Friday, July 27, 2012

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ


 
......«ሐምሌ 22 ቀን 1928  ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። .........

በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።
ከዚያም ከቅኔው ዐውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩ ሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አሔዱ።
ከዚህ በኋላ ልክ በ1900 ዓ.ም. እዚያው ወሎ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሔድ ወንበር ዘረጉ። በዚያው ቦታ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ።
በዚህ ዓይነት በመማርና በማስተማር ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል በሚገባ ከጐሰሙ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ። ብዙም ሳይቆዩ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለው ከወንበሩ አገልግሎት ጋር የቤተ መቅደሱን ተልእኮም ደርበው ያዙ።
በ1910 ዓ.ም. መምህር ኃይለ ማርያም ተብለው በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም. እንደገና በዝዋይ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በ1919 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ። 
የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ አገረ ስብከት ተሾሙ።
በ1928 ዓ.ም. አረመኔው የኢጣልያ ፋሺስት በግፍ አገራችንን ለመውረር ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት በማለት ውቅያኖስ አቋርጦ በመምጣት ኢትዮጵያን ሲወርና ሕዝቧን፣ ሊቃውንቷን፣ ገዳማቷንና አድባራቷን በግፍ ሲጨፈጭፍ ያዩት ብፁዕነታቸው ወራሪውን ኃይል ከኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎት ሊዋጉት ቆረጡ። የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከአረመኔው ፋሺስት ጦር ጋር በመፋለም ላይ የነበረውን አርበኛ ለማበረታታት ወደ ማይጨው በሔዱ ጊዜ ብፁዕነታቸው ተከትለው ሔዱ። ከዚያ እንደ ተመለሱም በታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ተሰባስበው የቤተ ክርስቲያን አምላክ በኢትዮጵያውያን ላይ የመጣውን ችግር እንዲያስታግሥ በጸሎት እየተጉ ወደነበሩት አባቶችና አርበኞች በመሔድ ለአገርና ለነጻነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን በመስበክ ሁሉም እንዲጋደሉ ማሳሰብ እና ማትጋት ጀመሩ። ኋላም የገዳሙ መነኮሳትና የሰላሌ አርበኞች ይባሉ የነበሩት አርበኞች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተሳታፊ ሆኑ። ከዚያም አርበኞቹ የቻሉትን ሁሉ አድርገው ወደ ሰላሌ ሲመለሱ ብፁዕነታቸው አዲስ አበባ ቀሩ። ብዙም ሳይቆዩ በጠላት እጅ ተያዙ።
ብፁዕነታቸው በተጠቀሰው ቀን በጠላት እጅ ከወደቁበት ቀን ጀምሮ በፋሺስት ኢጣልያ የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞችና የታሪክ ጸሐፍት እንደሚከተለው ዘግበውታል።
«በኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ» የሚለውን ቃለ ምዕዳን ለገዳዮቻቸው ፋሺስቶች ያስተላለፉት ስለ አገር ነጻነት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር፣ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ሲሉ በሰማዕትነት ያረፉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው።
ይህንንም የተናገሩት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት ሕይወቱን ለመስጠት በዚያች በመከራ ሌሊት ሊይዙትና ሊገድሉት ለመጡት ለሮማውያን ጭፍሮች “ማንን ትፈልጋላችሁ? እኔ እንደ ሆንኩ አለሁላችሁ። እነሱን ግን ተዉአቸው ይሒዱ” /ዮሐ. ፲፰፥፰/ ሲል በተከታዮቹ ላይ መከራ እንዳይፈጽሙባቸው የተናገረውን ቃል ለሕይወታቸው መመሪያ በማድረግ፣ መስቀሉንም ተሸክመው በኋላ ለመከተልና ፍኖተ መስቀሉንም ተጉዘው የሰማዕትነት አክሊል ለመቀዳጀት ነበር። ቆመው ሞትን በሚጠባበቁበት ጊዜ የዛሬ 75 ዓመት ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ነበር።
እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገባው ቺሮ ፓጃሊ “ከሪያሬ ዴስራ” የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረ ሲሆን ስለ አቡነ ጴጥሮስ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።
«ሐምሌ 22 ቀን 1928 አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዝያኒ ቀረቡ። በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊው ጳጳስ ቀርበው ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም ሲሉ ለግራዝያኒ ነገሩት። ምክንያቱም ይላሉ አቡነ ቄርሎስ፤ አቡነ ጴጥሮስ ታላቅ ሰው ናቸው። በመሠረቱ ሊያዙ ባልተገባ ነበር። ከተያዙም ደግሞ ልትገድላቸው ትችላለህ። ነገር ግን በርሳቸው ላይ የምታደርገውን ነገር ሁሉ ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ ምንም ማድረግ አይገባህም አሉት።
አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው እንደ ነበር ግልጥ ነው። ነገር ግን ግራዝያኒ ይህ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብፅ ከአዲስ አበባ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም ትእዛዝ አስተላለፈ።
