Showing posts with label ድንግል ማርያም. Show all posts
Showing posts with label ድንግል ማርያም. Show all posts

Friday, August 22, 2014

ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር

እንኳን  አደረሳችሁ



ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤ በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ ፤ ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ

እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ፡፡ ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡
               መልክአ ማርያም


ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡

Tuesday, November 27, 2012

እምነ ጽዮን - እናታችን ጽዮን

እንኳን ለኅዳር ጽዮን በሰላም አደረሳችሁ
በቅዱሳት መጻሕፍት ጽዮን የሚለው ቃል ተደጋግሞ በነቢያቱ ተነግሯል፡፡ ሆኖም የጽዮን ትርጉም እንደተነገረበት ዐውደ ትንቢት እንደተሰበከበት መዋዕለ ትምህርት ምስጢሩ ይለያያል፡፡
ድንግል ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳ
 ታቦተ ጽዮን በፈቃደ እግዚአብሔር በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ለሰው ልጆች ተሰጥታ እስራኤላውያን ሲባረኩባት፣ መሥዋዕታቸውን ሲያቀርቡባት ከእግዚአብሔር ሲታረቁባት ኖረዋል፡፡ከአራት ሺሕ ሦስት መቶ ሃያ ሰባት ዓመተ ዓለም (4327 ዓ.ዓ.) ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያህል እስራኤላውያንን በክህነት ያገለግል የነበረው ካህኑ ዔሊ ዕድሜው ሲገፋ ሁለት ልጆቹን ጠርቶ ምሉዕና ዱግ /ዋናና ምክትል/ አድርጎ ሾማቸው፡፡
በደብተራ ኦሪት ታቦተ ጽዮንን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሁለቱ ወጣት ካህናት /አፍኒን እና ፊንሐስ/ ፈቃደ እግዚአብሔርን ተላልፈው ሦስት ታላላቅ በደሎችን ፈጸሙ፡፡ የመጀመሪያው በደል፤ በሙሴ ሥርዓት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርታ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት የምትጠፋ መብራት እንድትቀመጥ የተሠራ ሥርዓት ነበር፡፡ ሆኖም አገልግሎት ከሌለ ሲበራ ማደሩ ለምን ? ብለው መቅረዙን አነሡ፤ መብራቱንም አጠፉ፡፡ ሁለተኛ፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ለመሥዋዕት እንዲሆን ከመጣው እንስሳ ታርዶ ስቡ ሳይጤስ፣ደሙ ሳይፈስ ሥጋውን እየመረጡ ተመገቡ፡፡ሦስተኛ ጸሎት እናደርሳለን ሥርዓተ አምልኮ፣ እንፈጽማለን ብለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጡ ከነበሩት እስራኤላውያን ቆነጃጅት ጋራ በዝሙት ወደቁ፡፡ አባታቸው ካህኑ ዔሊም የልጆቹን በደል እያየ እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ቸል በማለቱ እግዚአብሔር አዘነ፡፡ በዚህም ምክንያት ፍልስጥኤማውያንን አስነሥቶ በጦርነት ቀጣቸው፡፡

Wednesday, November 14, 2012

የቤተልሔም ሕጻናት እና የራሔል እንባ


« እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክየይ ፤ ለሥራሽ ፤ ዋጋ ይሆናልና ፥ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ ፥ ይላል እግዚአብሔር ፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸዎ ይመለሳሉ። » ኤር ፴፮ ፥፲፭ ፡፡

የቤተልሔም ህጻናት በግፍ ሲገደሉ
ቅዱሳን ነቢያት የሚናገሩት ስለ ዘመናቸው ብቻ አይደለም ፤ ከዘመናቸው ጋር በማገናዘብ ስላለፈው ይናገራሉ ፥ ስለሚመጣውም ይተነብያሉ። ዓረፍተ ዘመን ሳይገታቸው ኃላፊያትንም መጻእያትንም ይተረጉማሉ። በመሆኑም ይህ ቃለ ኤርምያስ ወደኋላም ወደፊትም የሚሠራ ነው። ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ የባርነት ዘመን የነበሩበትን ዘመን ያስታውሳል ፥ ለፍጻሜው ደግሞ በዘመነ ሥጋዌ መባቻ ማለትም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የተፈጸመውን ያሳያል።

Sunday, October 7, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 2


የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
  የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን  አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

Friday, August 10, 2012

ፅንሰታ ለማርያም

እንኳን ለፅንሰታ ለማርያም በዓል ነሐሴ 7 በሰላም አደረሳችሁ
ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ 
አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ

ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ፤ 
በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም
ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር: እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ:፡ እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸውባለጸጎች ነበሩ::ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅአልነበራቸውምና መካን ነበሩ:፡

Friday, February 24, 2012

ኪዳነ ምሕረት



ኪዳን የሚለው ቃል ‹‹ቃል›› ከሚለው ጋር እየተዛረፈ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳን ደግሞ ከ32 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ኪዳን›› ቃሉ ‹‹ተካየደ›› ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ምሕረት›› የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡

‹‹
ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ›› ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ (መዝ88.3) ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡

        በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃል ኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡

Monday, December 12, 2011

በዓታ ለማርያም


እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽዕ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡
ከዚህ በኋላ እመቤታችን መዋዕለ ጥብ እስክታደርስ ድረስ በአባት እናቷ ቤት 3 ዓመት ተቀመጠች፡፡ ከመዝ ነበረት ውስተ ቤተ አቡሃ ወእማ 3ተ ዓመተ እንዘ ትጠቡ ሐሊበ እማ (እንዳለ በነገረ ማርያም፡፡)
ኢያቄምና ሐናም ልጃቸውን ሲያሰሳድጉና ስላደረገላቸውም ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው ሲያመሰግኑት ሦስት ዓመት ኖሩ። በጾም፤ በጸሎት ተወስነው ለድሆችና ለጦም አደሮች ምፅዋት እየሰጡ በጐ ሥራ መሥራትን አበዙ።
      ልጃቸውንም ድንግል ማርያምን በንጽሕና ሲያሳድጉ ሦስት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሐና ባሏን ኢያቄምን “ወንድሜ  ሆይ ልጃችንን ለቤተ እግዚአብሔር ብፅዐት አድርገን እንስጥ። ልጃችን ቤተ እግዚአብሔርን ልታገለግል እንጂ በዚህ ዓለም እኛን ልታገለግል እንዳልተሳልን አስብ አለችው።” ኢያቄምም ይህን ነገር ከሚስቱ በሰማ ጊዜ ደስ አለው።