Wednesday, November 14, 2012

የቤተልሔም ሕጻናት እና የራሔል እንባ


« እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክየይ ፤ ለሥራሽ ፤ ዋጋ ይሆናልና ፥ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ ፥ ይላል እግዚአብሔር ፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸዎ ይመለሳሉ። » ኤር ፴፮ ፥፲፭ ፡፡

የቤተልሔም ህጻናት በግፍ ሲገደሉ
ቅዱሳን ነቢያት የሚናገሩት ስለ ዘመናቸው ብቻ አይደለም ፤ ከዘመናቸው ጋር በማገናዘብ ስላለፈው ይናገራሉ ፥ ስለሚመጣውም ይተነብያሉ። ዓረፍተ ዘመን ሳይገታቸው ኃላፊያትንም መጻእያትንም ይተረጉማሉ። በመሆኑም ይህ ቃለ ኤርምያስ ወደኋላም ወደፊትም የሚሠራ ነው። ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ የባርነት ዘመን የነበሩበትን ዘመን ያስታውሳል ፥ ለፍጻሜው ደግሞ በዘመነ ሥጋዌ መባቻ ማለትም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የተፈጸመውን ያሳያል።

የራሔል እንባ እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ የባርነት ዘመን የነበሩበትን ዘመን ያስታውሳል

  እስራኤል በባዕድ ሀገር በግብፅ በዮሴፍ ስም ተወደው ተከብረው ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ዮሴፍን የማያውቅ ፥ አንድም ደግነቱን ጥበቡን የማያውቅለት ንጉሥ ተነሥቶ ቀንበር አጠበቀባቸው። ይኸውም፦ የእሥራኤል ልጆች ፈጽመው በዝተዋል ፥ ከእኛም እነሱ ይጸናሉ ፥ ስለዚህ ወደፊት ጠላት ቢነሣብን ከእነርሱ ወገን ተሰልፈው ይወጉናል ፥ አንድም ከበዙ ዘንድ አገራችንን ያስለቅቁናል። ብሎ ገና ለገና በመፍራት ፈሪ ሰው ጨካኝ በመሆኑም፦ « ኑ ብልሃት እንሥራባቸው ፤ ጡብ እናስጥላቸው ፥ ኖራ እናስወቅጣቸው ፥ ጭቃ እናስረግጣቸው ፤ ይህን ሲያደርጉ ከዋሉ ልሙዳነ ፀብእ አይሆኑም ፥ አንድም ከድካም ብዛት ከሚስቶቻቸው አይደርሱም ፥ ካልደረሱም አይባዙም ፥ ካልበዙም አኛን አያጠፉም ፤ » አለ። ይኽንንም ብሎ አልቀረም። በብዙ ማስጨነቅ ፌቶም ፥ ራምሴንና ዖን የተባሉ ጽኑ ከተሞችን በግንብ አሠራቸው። 
                    የእስራኤላውያን ባርነት በግብጽ

እስራኤል ዘሥጋ መከራ የሚያጸኑባቸውን ያህል እንደ መከራው ብዛት  እየበዙ ይጸኑ ነበር። ግብጻውያን ግን የእሥራኤልን ልጆች ያስመርሯቸው ፥ እየገፉ እያዳፉ በግፍዕ ይገዟቸው ነበር፡፡ በሕይወት መኖርን በሚያሰቅቅ ሥራ ሰውነታቸውን ያስጨንቋት ነበር።

ከዚህም ሌላ ንጉሡ ዓቀብተ መወልዳትን ( አዋላጆችን ) ሾሞባቸዋል፡፡ እነርሱንም « ዕብራውያትን ሴቶች ስታዋልዱ ለመውለድ እንደደረሱ በአያችሁ ጊዜ ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት ፤ ሴት ብትሆን ግን አትግደሏት ፤ » አላቸው። እነርሱ ግን እግዚአ ብሔርን ፈርተው እንዳዘዛቸው አላደረጉም። ንጉሡም ጠርጥሮ አንድም ከነገረ ሰሪ ሰምቶ ፦ « ለምን ያዘዝኳችሁን አልፈጸማችሁም ? » ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ምክንያቱም ወንድ ልጅ ተወልዶ ከሦስት ወር በኋላ ሲያለቅስ ፥ ሲያነጥስ በድምጹ ይታወቃልና ነው።  ሴቶች ምክንያት አያጡምና ( ብልሆች ናቸውና )፦ « የዕብራ ውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም ፥ አዋላጅቱ ሳትመጣ ወልደው ይቆያሉ ፤ » ብለው መለሱለት። እነርሱ ለእስራኤል በጐ ነገር በማድረጋቸው ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱም በጐ አደረገላቸው ፤ ንጉሡ እንዳይገድላቸው አደረገ። ( የንጉሥ ትእዛዝ መተላለፍ ያስገድላልና )።

