“የነገር ጥላ አለውና” ዕብ 10፡1 እንደ ተባለ ለሰው ረቂቁን በግዙፉ ፡ የሚታየውን በማይታየው መስሎ መናገርና ማስረዳት የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም እኛ የሰው ልጆች ከህሊናት በላይ የሆነውን እግዚአብሄርን መረዳት የቻልነው በምሳሌ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ ነበር፡፡ በዚህም አንፃር መልከ ፄዴቅ የወልደ እግዚአብሄር ምሳሌው እንጂ ራሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ምሳሌ የሆነውም መልከ ፄዴቅ ብቻ አልነበረም ፦ዮናስ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል ማቴ 16፡4 ፣ ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው እባብ ዮሐ 3፡14 ፣ ሙሴ ዉሃን ያፈለቀበት ዐለት 1ኛቆሮ 10፡1 እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሳሌወችም አሉት፡፡
ታዲያ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልከ ፄዴቅ የተመሰለበት ምክንያትም የሚከተሉት ናቸው ;-
ታዲያ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልከ ፄዴቅ የተመሰለበት ምክንያትም የሚከተሉት ናቸው ;-
- ለመልከ ጼዴቅ አባቱ እገሌ ነው እናቱ ደግሞ እገሊት ናት ተብሎ አለመነገሩ ለጌታም ለሰማያዊ ልደቱ ከአብ ሲወለድ እናቱ እገሊት ናት አይባልም፡፡ ለምድራዊ ልደቱም ከእመቤታችን ሲወለድ አባቱ እገሌ ነው አይባልም፡፡ እርሱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት፣ ድኅረ ዓለም ደግሞ ከእመቤታችን ያለ አባት ተወልዷልና፡፡
- ለመልከ ጼዴቅ ‹‹ለዘመኑም ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም›› ተብሎለታል፡፡ ጌታችንም ለዘመኑ ጥንትና ፍጻሜ የለውም፡፡ ‹‹አልፋና ኦሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው›› እርሱ ነው (ራእይ፡- 22÷1፣1÷17)፡፡
- መልከ ጼዴቅ በስንዴ እና በወይን ያስታኵት ነበረ፡፡ ጌታችን ደግሞ ሥጋውን በስንዴ ደሙንም በወይን አድርጐ ሰጥቶናል (ማቴ. 26÷26)፡፡ መልከ ጼዴቅ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ለመጣው ለአብርሃም ኅብስትና ወይንን እንደመገበው ጌታም በመስቀል ላይ የቆረሰው ኅብስት-ሥጋውን እና ያፈሰሰውን ወይን-ደሙን ዮርዳኖስን ተሻግረን (ተጠምቀን) ለቀረብን ለውሉደ ጥምቀት (ለጥምቀት ልጆች) መግቦናል፡፡
- መልከ ጼዴቅ ሹመቱን ከእገሌ አግኝቶታል፣ ለእገሌም ተላልፏል አይባልም፡፡ ሹመቱን ያገኘው ከእግዚአብሔር ነው፡፡ “ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፡፡ ነገር ግን ‹‹አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፡፡ እንደዚህም በሌላ ሥፍራ ደግሞ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ “ (ዕብ.5÷5) ተብሎ ተነግሮለታል፡፡ በዚህ መሠረት ጌታንም ስለለበሰው ሥጋ “ሤሞ አቡሁ፡- አባቱ ሾመው ይለዋል”፡፡ እዚህ ላይ የተሾመው፣ ሥልጣንን ያገኘው፣ በተዋሕዶ አምላክ የሆነ ሥጋ ነው፡፡ ይህም ሹመት እንደ መልከ ጸዴቅ ሹመት ለእገሌ አለፈ አይባልም፡፡
የሌሎቹን
ሊቃነ ካህናት ሹመት ብንመለከት ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የአሮን ሹመት ለልጁ ለአልዓዛር ተሰጥቷል (ዘኁ.20÷22)፡፡
ካህናት፣ ሊቃነ ካህናት ሆነው የሚሾሙትም ሌዋውያን ብቻ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ መልከ ጼዴቅን የጠቀሰው ያለ ምክንያት
አልነበረም፡፡ ለሮሜ ምእመናን በጻፈው ክታቡ (ሮሜ.4÷1) ጽድቅን ከኦሪት አውጥቶ ለወንጌል እንደሰጠ ተናግሮ፣ ለዚያው ምስክር
አብርሃምን እንዳመጣ፣ ከዚህም ክህነትን ከቤተ ሌዊ አውጥቶ ለቤተ መልከ ጼዴቅ አምጥቶታል፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የጥንቱን ይዘው
ክህነት ለሌዋውያን ብቻ ነው ይሉ ስለነበር ነው፡፡
ጌታችን ስለምን ሊቀካህናት ተባለ?
