Showing posts with label ነገረ ክርስቶስ. Show all posts
Showing posts with label ነገረ ክርስቶስ. Show all posts

Wednesday, January 7, 2015

የመገለጥ ሃይማኖት በአስተርእዮ

በዲያቆ ብርሃኑ አድማስ
የጥምቀት በዓል በጎንደር
ሃይማኖት የምንቀበለውና የምንጠብቀው እንጂ የምንሠራውና የምናሻሽለው አይደለም ከታኅሣሥ 29 ቀን ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት /ጊዜ/ ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ወራት/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በታኅሣሥ 29 ቀን የጌታችን ልደት ስለሆነ በዚህ አምላክ በሥጋ የተገለጠበት በዓል ይከበራል፡፡ ጥር 11 ቀን ደግሞ በጌታችን ጥምቀት የሥላሴ አንድነት ሦስትነት በይፋ የተገለጠበት ነው፡፡ ጥር 12 ቀን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ማስተማር በጀመረበት ጊዜ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ አምላክነቱን በይፋ የገለጠበት በዓል ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ዓበይት መገለጦች ወቅቱን በአጠቃላይ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተገለጠበትን መታሰቢያ አደረጉት፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን ትክክለኛ ሃይማኖት ከሚያሰኙት መሠረታዊ ነጥቦች ዋነኛውና ቀዳሚው የመገለጥ ሃይማኖት /Revealed Religion/ መሆኑ ነው፡፡

Sunday, April 13, 2014

አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል


               በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት አሥራ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)

              መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተኰርዖት›› የሚለው ቃል ኩርዐ - መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ርእስ ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ 27-24 ማር 15-15 ሉቃ 23-25 ዮሐ 18-39)፡፡

                መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው ራሱ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር 15-19)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾህ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የሆነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ ተንኮል የተጐነጐነ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡

Tuesday, January 15, 2013

ምሥጢረ ሥላሴ

                  እንኳን ለጥር ሥላሴ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ምሥጢር
አመሠጠረ ከሚለው ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ስውር ድብቅ ሽሽግ ማለት ሲሆን አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትም ምሥጢር የተባሉበት ምክንያት
  • በሥጋዊ ጥበብ ምርምር መረዳት ስለማይቻሉ
  • ላመኑት እንጂ ላላመኑት ሰዎች የተሰወሩ በመሆኑ
 ምሥጢር በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም፡-
 የፈጣሪ ምሥጢር- ሊገለጥ የማይችል ነው፡፡ እስከ የሌለው ምሥጢርም ይባላል፡፡
 የፍጡራን ምሥጢር- በጊዜ የሚገለጥ /የሚታወቅ/ ነው፡፡ የሰውና የመላእክት ምሥጢር በዚህ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

Tuesday, November 6, 2012

መልከ ፄዴቅ የክርስቶስ ምሳሌ ክፍል 2



ካለፈው ክፍል አንድ የቀጠለ

ታዲያ የጌታችን ክህነት በመልከ ፄዴቅ ክህነት ለምን ተመሰለ?

የነገር ጥላ አለውና” ዕብ 10እንደ ተባለ ለሰው ረቂቁን በግዙፉ  የሚታየውን በማይታየው መስሎ መናገርና ማስረዳት የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም እኛ የሰው ልጆች ከህሊናት በላይ የሆነውን እግዚአብሄርን መረዳት የቻልነው በምሳሌ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ ነበር፡፡ በዚህም አንፃር መልከ ፄዴቅ የወልደ እግዚአብሄር ምሳሌው እንጂ ራሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ምሳሌ የሆነውም መልከ ፄዴቅ ብቻ አልነበረም ፦ዮናስ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል ማቴ 16 ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው እባብ ዮሐ 314  ሙሴ ዉሃን ያፈለቀበት ዐለት 1ኛቆሮ 10እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሳሌወችም አሉት፡፡ 

ታዲያ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልከ ፄዴቅ የተመሰለበት ምክንያትም የሚከተሉት ናቸው ;- 

Tuesday, October 30, 2012

መልከ ፄዴቅ የክርስቶስ ምሳሌ ክፍል 1


ዕብራውያን 7: 1-10 “ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።…….”

          አብርሃምና መልከጼዴቅ እንደተገናኙ
ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ጠቀሰው
በታላቁ መምህር በገማልያል እግር ሥር በትሕትና የተማረው ምሁረ ኦሪት ቅዱስ ጳውሎስ ከደማስቆ ከተማ ተጠርቶ፣ ሕገ ወንጌልን ተቀብሎ፣ በሕገ ወንጌል ጸንቶ ለወገኖቹ ለዕብራውያን ባስተላለፈው መልእክቱ ስለዚህ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፣ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ (ዕብ.3÷1)፡፡