 ከፍ ብሎ በእግዚአብሔር ቸርነት ፥ ዝቅ ብሎ በአዋላጆች ደግነት እሥራኤል እጅግ በዝተው በረቱ። ያንጊዜም ፈርዖን ተቆጥቶ « ከዕብራውያን የሚወለደውን ወንድ ወንዱን ከፈሳሽ ውኃ ጣሏቸው ፥ ሴት ሴቱን ግን በሕይወት ተዉአቸው ፤ » የሚል አዋጅ አናገረባቸው። 

የእንባ ሰው ራሔል የነበረችው በዚህ ዘመን ነው። ሮቤልም ስምዖንም የሚባል ባል ሞቶባት ሐዘንተኛ ነበረች። እርሱ ሲሞት ነፍሰ ጡር ብትሆንም « በእርሱ ምትክ ኖራ ውቀጪ ፥ ጭቃ ርገጪ፤ » ተባለች። መንታ ፀንሳ ኑሮ ደም ፈሰሳት ሕፃናቱም ወጥተው ፥ ወጥተው ፥ ከጭቃው ወደቁ ። ደንግጣ ብትቆም ፥ ምን ያስደነግጥሻል ? የሰው ደም ፥ የሰው ሥጋ ጭቃውን ያጸናዋል እንጂ ምን ይለዋል ብለሽ ነው? ርገጪው ፤ » አሏት ፡፡ በዚህን ጊዜ ነው ፥ « ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እሥራኤል ፤ በውኑ በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን ?» ብላ እንባዋን ያፈሰሰችው። ይኽንንም እንባ በእፍኟ እየሰፈረች ወደ ላይ ረጨችው። «እንደገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤» እንዲል ፤ ኢሳ ፳፭ ፥ ፰ ፤ እንባን የሚያብስ እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ ታምናለችና።

 እንባዋ ወደ ምድር አልተመለሰም ፥ ከመንበረ ጸባዖት ደረሰ እንጂ ። « ወዐበየት ተናዝዞ ወነጊፈ ላህ ፤ ልቅሶ መተውን መጽናናትን እንቢ አለች።» ምክንያቱም ግፉ ያሳዝናልና ፥ የሕፃናቱ ሞት የፃር ነውና ፥ ሐዘን በየደጁ ኹኗልና፡፡ « እስመ ኢኮንዋ ውሉዳ ውሉደ ፤ ልጆቿ ልጆች አልሆኗትምና ፥» ሙተዋልና ፥ ባሌ ቢሞት በልጆቼ እጽናናለሁ። ያለችው ከንቱ ኹኖባታልና ። « ወኢሀለዉ በሕይወተ ሥጋ የለምና ፤» መጽናናትን እንቢ አለች፡፡ ይኽንን ነው ፥ ነቢዩ ኤርምያስ « የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ » ያለው።
የራሔል እንባ እግዚአብሔር እንዲናገር ፥ በረድኤትም እንዲወርድ አድርጐታል። « ሰማዕኩ ገዓሮሙ ለሕዝብየ ፥ ወወረድኩ ከመ አድኅኖሙ ፤ የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ ፥ ላድናቸውም ወረድኩ » አሰኝቶታል። « እግዚአብሔርም ሙሴን በግብፅ ያሉ የወገኖቼን መከራ አይቼ ፥ በሠራተኞች የተሾሙ ሹማምንት ካመጡባቸው መከራ የተነሣ ጩኸታቸውን ሰምቼ ፥ መጨነቃቸውን አውቄላቸዋለሁ። ከግብጻውያን እጅ አድናቸው ፥ ወደ ተወደደችም ሰፊ ወደምትሆን ወደ ከነዓንም እወስዳቸው ዘንድ ወረድኩ። ከግብፅም አውጥቼ ማርና ወተት ወደሚጐርፍባት ፥ ተድላ ደስታ ወደማይታጣባት አገር እወስዳቸዋለሁ ፤ » አለ። ማር ያለው ሕገ ኦሪትን ነው ፥ ማር የነካው ጨርቅ በውኃ ቢያጥቡት ፈጥኖ እንዲለቅ ሕገ ኦሪትም የሚለቅ ሕግ ነበርና። ወተት ያለው ደግሞ ሕገ ወንጌልን ነው። ወተት (ቅቤ) የነካው ጨርቅ በውኃ ቢያጥቡት እንደማይለቅ ሕገ ወንጌልም የማትለቅ ( ጸንታ የምትኖር ) ሕግ ናትና ። ዘጸ ፫ ፥ ፰ ፡፡

