በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት አሥራ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተኰርዖት›› የሚለው ቃል ኩርዐ - መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ርእስ ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ
27-24፤ ማር
15-15፤ ሉቃ
23-25፤ ዮሐ
18-39)፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው ራሱ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር
15-19)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾህ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የሆነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ ተንኮል የተጐነጐነ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡
2. ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተፀፍዖ›› የሚለው ቃል ፀፍዐ በጥፊ መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ መልታሕት ደግሞ ፊት ጉንጭ ማለት ነው፡፡
ጌታችን ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቆጥሮበት መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡ በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ
27-27)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ
19-2-4)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡
3. ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)
ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው የክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ሁኔታ ምራቃቸውን እንደተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ወሪቅ›› የሚለው ቃል ወረቀ ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም እንትፍ አለ፣ (ተፋ) ማለት ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ (ምዕራፍ 5ዐ-6)
‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደተነገረ እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት (ማቴ
27-29-3ዐ፤ ማር
15-19)፡፡ በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የሆነውን ምራቅ ተቀበለ፡፡
4. ሰትየ ሐሞት (መራራ ሐሞት መጠጣት)
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ሰተየ›› ማለት ጠጣ ማለት ነው፡፡ ሐሞት የሚለውም አሞት ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ በመዝሙር 68
ቁጥር 21 ላይ ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ሆምጣጤ ተሞልቶበት ተቀምጦ ከነበረው ዕቃ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ
27-34)፡፡ ጌታችንም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ (ማቴ
27-48፤ ማር
15-36፤ ሉቃ
23-36፤ ዮሐ
19-29)፡፡
ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃ ምንጭ የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ
55-1)፡፡ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ኳትነው ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከአለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ
16-1-2ዐ፤ 1ቆሮ 1ዐ-3)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ሁሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ሆምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡
5. ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተቀሥፎ›› የሚለው ቃል ቀሠፈ - ገረፈ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ዘባን›› ደግሞ ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጠው የተገረፈ አይሰቀልም፡፡ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ጲላጣስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገረፈው፡፡ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብሎ ከታጠበ በኋላ ክርስቶስን ያለ ኃጢአቱ በመግረፍ ለአይሁድም አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ
27-28፤ ማር
15-15፤ ዮሐ19-1)፡፡
መድኃኒታችን መንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጣስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይሆን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወህኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ››
(በኢሳ 5ዐ-6)
ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡
6. ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተዐርቆተ›› ማለት ታረዘ፤ ተራቆተ ማለት ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የጸጋ ሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡
የሲኦል ወታደሮች የሆኑት አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ በሰጣቸው ሰዓት ወታደሮች ልብሱን ገፍፈውታል (ማቴ
27-27)፡፡ የሰው ልጅ ለቀረበለት ምርጫ የሰው ምላሽ ዘራፊው፤ ገራፊው ወንበዴ በርባን እንዲፈታለት ነበር፡፡ ‹‹አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ ፣ ደይ እዴከ ኅበ ዘፈቀድከ! እነሆ እሳትና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፣ እጅህን ወደ ፈቀድከው ስደድ›› ሲባል የሰው ልጅ እጁን ወደ እሳት ሰደደ፡፡
7. ርግዘተ ገቦ (ጎንን መወጋት)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር መወጋቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ርግዘት›› የሚለው ቃል ረገዘ- ወጋ ከተሰኘ የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ገቦ ማለት ደግሞ ጎን ማለት ነው፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አጠገብ፣ በግራና በቀኙ ሁለት ወንበዴዎች ተሰቅለው ነበር፡፡ ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር ጭናቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ አይሁድ ጲላጦስን በለመኑት መሠረት ጭፍሮቹ የሁለቱን ወንበዴዎች ጭን ጭናቸውን ከሰበሩ በኋላ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ፈጽሞ እንደሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፡፡ ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ (ዮሐ
19-33)፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በሆነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለጣለው ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?››