ከላይ በመልከ ፄዴቅ እንደተመሰለ አሁን ደግሞ በኦሪት ሊቀ ካህናት ተመስሏል፡፡ ስለ ምን? ስለጌታችን ክህነት የመልከ ፄዴቅ ምሳሌነት ያልገለጠው ነገር አለ ፤ ይሄውም አገልግሎቱ ነው፡፡ ጌታችንም ሊቀ ካህናቱን ምሳሌ ያደረገው ከዚህ አገልግሎቱና ከአለቅነቱ አንፃር ነው፡፡ ይሄውም ፦
1. ሊቀ ካህናት ከሰው ተመርጦ ለሰው ይሾማል - - - ዕብ.5:1 “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና” እንዲል፡፡ ሊቀ ካህናት ሰው ነው ፡ ከሰው ይመረጣልና የሚሾመውም ለሰው እንጂ ለራሱ ክብር አይደለምና፡፡ ጌታችን ክርስቶስም ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ነው፡፡ የአብርሃም ልጅ የዳዊት ልጅ ተብሏልና፡፡ማቴ 1፡1 ሊቀ ካህናት ስለሰው እንደሚሾም ጌታችንም ሰው የሆነውና ክህነትን ገንዘብ ያደረገው ስለ ሰው ነው፡፡ የሰውን ሃጢአት ለማራቅ ሰው ሆኗልና፡፡ዮሐ.3:16-17 ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” 1ጢሞ.1:15 “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” እንደተባለ፡፡
2. ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው ሊቀ ካህናት ብቻ ነው - - - ይህንንም በዘሌ16፡2 የተጠቀሰውን ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.9:6-7 “ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ገልፆታል፡፡ ጌታችንም የገባባት ቅድስተ ቅዱሳን በሰው ያልተተከለች በፈቃደ እግዚአብሄር የሆነች ከእርሱም በፊት ከእርሱም በኅላ ማንም ያልገባባትና የማይገባባት ናት፡፡ ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ ይገባል ፡ እርሱ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ገባ ፤ ለዓለምና ለዘላለም መስዋእቱ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እነዚያ በየዓመቱ የሚገቡት ሟች ስለሆኑ መስዋእታቸውም ሙት ነውና ሌላ አዲስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ዕብ.9:11-12 “ ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ተብሎ ተፅፏል፡፡ ጌታችን የገባባት ድንኳን የተባለችው “መስቀል” ናት፡፡ ድንኳን ያላት የዘላለም መስዋእት የሆነው የጌታ ቅዱስ ስጋ የተቆረሰው ክቡር ደሙም የፈሰሰው በመስቀሉ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚች ድንኳን “አንድ ጊዜ ፈፅሞ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገባ” በማለት ራሱን መስዋእት አድርጎ የወጣበት መስቀል መሆኑን በግልፅ አስረድቷል፡፡ “በሰው ያልተተከለች” ሲልም አይሁድ መስቀሉን ጌታን ለመግደል እንጂ መስዋእተ እግዚአብሄር ይቀርብበታል ብለው ስላልሆነ ነው፡፡ “ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች” ማለቱም በመስቀል ላይ እራሱን መስዋእት ሊያደርግ የሚችል ሰው የለም ፤ ቢኖርም እንኳ ሌላውን ራሱን ማዳን አይቻለውምና ፡ ለፍጥረት ባልሆነች ብሏታል፡፡
3. ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መስዋእትን ሊያቀርብ ይሾማልና ዕብ 8፡3 -- -- የሊቀ ካህናት ዋናው አገልግሎት መባንና መስዋእትን ማቅረብ ነው፡፡ ጌታችንም የዓለምን ሃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ የተባለበት ዮሐ1፡29 ራሱን መስዋእት አድርጎ ያቀረበ ብቸኛ ሊቀ ካህን ነው፡፡ ራሱ መስዋእት በመሆኑም ሌላ የሚያቀርበው መስዋእት አላስፈለገውም፡፡ ሁለቱንም አንድ ጊዜ መሆን ይቻለዋልና፡፡ ዕብ.9:12 “የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ዕብ.10:12 “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” እንዲል፡፡ ዕብ.9:26 “- - - አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ዕብ.8:1-3 “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው።” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ “በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን” ሲለን የትሩፋተ ስጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪ በልእልና ሃይል ባለው እሪና የተቀመጠ አስታራቂያችን ነውና ስለዚህ ተናገረ አንድም የዚህ ሁሉ ደገኛ ነገሩ ሊቀ ካህናታችን በልእልና ሃይል ባለው እሪና የኖረው መኖርን ይገልፃል፡፡ “እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” የተባለውበሰው ፈቃድ ያይደለ በእግዚአብሄር ፈቃድ በተተከለች በደብተራ መስቀል ራሱን መስዋእት ፡ መስዋእት አቅራቢውም ራሱ ደግሞም መስዋእቱንም ተቀባይ ራሱ ሆኖ ለቅዱሳን ሲያገለግል ኑሮ ነበር፡፡ የክርስቶስ መስዋእትም “ሕያው” ማለትም ለዘላለም የሚኖር ሲሆን እንደ ሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት አንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ ቶሎ የሚበላሽ ስለዚህም እለት እለት መስዋእት ማቅረብ የሚገባበት አይደለም፡፡ የቀደሙት ሊቀካህናት በሰው በተተከለችው ቅድስተ ቅዱሳን በአመት አንድ ጊዜ መስዋእትን ሊያቀርቡ እንደሚገቡ ያይደለ ለክርስቶስ ግን በእግዚአብሄር በተተከለች ደሙን ባፈሰሰባት ፡ ስጋውን በቆረሰባት ፡ ነፍሱን ካሳ አድርጎ በሰጠባት እውነተኛይቱ መቅደስና ድንኳን በተባለች በመስቀል አንድ ጊዜ ፈፅሞ ገባ ማለት ተሰቀለ፡፡ መስዋእቱን ያቀረበው ክርስቶስ የቀረበው መስዋእት የክርስቶስ ክቡር ስጋው ቅዱስ ደሙ ስለሆነ መስዋእት አቅራቢው እንደሌሎቹ ሊቀካህናት በራሱ ህፀፀ የለበትምና መስዋእቱም የሚበላሽ ፡ የሚሞት ፡ የሚበሰብስ እንደሆነው የቀደመው መስዋእት አይደለምና ነገር ግን ነገር ግን ለዘላለም የሚኖር ክርስቶስ ራሱን መስዋእት አድርጓልና የማስታረቁ ተግባር ፍፁም ነው፡፡ እርሱም ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ይህንን አንድ ጊዜ ፈፅሞ አድርጓልና፡፡ ክቡር ደሙና ቅዱስ ስጋውም ለዘላለም አምነውና በስላሴ ስም ተጠምቀው የሚመጡትን ሰወች ከሃጢአታቸው አጥቦ የዘላለም ህይወትን ሊያወራሳቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ አንድም ዘወትር (አሁንም) መስዋእትን በሰማይ ያቀርባል ካልን እለት እለት በሰማያት ክርስቶስ ወደ እውነተኛይቱ ድንኳን (መስቀል) ይወጣል ማለት ይሆንብናል (ይህም ይሰቀላል ማለታቸን ነው) - - - ደግሞም የክርስቶስ መስዋእት እንደሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት ድካም አለበት ፍፁም አይደለምና አንድ ጊዜ የሰዋው መስዋእት አልበቃውም ማለት ይሆንብናል፡፡ - - - ሌላም ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰዋው መስዋእት ሙሉውን የሰው ልጅ እዳ በደል አላቀለለም ማለት ይሆንብናል፡፡ ይህም ሊባል አይገባም ክርስቶስም አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ሰውን ሁሉ ይቅር ብሏል ፡የማስታረቅንም ተግባር ፈፅሟል በሰማያትም በአባቱም ቀኝ ተቀምጧል ይህም መቀመጡን እንጂ ለአገልግሎት መቆሙን አያሳይም፡፡ ክርስቶስም ለሃዋርያቱ እንደተናገረ ውደ አባቴ የምሄደው አሁን እንዳደረኩ ስለሃጢአታችሁ ላማልድ አይደለም ይልቁንም ልፈርድ እንጂ በማለት ማማለድን በምድር እንደፈፀመው በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጦም የሚፈርድ እርሱ እንደሆነ አስቀድሞ ተናገረን፡፡ ይህንንም ዮሐ.16:26 “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም” ብሎ አስረግጦ ተናገረ፡፡
በአጭር ቃል ጌታችን ሊቀ ካህናት ሊባል የተገባው ፍፁም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ በእውነተኛይቱ ሰው በማይገባባት ቅድስተ ቅዱሳን (መስቀል) አንድ ጊዜ ብቻ ስለገባ ፡ በእርሷም እውነተኛውን መስዋእቱን (ራሱን) ስላቀረበና ኃጢአተ ዓለምን ስላራቀ ነው፡፡ የቀደመው ክህነት ግን ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 ጌታችን ግን ክህነቱ ”ፍፁም” መሥዋዕቱም “ህያው” ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሁላችንም ኃጢአት፣ ኃጢአታችን
ይሠረይ፣ በደላችንም ይደመሰስ ዘንድ መሥዋዕትን በማቅረቡ ሊቀ ካህናት ተብሏል፡፡ ጌታችን ስለ እኛ ያቀረበው መሥዋዕት
መለኮት የተዋሐደውን የራሱን ሥጋና ደም ነው፡፡ እርሱ ኃጢአታችንን ፈጽሞ የሚያስተሠርይ በግ ሆነልን፣ ተሠዋልንም
(ዮሐ.1÷29)፡፡ #ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና እንዲል (1ኛቆሮ 5÷7)፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ
መሥዋዕት፣ ራሱ መሥዋዕት ተቀባይ የሆነ ሊቀ ካህናት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የጌታችንን ክህነት በመልከ ጸዴቅ ክህነት በመመሰል እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ
ብሎ እግዚአብሔር ማለ፤ አይፀፀትም ብሏል (መዝ.109÷4፤ ዕብ.5÷6)፡፡
-
- ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቢ፦ - መጽሐፍ ቅዱስ
- ወንጌል ትርጓሜ
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክታት ትርጓሜ
“ሁለቱ ኪዳናት” በእብራውያን መልእክት ትርጓሜ ላይ የተመሰረተ መጽሐፍ
kelehiwot yasemalen dn.melaku
ReplyDeleteKale hiwot yasemalin!beselam betena yitebikilin! Agelgilotihin yibarkilin!
ReplyDeleteጌታ ይባርክህ እየሩሳሌምን የመረጠ አማላክ ጸጋዉን ያብዛልህ፡፡ ሌላ ምን ይባላል በቅዱስ ቃሉ ስላነጽከን እናመሰግናለን እግዚአብሄር አማላካችን ያገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልን መጨረሻህንም ያሳምርልህ፡፡
ReplyDeleteጌታ ይባርክህ እየሩሳሌምን የመረጠ አማላክ ጸጋዉን ያብዛልህ፡፡ ሌላ ምን ይባላል በቅዱስ ቃሉ ስላነጽከን እናመሰግናለን እግዚአብሄር አማላካችን ያገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልን መጨረሻህንም ያሳምርልህ፡፡አሜን
ReplyDelete