Friday, December 23, 2011

አቡነ ዮሐንስ ዘጎንድ ተክለሃይማኖት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የጎንድ ተክለሃይማኖት የአንድነት ገዳም አባቶች ለሥራ ጉዳይ ወደጎንደር ከተማ መጥተው ስለነበር ሥራቸውን አጠቃለው ወደገዳማቸው ሲመለሱ በነበረን ቀጠሮ መሠረት አብሬአቸው ወደጎንድ ተክለሃይማኖት ገዳም መንገድ ጀመርን ፡፡
ወደማክሰኝት ከተማ የሚወስደውን ሚኒባስ በመያዝ የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረሥላሴ ፤ የገዳሙ አፈ መምህር አባ ገብረመድኅን እንዲሁም የገዳሙ ተወካይ አባ በትረስላሴ በጋራ በመሆን አርባ ኪሜ ከጎንደር ከተማ ርቀት የሚገኘውን የማክሰኝት ከተማ ስለገዳሙ እየተነጋገርን ደረስን ፡፡
ማክሰኝት ከተማ በሚገኘው የገዳሙ የእንግዳ ማረፊያ ቤት የሚቀጥለውን መኪና እስክናገኝ ዕረፍት ልናደርግ ስንገባ የገዳሙ አባቶችን መምጣት የተመለከቱት የአካባቢው ምዕመናን ከቤታችን ካልገባችሁ እያሉ ልመናቸውን አበዙት ፡፡ በመጨረሻም የሚበላ እና የሚጠጣ በመያዝ ወደገዳሙ የእንግዳ ማረፊያ ቤት ይዘው መጥተው በሚገባ አስተናገዱን ፡፡ የምዕመናኑ ለአባቶች ያላቸው ፍቅር እና ደጋግመው ሁሉም ማለት ይቻላል እንዲያው ለረድኤቱ ብለን ነው የሚሉት  ንግግራቸው ያላቸውን ፍቅር ይገልጻል ፡፡
ከማክሰኝት ከተማ በኋላ ደጎማ ከተማ ለመሄድ በመኪና ተሳፍረን የ 21ኪሜ የኮረኮንች መንገድ ከገዳሙ አባቶች ጋር ጉዞ ጀመርን ፡፡ በመንገዳችን ግራኝ በር የተባለውንና ግራኝ አህመድ ታላቅ ጦርነት አድርጎ በመጨረሻም ድል የተደረገበትን እና ተገደለበትን ቦታ እየተመለከትን ደጎማ ደረስን ፡፡

ደጎማ ከተማ አነስተኛ የከተማ መንደር ስትሆን በአካባቢው ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩት ከተማዋ ከጣሊያን ወረራ በፊት ቋራ ትባል እንደነበርና የፋሽስት ጣሊያን የጦር ጄነራል የነበረው ግራዥያኒ ቫስኮ ደጎማ ታሞ በመጨረሻም ሞቶ የተቀበረው በዚህች ከተማ ስለሆነ ስሟ እንደተቀየረ ይናገራሉ ፡፡
ከደጎማ ከተማ ወደገዳሙ ለመሄድ በእግር ከአርባ ደቂቃ በላይ እንደማይወስድ ስለተነገረን መንገዱን ጀመርነው ፡፡ የገዳሙን ወፍጮቤት አልፈን ቁልቁል ወደገዳሙ መንገድ ስንጀምር ገዳሙ ዙሪያውን በተራራ የተከበበ መሆኑ ግርማ ሞገሱን የበለጠ ጨምሮታል ፡፡የአቡነ ተክለሃይማኖት እና የአቡነ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ጎን ለጎን ይገኛሉ ተሳልመን ፤ ጸሎታችንን አድርሰን አባቶች ወደበዓታቸው እኔም ወደተዘጋጀልኝ ማረፊያ መሽቶ ስለነበር ሄድን - አባቶችም የእነርሱን መኝታ ለእኔ ሰጥተው በሰላም አድረን በሌሊት ስምንት ሰዓት ተኩል የሰዓታት ጸሎት ( ስብሐተ ፍቁር ) ለማድረስ ተደወለ ወደቤተክርስቲያን ገባን እስከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጸሎቱ ተከናወነ እና የገዳሙ አበምኔት እንደ ቤተክርስቲያናችን ባህል ስንክሳር እንዳነብ አዘዙኝ እኔም የዕለቱን ስንክሳር አንብቤ በረከት ተሳትፌ ስንወጣ ወደገዳሙ ዕቃቤት በመሄድ የአቡነ ዮሐንስን የብራና ገድል  መመልከት ጀመርኩ እስቲ በአጭሩ ከብራናው ላይ ያገኘሁትን በማሳጠር ሌሎችንም በመጨመር የተዘጋጀውን እንዲህ ተከታተሉ ፡፡
የአቡነ ዮሐንስ  እና የአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን
የአቡነ ዮሐንስ መቃብር ላይ የተሰራ
 
