፮፤ ዘፍ. ፭፥፳፪-፳፬/።

ነቢዩ ሄኖክ ከመሰወሩ በፊት በአኗኗሩ እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሰማያት ምሥጢር የተገለጡለት ከእግዚአብሔር የተማረ ነበር። በመጽሐፈ ኩፋሌ «ስሙን ሄኖክ አሉት፤ እርሱ አስቀድሞ በዚህ ዓለም ከተፈጠሩ ሰዎች ይልቅ መጻሕፍትንና ትምህርትን ጥበብንም ተማረ፤ የዘመኑን ጊዜ ያውቅ ዘንድ እንደወራቸው ሥርዓት የሰማይን ምልክት በመጽሐፍ ጻፈ።» /ኩፋሌ ፭፥፳፪-፳፫፤ ይሁዳ ፲፬-፲፭/ በማለት ይገልጸዋል።

በተጨማሪም ቅዱስን መላእክት የሰማይን ምሥጢር እያስጎበኙ ገልጠውለታል። እርሱም ከምድር ወደ ሰማይ በመነጠቅ በተመሥጦ ተረድቶታል። «ከነዚያ ወራት በኋላ በነፋስ ሰረገላ ተነጥቄ ነበርና፥ መላእክትም ወደ ምዕራብ ወስደውኝ ነበርና፥ በዚያ ቦታ የተሰወሩትን ራዕዮች አየሁ» /ሄኖክ ፲፬፥፩/ በማለት ይገልጾዋል።
ነቢዩ ኤልያስም ከደቀ መዝሙሩ ነብዩ ኤልሳዕ ጋር ሳለ እግዚአብሔር በእሳት ሰረገላ ወስዶታል። ከመወሰዱ በፊት ሙት በማንሣት፣ ሰማይ ዝናም እንዳይሰጥ በመለጐም እንደገናም ዝናምን በጸሎቱ በማዝነብ ወዘተ ተአምራት በማድረግ ለአምላኩ ቀናዒ መሆኑ ተመስክሮለታል። /፩ኛ ነገ. ፲፰፥፲፮-፵፮፤ ፪ኛ ነገ. ፪/። ከእርሱ ቀድሞ የተሰወረ ጻድቁ ሄኖክ ስለ ኤልያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል ገልጿል «የእስራኤል ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤልን ጸባዖት ነቢያት ጠርቶ አስተምሩ ብሎ ላካቸው፤ እስራኤል ይገድሏቸው ጀመር። ከነቢያት አንዱ ኤልያስ ከሞት ዳነ፤ ሞት አላገኘውም፤ ፈጥኖ ሄደ፤ በእስራኤል ከተማ አስተማረ። እስራኤል ሊገድሉት ወደዱ። የእስራኤል ገዥ እግዚአብሔር ከእስራኤል እጅ አዳነው ። ወደ እኔም አምጥቶ አኖረው።» ይላል።

እንግዲህ በብሔረ ሕያዋን የሚኖሩ በብሉይ ኪዳን እንደነነቢዩ ሄኖክና ነቢዩ ኤልያስ ያሉት ናቸው። በሐዲስ ኪዳንም በወንጌሉ የተነገረላቸውና ከእነርሱም በኋላ ብዙ ቅዱሳን እንዳሉ መጻሕፍት ያስረዱናል። ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ወንጌላዌው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌላቱ ገጸ ንባብ ስሙ ሳይጠቀስ በምልክት፥ በትርጓሜ ወንጌል ላይ ደግሞ በስሙ ተጠቅሶ ወደ ስውራኑ መኖሪያ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደተነጠቀ ይገልጽልናል። ለዚህም ቅዱስ ሉቃስ «እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ» /ሉቃ. ፱፥፳፯/ በማለት ሲጠቅስ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ስለራሱ «ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱ ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ «ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?» ያለው ነበር። ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን «ጌታ ሆይ ይህስ እንዴት ይሆናል?» አለው። ኢየሱስም «እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ» አለው። ስለዚህ ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ «እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?» አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።» /ዮሐ. ፳፩፥፳-፳፫/ በማለት ይገልጻል። በትርጓሜውም፣ በገድሉም፣ በስንክሳሩም ይህን መነሻ አድርገን ቅዱስ ዮሐንስ ከእነሄኖክና ኤልያስ ጋር በብሔረ ሕያዋን እንደሚኖር እናረጋግጣለን።
እነዚህ በብሔረ ሕያዋን ተሰውረው የሚኖሩ ቅዱሳን በአንዳንዶች ዘንድ «እዚያ ምን ይሠራሉ?» የሚል ጥያቄ ሊያሥነሳ ይችላል። በመጽሐፈ ሄኖክ ከመላእክት ጋር በቅዳሴ እንደሚያመሰግኑ እንደሚከተለው ተገልጿል። «ሥራውም ሁሉ በተሰወረበት ወራት በቅዳሴያቸው ከሚተጉ ቅዱሳን መላእክት ጋርና ከቅዱሳኑ ጋር ነበር።» በተጨማሪም «እኔም ሄኖክ ገናና ጌታን በአራቱ ማዕዝነ ዓለም የነገሠ እግዚአብሔርን አመሰግነው ጀመር» /ሄኖክ ፬፥፴፬/ በማለት ከተግባሩ አንዱ ምስጋና እንደሆነ ይገልጽልናል። እንዲሁም ቅዱሳኑ ከመላእክት ጋር ስለሰዎች ልጆች ድኅነት እንደሚነጋገሩና ነቢዩ ሄኖክ ወደ ደብር ቅዱስ ይሄድ ዘንድ በመላእክት እንደተነገረው እርሱ ከጻፈው መጽሐፍ እንረዳለን። «…ለቅዳሴያቸው የሚተጉ መላእክት እነሆ ይጠሩኛል። ...ለኃጢአት ለሚተጉ ሰማያዊ መዓርጋቸውን መንግሥተ ሰማያትን አጥተው ከሴቶችም ጋር ለጠፉ የቃየል ልጆችም እንደሚያደርጉ ላደረጉ ለደቂቀ ሴት ሄደህ ንገር አለኝ...» /ሄኖክ ፬፥፮-፯/ በማለት ቅዱሳን መላእክት ወደ ብሔረ ሕያዋን በመምጣት ሄኖክ ወደ ደቂቀ ሴት ከጥፋታቸው እነዲመለሱ እነዲነግራቸው ከእግዚአብሔር ተልከው ነግረውታል። እርሱም የተላከውን መልእክት ሊያስተላልፍ ወደ ደቂቀ ሴት እንደ ሄደና እንደነገራቸው «እውነት ነገር ያለበት ይህን ቃል እናገር ዘንድ በደብር ቅዱስም ለነበሩ በኃጢአታቸው ለሚተጉ ለደቂቀ ሴትም አስተምር ዘንድ ጀመርሁ» /ሄኖክ ፬፥፳፮/ በማለት በዚያም ያለውን የቃለ እግዚአብሔር የማስተማር ተልእኮውን ይገልጽልናል።