የራሔል እንባ በዘመነ ሥጋዌ መባቻ ማለትም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የተፈጸመውን ያሳያል
  በአዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታ በተወለደ ጊዜ የአይሁድ ንጉሥ የነበረ ሄሮድስን በግብር ፈርዖንን መስሎ እናገኘዋለን ፡፡ የሩቆቹ ወርቅ ዕጣንና ከርቤ ይዘው ፥ በኮከብ እየተመሩ ሁለት ዓመት ተጉዘው ሲመጡ የቅርቡ ሄሮድስ ግን ዜና ልደቱ አስደነገጠው ። ጥያቄያቸው ፦ « አይቴ ሀሎ ንጉሥ ዘተወልደ ፤ የተወለደው ንጉሥ ወዴት ነው ? » የሚል ነበርና ። ዓለም የሥልጣን ነገር ያሳስበዋል ፥ የደነገጠ አውሬም ያደርገዋል ። የደነገጠ አውሬ ማንንም እንደማይምር ዓለምም እንዲሁ ነው።
     ሄሮድስ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከሰብአ ሰገል በጥንቃቄ ከተረዳ በኋላ በልቡ ፦ «ለካ ያ ብላቴና ሁለት ዓመት ሆኖታል ፤» አለ። ካህናቱን በስውር ጠርቶ በተረዳውም መሠረት « ቤተልሔም ነው፤ » ብሎ ሰደዳቸው። ከዚህም ጋር ፦ « ሄዳችሁ የብላቴናውን  ነገር ጠይቃችሁ እርሱን ያገኛችሁት እንደሆነ እኔም እንድሰግድለት በእኔ በኲል ተመልሳችሁ ንገሩኝ፤ » አላቸው፡፡ እርሱ በሽንገላ ቢናገረውም ነገሩ ጥበበ እግዚአብሔር ነው። ሰብአ ሰገል፦ « ለካስ የሀገሩም ነገሥታት ያምኑበታልሳ ፤ » በሚል ሃይማኖታቸው እንዲጸናላቸው ነው ።
     ሰብአ ሰገል ግን ሳጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ እጣን ከርቤ ለሕፃኑ ከገበሩለት በኋላ መልአኩ እንደነገራቸው በሌላ ጐዳና ፥ በሌላ ኃይለ ቃል ፥ በሌላ ሃይማኖት ተመልሰዋል ። በሌላ ጐዳና ሁለት ዓመት የተጓዙትን በአርባ ቀን ገብተዋል፡፡ በሌላ ኃይለ ቃል « ወዴት ነው?» እያሉ መጥተው ነበር ፥ « አገኘነው ፤ » እያሉ ተመልሰዋል፡፡ በሌላ ሃይማኖት « ምድራዊ ንጉሥ ፤» እያሉ መጥተው ነበር ፥ ሰማያዊ ንጉሥ ፥ የባሕርይ አምላክ » እያሉ ተመልሰዋል።
     ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደዘበቱበት  ( ባንተ በኩል እንመለሳለን ብለው በሌላ ጐዳና እንደሄዱ ) በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ተበሳጨ። ጭፍራዎቹን ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደተረዳው ዘመን ልክ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ፥ ከዚያም የሚያንሱትን  ፥ በቤተልሔምና በአውራጃዎችዋ ሁሉ የነበሩትን አሥራ አራት እልፍ ሕፃናት አስገደለ። ያን ጊዜ ፦ በነቢዩ በኤርምያስ ፦ « ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ ተሰማ ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች ፤ ልጆቿ የሉምና። » የተባለው ተፈጸመ ፥ ይላል።
     የቤተልሔም ህጻናት በግፍ ሲገደሉ