ጸሐፊው ሲገልጥ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር። በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ። ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣልያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው። የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር። የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም ዐምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር። ዳኛውም «ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?» ሲል ጠየቃቸው።
አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ። «አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለአገሬና ስለቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ» አሉ።
ኢጣልያዊው ጋዜጠኛ ቺሮ ፓጃሊ «እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣልያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጐም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጐመም። እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበባ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቤ ተቀምጦ ስለነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለገለጠልኝ ነው። እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተሰበሰቡት ጣልያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር» ይላል።
ሆኖም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ እንደ ቀረ ይጽፋል። ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለእርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣልያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ይታይ ነበር።
«ይሙት በቃ» የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሟቸው ስለነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው። በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው። ብፁዕነታቸው እስከመቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ የሆነ ፍጹም የክብር ትሕትና ይታይባቸው ነበር።
የአገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ ለመገደል ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይጐዳ ግንብ ይፈለግ ጀመር። ሩቅ ባለመሔድ ከመካነ ፍትሑ 10 ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ። ከገዳዮቹም አንዱ «ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?» ሲል ጠየቃቸው። «ይህ የአንተ ሥራ ነው» ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ። ከመግደያውም ቦታ እንደ ደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ።
ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። 
የብፁዕነታቸው አስከሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር ተደረገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ» ሲል ጽሑፉን ይደመድማል። ይህም ጠላት የሰጠው ምስክርነት በካቶሊካዊው ፓፓ ቡራኬ አገራችንን የወረረውን የፋሺስት ኢጣልያን ጦር አረመኔነትና በአንጻሩ የታየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጀግንነት ሲያረጋግጥ ይኖራል።
በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «አቡነ ጴጥሮስ  እንዴት ሞቱ?» ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውም የሚከተለውን ተናግረዋል። «አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም የያዙትን መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው። ይህ እንደ ሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ። 
ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት «በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል» አለኝ። «እንዴት?» ብለው «አላየህም ሲያጨበጭብ?» አለኝ። እኔም «ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል» አልኩት። «እንዴት?» ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት። እሱም አሳየኝ። «ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ» ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኪስ ሰዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተሰንጥቋል። መስቀሉም ልክ በመሐከሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል። የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንደዚሁ ጥይት በስቶታል» ብለው ያዩትን መስክረዋል።» /ትንሣኤ፣ ቁጥር 58፣ 1978 ዓ.ም./
የብፁዕነታቸው አኩሪ ታሪክ ትውልድ ሲያዘክርላቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ሐውልት ቆሞላቸዋል።
የተጋዳዩና ሰማዕቱ አባታችን በረከት ይደርብን። አሜን።
ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ግንቦት/ሰኔ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም.