በአጠቃላይ በብሔረ ሕያዋን ምስጋና፣ ቅዳሴ፣ ቃለ እግዚአብሔርን መነጋገር፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር መነጋገር፣ መጸለይ፣ ስለሰው ልጆች ድኅነት ማሰብ ወዘተ እንዳለ እንረዳለን።

በተጨማሪም በብሔረ ሕያዋን በሚኖሩ ቅዱሳን መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ግርማ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር እንደተገለጠ ከወንጌሉ እንረዳለን። /ሉቃ. ፱፥፳፰-፴፮፤ ማቴ. ፲፯፥፩-፰፤ ማር. ፱፥፪-፰/። ይህም በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነቢዩ ኤልያስ በሥጋው እንዳረገ ስለሚያውቁ ከጌታችን ወደዚህ መምጣት ጋር ተጋጭቶባቸው የጌታችንን አምላክነት እንዳይክዱ ለሐዋርያቱ ከነቢያት አንዱ ኤልያስን ከመሰወሪያው ከብሔረ ሕያዋን በማምጣት እንዲያዩት አድርጓቸዋል። ይህንንም በማየት ቅዱስ ጴጥሮስ «እኔ ማነኝ?» ለሚለው ጥያቄ ጌታችን አምላክ እንጂ ነቢዩ ኤልያስ እንዳልሆነ «አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ» በማለት አረጋጧዋል።


ስውራን ቅዱሳን /ኅቡአን ቅዱሳን/ በፍጻሜ ዘመን ወዳለንበት ምድር መጥተው እንደሚገለጡና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መስክረው በአውሬው /ሐሳዌ መሲሕ/ ሰማዕትነትን እንደሚቀበሉ መጻሕፍት ያስረዱናል። በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ቅዱስ ዮሐንስን ጌታችን «እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ምን አግዶህ?» ብሎታል። ይህም ማለት በብሔረ ሕያዋን እስከምጽ
ት መዳረሻ /ጌታ እስከሚመጣበት ቀን ድረስ/ ሳይሞት ይኖር ዘንድ እንደፈቀደለት እንጂ ጭራሹኑ አይሞትም አላለውም። /ዮሐ. ፳፩፥፳፪-፳፫/። በሐሳዌ መሲሕ ዘመን በእውነተኛ ምስክርነቱ ሰማዕትነትን እንደሚቀበል፣ ነፍሱ ከሥጋው እንደሚለይ ያስረዳናል። ስለነቢያቱ ሄኖክና ኤልያስም ዮሐንስ በራዕዩ «ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች» በማለት የሐሳዌውን መሲሕ ክሕደት በመቃወም ምስክነታቸውን እንደሚሰጡ፥ በምድር ላይ ያሉትን ሕዝቦች እንደሚያስተምሩና ታላላቅ ተአምራትን እንደሚያደርጉ ከትርጓሜ ራዕየ ዮሐንስ እንረዳለን። /ዮሐ. ራዕ. ፲፩፥፬-፲፫/።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

11 comments:

 1. Kalehiwoten yasemalen! Yeagelgilot Zemenhen Yebark!

  ReplyDelete
 2. I believe this is very timely and GOD bless you Mele!!! Kale hiwotin yasemalin!!!

  ReplyDelete
 3. kala heiwoate yasamalen

  ReplyDelete
 4. Kalehiwoten yasemalen! Yeagelgilot Zemenhen Yebark

  ReplyDelete
 5. እንዴት ከረሙ ዲ/ን መላኩ ዳንኤል ቃለ ህይወትን ያሰማኝ እግዚአብሔር ይጠብቅህ

  ReplyDelete
 6. እንዴት ከረሙ ዲ/ን መላኩ ዳንኤል ቃለ ህይወትን ያሰማኝ እግዚአብሔር ይጠብቅህ

  ReplyDelete
 7. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ! ቸሩ አምላካችን በአገልግሎት ያጽናህ !

  ReplyDelete
 8. kalehiowten yasemalen!

  ReplyDelete
 9. qalehywetn yasemaln!

  ReplyDelete