የጎንድ ተክለሃይማኖት የአንድነት ገዳም በዛሬው ሰሜን ጎንደር በምዕራብ በለሣ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡ ገዳሙ የጥንት ስሙ ጎንድ አማኑኤል ሲሆን በዘመን ብዛት ጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተባለ፡፡  የዚህ ቅዱስ ገዳም መሥራች አባት አቡነ ዮሐንስ የትውልድ ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ፍልስጤም በምትባል አውራጃ ሲሆን ከአባታቸው ከዲላስር እናት ከእናታቸው ከእምነፅዮን ተወለዱ፡፡ እኒህ ቅዱሳን ልጅ በማጣት ዘወትር ወደ ፈጣሪያቸው ልጅ እንዲሰጣቸው በፆምና ፀሎት ሲለምኑ ፀሎታቸው ከልዑል እግዚአብሔር ፊት ደርሶ በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ገድሉ ትሩፋቱ ሰማይና ምድር የማይችሉት ልጅ ትወልዳላችሁ ይሁንና በተወለደ በ5 ዓመቱ ከናንተ  ተለይቶ ለ495 ዓመት በገዳም ይኖራል ተብሎ ተነገራቸው፡፡ በዚሁ መሠረት የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ቀን 1110 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡

በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ገዳመ ኤራን ገብተው ከአባ ኤስድሮስ ዘንድ 45 ዓመት ከኖሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጡ ዘመኑ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከመተሎሚ ጋር ስለሃይማኖት ጉዳይ ይከራከሩ የነበረበት በመሆኑ ከአቡነ ተክለሃይማኖት እጅ ምንኩስናን ተቀብለው በደብረሊባኖስ 50 ዓመት በትሩፋት ሥራ ተጠምደው ብዙ ገቢረ ተአምራትን ያደረጉ አባት ስለነበሩ ይህንኑ ትሩፋታቸውንና ተአምራቸውን አባታችን  አቡነ ተክለሃይማኖት ተመልክተው ልጄ ዮሐንስ ሁለት መብራት በአንድ ላይ አይቀመጥምና ከእንግዲህ ወደ ደብረ ኢጎራ /ሸዋ/ ሒድ ተብለው በመታዘዛቸው በደብረ ኢጎራ በስብከተ ወንጌል 50 ዓመት ከዚያም ወደ ደብረ ሳፍጅ በመሄድ ስብከተ ወንጌልን ለሕዝቡ እያሰራጩ መንፈሳዊ ተጋድሎአቸውን ሳያቋርጡ 50 ዓመት አገልግለዋል፡፡
በመሆኑም ጌታችን ተገልፆ በብዙ ተጋድሎ መከራን ተቀብለሃልና ተዝካርህን ለአደረገ በፀሎትህ የታመነውን በስምህ ያበላውን ያጠጣውን እስከ 10 ትውልድ እምርልሃለሁ ካላቸው በኋላ በተጉለት 50 ዓመት ስብከተ ወንጌልን እንዲያሰራጩ ከዚያም ወደ ፀገሮሞና ወደገሮ አውራጃ በመሄድ 50 ዓመት አስተምረዋል፡፡  በዚህ ሥራቸው ሁሉ በየዓመቱ 3 ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ይሳለሙ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ ደብረ ኢጎራ ተመልሰው መሬት ቆፍረው ከአዘቅት ውስጥ ቁመው በከፍተኛ መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲኖሩ አፄ ዘርዓያዕቆብ ደግነታቸውን ሰምተው ልጃቸውን ክርስትና ያነሱላቸው ዘንድ ሲለምኗቸው እሺ ብለው በደብረ ብርሃን ሥላሴ ክርስትና በማንሳት የልጁን ስም በእደማርያም ውዱስ ምግባር ብለው በመሰየማቸው ንጉሡ ተደስተው ምን ልስጥዎ ቢሏቸው ሰሜን ጎንደር በበለሣ አውራጃ የምትገኘውን ሀገረ ብሕንሣን ይስጡኝ ቢሏቸው ንጉሡም እሺ ብለው ገድመው ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ተመልሰው ወደ ደብረ ኢጎራ በመሔድ በአዘቅት ጉድጓድ ውስጥ ሆነው ተጋድሏቸውን ቢጀምሩም የአካባቢው ሕዝብ ሀገራችንን በንጉሡ በማስፈቀድ ይወስዱብናል በማለት በቅናት መንፈስ ጉባኤ አድርገው ስላመፁባቸው ቅዱስ አባታችን በ1460 ዓ.ም. ቦታውን ረግመው በብርሃን ሠረገላ ተጭነው ጎንደር ምድር በመምጣት የገዳሙን ቦታ በመመልከት በዋሻ ውስጥ ገብተው 50 ዘመን በበለሣ ስብከተ ወንጌልን እያሰራጩ አጋንንትን በነፋስ ፊት እንደትቢያ እያደረጉ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ከቆዩ በኋላ ጌታችን በብርሃን ሠረገላ ሆኖ ከቅዱሳን መላእክትና ሐዋርያት ጋር ተገልፆ 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳን ከመስጠቱም በላይ ስለድንግልናህ ንፅሕና ከፍተኛነት የክረምት ዝናብ ነጠብጣብ ያህል የኃጥአንን ነፍስ ከሲኦል አወጣልሃለሁ ካላቸው በኋላ በደመና ላይ 50 ዘመን እንዲኖሩ ስለወሰነላቸው በደመና ላይ ወጥተው 50 ዘመን ሙሉ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ሲኖሩ የእመቤታችን የብርሃናውያን መላእክት ሥዕል ያለበት መስቀል ተሰጣቸው፡፡