ራሔልን አነሣ እንጂ ልያን አላነሣትም። ምክንያቱም ;-
1-     ጌታ የተወለደው ከልያ ወገን ስለተወለደ ዕዳዋ ነው። ራሔል ግን ከእርሷ ወገን ስላልተወለደ ያለ ዕዳዋ ነው።
2-    የልያ በርኅቀተ ሀገር በብዛት ድነውላታል ፤ የራሔል ግን በማነስ በቅርበት አልቀውባታልና ነው።
3-    አንድም በራሔል የልያንም መናገር ነው።
4-   አንድም « እናታችን ራሔል ኑራልን ፥ መከራችንን አይታልን ባለቀሰችልን ፣» ብለው ስላለቀሱ ነው።
5-   አንድም እንድናለን መስሏቸው ከመቃብረ ራሔል ገብተዋል ፥ ከዚያም ተከትለው ገብተው ልጆቻቸውን ከእቅፋቸዋ ነጥቀው ፥ አንገታቸውን ጠምዘው አርደውባቸዋል። በዚህን ጊዜ አፅመ ራሔል አንብቷል።  የራሔል መቃብር ከቤተልሔም አንድ ኪ.ሜ. ይርቃል።
      በሌላ በኲል ደግሞ ከልያም ከራሔልም ወገን የተወለዱትን ሊያገናኝ የሚችለውን አባታቸውን ያዕቆብን አላነሣም። ያነሣው እናታቸውን ራሔልን ነው። ምክንያቱም፦ ወንድ ልጅ ለአቅም አዳም ፥ ሴት ልጅ ለአቅመ ሔዋን ደርሰው የሞቱ እንደሆነ ኀዘን በአባት ይጸናል። በሕፃንነት ዘመን የሞቱ እንደሆነ ግን ኀዘን በእናት ይጸናልና ለዚህ ነው ።
          ቅዱስ ማቴዎስ « ራሔል » ብሎ ትንቢተ ኤርምያስን የጠቀሰው ለዚህች ብቻ ሳይሆን በግብፅ ለነበረችውም ነው። ይኸውም ግፍን ከግፍ ሲያነፃፅር ነው።

እነዚህን ሁሉ ሕፃናት እንዴት አድርጎ ሰበሰባቸው?
   ሄሮድስ አሥራ አራት እልፍ ሕፃናት የሰበሰበው « ንጉሡ ቄሣር ፦  ሕፃናትን ሰብስበህ ፥ ልብስ ምግብ እየሰጠህ ፥ በማር በወተት አሳድገህ ፥ ለወላጆቻቸው ርስት ጉልት እየሰጠህ ጭፍራ ሥራልኝ ብሎኛል፤ » የሚል አዋጅ አናግሮ በጥበብ ነው። ያላቸው ልጆቻቸውን፥ የሌላቸው ደግሞ ልብስ ምግብ ልቀበልበት ብለው እየተዋሱ ሄደዋል። እንዲህ አድርጎ ሰብስቦ ፈጅቷቸዋል። ለሁለቱም የግፍ ታሪኮች «የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ፤» የተባለው በመላእክት ዘንድ ተሰማ ፥ ማለት ነው። ምክንያቱም ኢዮር ፥ ራማ ፥ ኤረር ዓለመ መላእክት ናቸውና። አንድም በመላእክት ፈጣሪ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰማ ማለት ነው። ምክንያቱም መላእክት ባሉበት እግዚአብሔር አለ። አንድም ራማ የተባለች መንግሥተ ሰማያት ናት። ምሥጢራዊ ትርጉሙም ሃይማኖት ይዞ ምግባር ሠርቶ የሚገባባት አጥታ ታዝናለች ፥ ታለቅሳለች ማለት ነው።
የራሄል መቃብር ኢየሩሳሌም
በዚህ ዘመን የሚያስፈልገው ሌላ ነገር ሳይሆን ይህ የራሔል እንባ ነው። ዓለም በግፍ ተከድናለችና ፥ ነፃ ሰው የለምና። «ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ ፥ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም። እግዚአብሔርን የሚፈልግ አስተዋይ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ ፤ አንድ ስንኳ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም፡፡ ሕዝቤን እንጀራን እንደ መብላት የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁም ፥ እግዚአብሔርን አይጠሩትም።» እንዲል፡፡ መዝ ፶፪ ፥ ፩-፬ ።