16 comments:

  1. amene!!!yatanewe endihe anyenet girum egiziaharen yemifera abate newe

    ReplyDelete
  2. GOD bless you Mele! Kale hiwot yasemalin!

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔር ይስጥልን ዲ/ን መላኩ!
    ዛሬ የአባቶቻችን እምነት እና ጥንካሬ የት ገባ

    ReplyDelete
  4. God bless U Bro ! Abune Petros Martyr of Ethiopia U R In On the hip of our heart !

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር ይስጥልን ዲ/ን መላኩ!
    ዛሬ የአባቶቻችን እምነት እና ጥንካሬ የት ገባ

    ReplyDelete
  6. «አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለአገሬና ስለቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ» አሉ።

    መንፈሳዊ ሰው ሀገሩን ይወዳል እስከ ሞትም ይደርሳል፡፡ ይህንን አባታችን በተግባር አሳይተውናል፡፡የቅዱሱ አባታችን በረከታቸው በሁላችንም ይደርብን አሜን፡፡

    ReplyDelete
  7. amene mechi yihone enedzihe yalu abate yemenagegn!!!

    ReplyDelete
  8. ዲ/ን መላኩ ጽሁፍህ ጥሩ መልእክት ያስተላልፋል ግን አንዳንድ ግድፈቶች አሉት ለምሳሌ ''በ1916 ዓ.ም. እንደገና በዝዋይ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመምህርነት ተሾሙ።'' የሚለው ስህተት ነው:: በዝዋይ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሚባል የለም:: ዝዋይ ላይ ያለው የቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሐመረብርሐን ነው የሚባለው:: በዛ ወቅት ደግሞ ሐመረ ብርሐን አልነበረም ወይም አልተመሰረተም:: በተጠቀሰው ወቅት አቡነ ጴጥሮስ መምህር ኃይለ ማርያም ተብለው የተሾሙት በዝዋይ ደብረጽዮን ቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም ነው:: መምህር ኃይለ ማርያም/አቡነ ጴጥሮስ ከዚያች ገዳም ተነስተው አዲስ አበባ ሲመደቡ ዝዋይ ደብረጽዮን ገዳምን በጣም ይወዷት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ ይወዱት የነበረውን መቋሚያቸውን ለገዳሙ አበርክተው ነው የሄዱት:: አሁንም ድረስ ስማቸው የተጻፈበት መቋሚያቸው በዚያች ገዳም በቅርስነት በክብር ተቀምጧል:: ይህ ገዳም የሚገኘው በዝዋይ ሐይቅ ላይ ከሚገኙት ደሴቶች በአንዱ ነው:: ይህች ደሴት/ገዳም በአርሲ ሃገረ ስብከት ስር የምትገኝ ስትሆን ታቦተ ጽዮንን በዮዲት ጦርነት ዘመን ተቀብላ በክብር ለ40 አመታት ጠብቃ በማቆየት ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ አበርክታለች:: ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ቦታዎች የማይገኙ ድንቅ ድንቅ የጥንት የብራና መጻህፍትን እስካሁንም በክብር ይዛ ትገኛለች:: ከነዚህ ጥቂቱን ለመጥቀስ ያክል: (1) መጽሐፈ ሔኖክ በዚች ደሴትና በጣና ሃይቅ ላይ በሚገኝ አንድ ደሴት ብቻ ተገኝቷል አሁንም በክብር አለ:: (2) በ1972 ዓ.ም በሌጎስ ላይ በተካሐደው የአለም እደጥበባት ውድድር ላይ ኢትዮጵያ 1ኛ እንድትሆንና የወርቅ ሽልማት እንድታገኝ ያስቻላት የ19 ቅዱሳንን ገድል በአንድነት የያዘውና በክብደቱ እጅግ ትልቅ ከመሆኑ የተንሳ አንድ ሰው/በጣም ጉልበት ያለው ሰው ሊያንቀሳቅሰው የማይችለው ትልቁ የብራና መጽሐፍ ነው::

    Mekonnen

    ReplyDelete
  9. ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት «በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል» አለኝ። «እንዴት?» ብለው «አላየህም ሲያጨበጭብ?» አለኝ። እኔም «ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል» አልኩት።

    ReplyDelete
  10. ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት «በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል» አለኝ። «እንዴት?» ብለው «አላየህም ሲያጨበጭብ?» አለኝ። እኔም «ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል» አልኩት።

    ReplyDelete
    Replies
    1. Ye Abatachinin meswat Egziabher yimelket. ahunim yihichin hager kemenafik ena kekifu agezaz Egziabher yitadegat. Egziahbher yeagelot zemenhin yibark

      Delete
  11.  GOD beless u deakon

    ReplyDelete
  12. bereketachew yideriben

    ReplyDelete
  13. የሳቸውን ወኔ በሁላችን እመቤታችን ትሳልብን.

    ReplyDelete