ከዚህ በኋላ 50 ዘመን ዓለምን ዞረው እንዲያዩ ተፈቅዶላቸው ከደመና ወርደው 50 ዘመን ዑደተ አፅናፈ ዓለም አድርግው ወደ ገዳማቸው ጎንድ በመመለስ ዕረፍት እንዲያገኙ ወደ ፈጣሪያቸው ቢያመለክቱ በወዳጄ በተክለሃይማኖት ወንበር በዕጨጌነት /በጠባቂነት/ ማዕረግ እንድትሾም ለ7 ቀን ዕድሜ ስለፈቀድኩልህ ወደ ደብረሊባኖስ እንዲሔዱ ታዘዙ፡፡
ከዚያም ደብረሊባኖስ ሲሔዱ ዕጨጌ አግናጥዮስ አርፈው የአቡነ ተክለሃይማኖት የቆብ ልጅ ካልሆነ በአቡነ ተክለሃይማኖት ወንበር ሌላ አይቀመጥምና አቡነ ዮሐንስ 36ቱ ኖሎት ዕጨጌነት ሹመዋቸዋል በዚያ የ7 ቀን ሹመት ውስጥ 11 ሙት አስነስተዋል፡፡ ይኽ የ7 ቀን ጨጌነት ሹመት እንዳበቃ ወደገዳማቸው ጎንድ ሐምሌ 26 ቀን በመመለስ ሐምሌ 27 ቀን ለሞት በሚያበቃ ደዌ በመታመማቸው ሐምሌ 29 ቀን ሊያርፉ እንደተቃረቡ ጌታችን ከገዳመ አስቄጥስ  መነኮሳትን ቅዱስ ሚካኤልን በቀኝ ቅዱስ ገብርኤልን በግራ ቅዱስ ፋኑኤል በፊት ቅዱስ ራጉኤል በኋላ በመሆን መቃብራቸውን አንስተው በጌታችን አስባርከው ቃል ኪዳን ተቀብለው ነፍሳቸው በመዓዛ  ገነት በይባቤ መላዕክት ከክብር ሥጋቸው በመለየት ጌታችን ከቅዱሳን ወዳጆቹ ጋር ይዟት ሲሄድ አስከሬናቸው በቅዱሳኑ በምሥጋና ተገንዞ በ1610 ዓ.ም ተቀብሯል፡፡ ከተቀበሩበት ቀን እስከ 80 ቀን ድረስ በገዳሙ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ ሰንብቷል፡፡
ባረፉ 157 ዘመን ጳጳሳቱ ነገሥታቱ ካህናቱ መኳንንቱ ወደ ጎንድ በመምጣት በብዙ ምህላና ፆም ፀሎት አፅማቸውን አውጥተው በክብር በምስጋና ወደሸዋ ደብረ ኢጎራ በመውሰድ የረገሙትን ምድር እንዲባርኩ አድርገዋል፡፡  ይህ ታላቅ ገዳም /ጎንድ/ ከአባታችን ዕረፍት እስከ ግራኝ መነሳት በሠላም ቆይቶ በግራኝ ተቃጥሎ ለ15 ዓመታት ጠፍ ሆኖ ሲቆይ በአፄ ገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት እንደገና ተቋቁሞ በሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በመነኮሳቱ ላይ በተፈፀመ ጭፍጨፋ ተዳክሞ ቆይቶ በአፄ ዳዊት እንደገና ገዳሙ ተስፋፍቶ እስከ ፈፃሜ መንግሥት አፄ ተክለጊዮርጊስ  ድረስ በሠላም ቆይቶ በአፄ ዮሐንስ ዘመን በድርቡሽ ወረራ ገዳሙ ጠፍቶ መነኮሳቱ ከሰይፍ ያመለጡት ተሰደዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ድርቡሾች የፃድቁን ገድል ወስደው ወደ ሀገረ እንግሊዝ አሻግረው በዚያ የተነሳ ገድሉ ከቦታው በመጥፋቱ አፄ ምኒሊክ በራስ መኮንን ባልደረባነት ገድሉ ክደብረ ሊባኖስ ገዳም ተጽፎ ወደገዳሙ እንዲላክ ተደርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአንድነት ገዳሙ መነኮሳትና አርድዕት በማህበር ይተዳደሩ የነበረው በእርሻ ሥራና ከሁለት ቋት ወፍጮዎች በሚገኝ ገቢ ሲሆን በየጊዜው በተደጋጋሚ በደረሰው የዝናብ እጥረት በወፍጮዎች መበላሸትና መለዋወጫ ማጣት የተነሳ በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ፡፡
ገዳሙ በሥዕለትና በሌሎችም ገቢዎች እንዳይገለገል ከዋናው መንገድ የራቀ በመሆኑ ጭምር ይህ የሀገሪቱ ዋና ቅርስ የሕዝቡ ሰፊ መርከብ የሆነው ጥንታዊ ገዳም የፈረሱ ቤተክርስቲያኖች ለመጠገን እንዲሁም ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ ችግሩ ከገዳሙ መነኮሳት አቅም በላይ በመሆኑ ይህ ታላቅ ገዳም ከመጥፋቱ በፊት ምዕመናን እገሌ ከገሌ ሳንባባል ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ከፃድቁ አባታችን ረድኤትና በረከት እንድንሳተፍ በፃድቁ አባታችን ሥም ገዳሙ ጥሪውን ያስተላልፋል ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን በሠላም ይጠብቅልን፡፡5 comments:

 1. Wolde Amanuel Ke' ZambiaDecember 23, 2011 at 10:33 AM

  Wondimachin Diakon Melaku,
  Fetari Alemat ajig adirgo bereketun yadilih! Ye'abatachin Abune Yohannes & Abune Teklehayimanot milja ayileyih! Le'egnam Amlak endiaberetanina gize lenisiha setiton Gedamun lemayet endiabekan betselotih asiben!
  Silehulum neger Egziabher Yimesgen!!!

  ReplyDelete
 2. ዲያቆን መልአኩ
  ፈጣሪ ዕውቀቱን ያብዛልህ።

  ReplyDelete
 3. May the Lord bless you and your family
  One thing I don`t agree is:
  ከተማዋ ከጣሊያን ወረራ በፊት ቋራ ትባል እንደነበርና የፋሽስት ጣሊያን የጦር ጄነራል የነበረው ግራዥያኒ ቫስኮ ደጎማ ታሞ በመጨረሻም ሞቶ የተቀበረው በዚህች ከተማ ስለሆነ ስሟ እንደተቀየረ ይናገራሉ ፡፡
  Is it so ...Is it not named from the leader of the portugal 400 army members called Christopher Dagama, the son of Vasco Dagama?

  ReplyDelete
  Replies
  1. by the way DEGOMA the word it self in Amaharec means to help to support specially in old age...it dos not mean Dagama or any other thing.. and by the way i was born in Degoma.. and most of my family including my father is buried in GOND TEKLEHIMONOT. GONDTEKLEHIMANOT it is special place for me and countless generation of my family!!!
   and thank you for the story it is the hardest article i have ever read,i have a lots of connection to that holy place...i don't know how i can help but i will do everything in my power to do so,and GOD almighty to help me...

   Delete
 4. thank you brother! May God give you the strength!very interesting stories and places I know!

  ReplyDelete