እመቤታችን ቅድሰት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ እና ከዮሴፍ ጋር በመሆን በግብጽ በስደተኛነት ስለኖሩበት ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሃንስ በራዕዩ እንዳየው እንዲህ ይላል ጸሃይን የለበሰች ጨረቃን ከእግሮቿ በታች የረገጠችና በራሷም ላይ ዘውድ የደፋች አንዲት  ሴት ታየች;አየሁም ሰባት ራሶች አስር ቀንዶች ያሉት ታላቅ ቀይ ዘንዶ ልጇን ለመብላት በወለደችው በዚህች ሴት ፊት ቆመ፡፡ እነሆ ሴቲቱም አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀናት ያህል ይመግብዋት ዘንድ በእግዚአብሄር ተዘጋጅቶላት ወደነበረው ስፍራ ወደ በርሃ ሸሸች፡፡” (ራዕ 121-6)
ሴቲቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፣ ዘንዶው በንጉስ ሄሮድስ ላይ አድሮ ሕጻኑን ለመግደል የፈልገውና ያሳደደው ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ነው ፡፡ 
ህጻኑን እና እናቱን ይዘህ ወደግብጽ ሽሽ
እንግዲህ እመቤታችን ቅድሰት ድንግል ማርያም ከልጅዋ ከዮሴፍ እና ከሰሎሜ ጋር በግብጽ በረሃ ቆየችባቸው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀናት ( ሶስት ዓመት ከስድስት ወር )  እጅግ ብዙ ተአምራት እንደተፈጸመ ሁሉ ድንግል ማርያም ከሕጻኑ ጋራ ብዙ መከራና ስቃይን ተቀብላለች፡፡ ስለልጇም እንባዋ እንደ ጅረት ፈሷል፡፡ከቤተክርስቲያናችን ታሪክ እንደምንረዳውና እንደተማርነው እመቤታችን ቅድሰት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ እና ከዮሴፍ እና ሶሎሜ ጋር በመሆን በግብጽ በስደተኛነት በቆየችባቸው ጊዜያት ብዙ ተአምራትም ተሰርተዋል፡፡ የልጇም ሁሉን ቻይነት(ኤልሻዳይነት) ታይቷል፡፡ 
በመጨረሻም የህጻኑን ነፍስ ሲፈልግ የነበረው ንጉስ ሄሮድስ በመሞቱ ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው ወደ ናዝሬት እንዲመለሱ የእግዚአብሄር መልአክ ለዮሴፍ በህልሙ ተገልጾ ሕጻኑን እና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ ህጻኑን ሊገድለው የሚፈልጉት ሞተዋልና አለው፡፡ ዮሴፍም ሕጻኑን እና እናቱን ይዞ ተመለሰ፡፡ (ማቴ 219)
እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ስደተኞቹ እመቤታችንና ጌታችን እንዲሁም ዮሴፍ ከስደት ሲመለሱኅዳር 6 ቀን ደብረ ቍስቋም ከሚባለው ተራራማ ቦታ እረፍት አድረገዋል፡፡  በየአመቱ የእመቤታችንን እና የጌታችንን የዮሴፍንም ስደት መታሰቢያ በአል ኅዳር 6 ቀን ታከብራለች፡፡ ከስደቱም 10 ዓመት በኋላ አባታችን ቅዱስ ዮሴፍ አርፏል፡፡ 

«ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ ፤
ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ››
ቅዳሴ ማርያም

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት፤ ፍቅርና አማላጅነት 
                       በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር፡፡

ዋቢ
 Ø መጽሐፍ ቅዱስ
 Ø ወንጌል ትርጓሜ
 Ø ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ
 Ø ቤተደጀኔ ድረ ገጽ

8 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን፣
    በሀይማኖት ፀንተህ እንድትኖር አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡
    አምላካችን ፀጋውን ያብዛልህ፡፡ የቅድስት እናታችን እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት፤ ፍቅርና አማላጅነት
    አይለይህ፡፡
    እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. ቃለ ህይወት ያሰማልን፣
      ይህን መንገድ ያስመለከተህ ዓምላክ በሀይማኖት ፀንተህ እንድትኖር አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡
      አምላካችን ፀጋውን ያብዛልህ፡፡ የቅድስት እናታችን እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት፤ ፍቅርና አማላጅነት
      አይለይህ፡፡ በርታ!
      እግዚአብሔር ይመስገን፡፡


      Delete
  2. በጣም የሚደንቅ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት

    ReplyDelete
  3. Kale hiwot yasemalin. Egziabher beselam betena yitebikilin!

    ReplyDelete
  4. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  6. Dn, It is really deeply touching and in depth article. Keep it up, never forget your blessing by God to serve us. Keep on being very polite and pray so that your ending is much better than your beginning. Remember those with various blessings from God, but fail by the various plots of the devil so that you always pray and fast to get more blessings and protection from God. Redeate Egzeabhere kant gar yehun, Amen.

    ReplyDelete
  7. Kala heiwot yasamalen

    ReplyDelete