ተባለ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት ነበርና (1ቆሮ
15-54-55፤ ኢሳ
25-8፤ ሆሴ
13-14)፡፡
ከተወጋው የጌታችን ጎን ደምና ውኃ መፍሰሱም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛልና (ዮሐ
3-5፤ ዮሐ
6-54)፡፡
8. ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተአሥሮት›› የሚለው ቃል አሠረ (ሲነበብ ይላላል) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አሠረ ማለት ነው፡፡ ‹‹ድኅሪት›› የሚለው ቃል ደግሞ ተድኅረ- ወደኋላ አለ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለትና ሰዓት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል፡፡ አፍገምግመውታል (ዮሐ
18-12)፡፡
በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡
9. አምሥቱ ቅንዋተ መስቀል
መድኃኒታችን በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ቅንዋት›› የሚለው ቃል ቀነወ- ቸነከረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ መስቀል ማለት ደግሞ ዝም ብሎ የቆመ ግንድ ሳይሆን አሁን በየሥፍራው እንደምናየው ምልክት የተመሳቀለ እንጨት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረባቸው አምስቱ ችንካሮች ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ ይባላሉ፡፡ እነዚህም የአምሥቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መሆናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡
ሐዋርያው ቶማስ ከትንሣኤ በኋላ ወንድሞቹ ሐዋርያት ስለ ትንሣኤው በነገሩት ጊዜ ‹‹የችንካሩን ምልክት በዓይኖቼ ካላየሁ፣ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላስገሁ፣ በእጄም የተወጋውን ጎኑን ካልዳሰስኩ አላምንም›› ማለቱ በብረት ቀኖት በመቸንከሩ ነበር (ዮሐ 2ዐ-25)፡፡ መድኃኒታችን በኃጢአት ቀኖት (ምስማር) ተይዞ የነበረውን ሰው ለማዳን በብረት ቀኖት ተቸነከረ፡፡
እንግዲህ አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የሚባሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ድሀ ያይደለ ጌታ፤ ፍጡር ያይደለ የፈጠረውን ሥጋ ገንዘብ ያደረገ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ብሎ ተናቀ፡፡ የሕማም ሰው፤ ደዌንም የሚያውቅ ሆነ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፡፡ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ይህም የሰውን ልጅ ለማዳን ማለትም እኛን ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰንና ከሕማመ ሥጋ ከሕማመ ነፍስ ሥቃይ ያሳርፈን ዘንድ ነው፡፡ ቁስለ ኃጢአታችንን ያደርቅልን ዘንድ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፡፡ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ስለ በደላችን ደቀቀ፡፡ ሊያረጋጋን ተጨነቀ፡፡ ሊያሣርፈን ተሠቃየ፡፡ አፉንም አልከፈተም፡፡
የእግዚአብሔር የመሥዋዕቱ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ መልካምን እንጂ ግፍን አላደረገም ነበር፡፡ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ወሰብእ ወልድ ዋህድ ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ በተመረመረ ጊዜ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም፡፡ በፈቃዱ ነፍሱን ስለ እኛ መሥዋእት አደረገ፡፡ ፋሲካችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሥጋውን ቆረሰልን፣ ደሙንም አፈሰሰልን (ኢሳ.
53-1-13፤ ዮሐ.
10-18፤ ዮሐ.
19-30፤ 1ኛቆሮ.
5-7)፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈረደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡›› ለኃጢአት ሞትን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን ተሸከመ፡፡ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ ብሏል (1ጴጥ.22-2-25)፡፡ ክርስቶስ የሞተልን ለጽድቅ ሞተን ለኃጢአት እንድንኖር አልነበረም፤ የኃጢአት ኑሮ እንዲያከትምልን እንጂ፡፡
እንግዲህ የእኛ ሕያውነትስ ለጽድቅ ይሆን ወይስ ለኃጢአት ዛሬ ሕይወታችንን መለስ ብለን ልናጤነው ሥጋዊ ፍላጎታችንንና የዓይን አምሮታችንን ክደን ነፍሳችንን ለማዳን መከራ መስቀሉን ተሸክመን ሕማማቱን እያሰብን ፈጣሪአችን ክርስቶስን ልንከተለው ይገባን ነበር (ማቴ.16-24)፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትምክህታችን መስቀሉ ማለትም በመስቀሉ ላይ የተፈፀመው ቤዛነት መሆን አለበት፡፡
ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም ያድርሰን
ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም ያድርሰን
Amen, Kale Hiwot Yasemalen.
ReplyDeletedn kale hiwot yasemalen be'dme betsega ytebkln!!!
ReplyDeleteGOD bless you Mele! Kale Hiwot Yasemalin. Libona yisten Medhanialem!
ReplyDeleteamen
ReplyDeleteAmen! KHY
ReplyDeleteDn, you mentioned only nine
He listed 1 through 9 but it consists of 13. Have a look @ number 9. "Amstu Kinwate Meskel"
DeleteKalehiywote yasmalen
ReplyDeleteዲ,መላኩ ;
ReplyDeleteበእዉነቱ መልካም ትምህርት ነዉ::
እግዚአብሔር በረከቱን ያብዛልህ::
ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም ያድርሰን
ReplyDeleteAmen!
Amen!
Amen!
13/04/2012 @ 10:55AM
ዲ,መላኩ ;
ReplyDeleteበእዉነቱ መልካም ትምህርት ነዉ::
እግዚአብሔር በረከቱን ያብዛልህ:: አሜን ያብዛልህ::
God bless u! please prepare Pdf
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡
ReplyDeleteአሜን !
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን!
አሜን !
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን አንተንም በሰላም ለትንሳኤው ያድርስህ !
amennnnnnn
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን አንተንም በሰላም ለትንሳኤው ያድርስህ !
ReplyDeletePlease your foto is not important on your websight .One preacher is good with
ReplyDeletetraditional cloth not with necktie.
መልካም ትምህርት ነው!!!
ReplyDeleteጌታችን አምላካችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና ስለ እኛ ብሎ በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ አስራ አምስት ምእራፎችን አልፏል ከሶስት ጊዜ በላይ መስቀል ተሸክሞ ወድቋል ስለዚህም ዘርዘር ብሎ ቢፃፍልን መልካም ነው እላለሁ!!!
መንግስተ-ሰማያትን ያውርስልን ።
ReplyDeleteበቅድሜያ ለዚሕ ድሕረገጽ ተከታታዬች እንኮን ለዝች ቀን ደረሳቾሁ፤ አደረሰን እላለሁ።
ReplyDelete14 stations from jerusalem: http// youtu.be/
ZN3DQQtfRBw
ግዚ ሴኖር እንመለከት። ዳ/ ን መላኩ በዚሕ የከፋ ግዚ አሉን ከሜባሉት ቤተክርስቴያናችን ኮትኩታ ካሳደገቻቸው ልጆች አንዱ መሆኑን አንርሳ። በተገኘው አጋጣሜ ልናበረታታ ይገባል። እንዲያው በዘፈቀደ ባንተች መልካም ነው።