Tuesday, April 22, 2014

ዘመነ ትንሳኤ ( የትንሳኤ ሳምንት)

«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡

- መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
«ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
«ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡

1)    አንደኛው «ትንሣኤ» ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡
2)    ሁለተኛውም «ትንሣኤ» ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
3)    ሦስተኛው «ትንሣኤ» ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡
4)    አራተኛው «ትንሣኤ» የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡ 
5)    ዐምስተኛውና የመጨረሻው «የትንሣኤ» ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «ትንሣኤ» መሠረት ያደረገ «ትንሣኤ ዘጉባኤ» ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡

ወደተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ «ፋሲካ» ተብሎ ይጠራል፡፡
         
«ፋሲካ» ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ በግሪክኛው «ስኻ» ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል «ትንሣኤ» ተተክቶበታል፡፡
ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ
  • ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣
  • ከኃሳር ከውርደት ወደክብር፣
  • ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣
  • ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡
  •  
- ክርስቲያኖች የትንሣኤን በዓል በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት ያከብሩታል፡፡ ስለዚህም ከበዓላት ሁሉ የበለጠ ሆኖ ይታያል፡፡
- መድኀኒታችን ሞትን በሞቱ ድል መትቶ፣ ስሙና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት 29 ቀን 34 . እንደሆነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡
- የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡት ተከታዮቹ ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀነስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡
«እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን»
ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታት ሰሙነ ፋሲካ ወይም ትንሣኤ እየተባሉ የየራሳቸው ምስጢራዊ ስያሜ አላቸው፡፡ ይኸውም፡-
ሰኞ
 ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሆና «ፀአተ ሲኦል ማዕዶት» ትባላለች፡፡ ዮሐ. 19-18 ሮሜ. 5-10-17 የዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ግን ገበሬው፤ ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ሁሉ ሴቶቹ ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለሆነች «እጅ ማሟሻ» ሰኞ ትባላለች፡፡

 ማክሰኞ
 የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ሐዋርያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት እኔ ሳላይ አላምንም በማለቱ በዚህ ጥያቄው መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ ሆና ዕለቲቱ «በቶማስ» ተሰየመች፡፡ ዮሐ. 20-24-30
 ረቡዕ
 ከሞተና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣው፣ አላዓዛር መታሰቢያ የእርሱንም ተነሥቶ በማየት በጌታችን ብዙ ሕዝብ ስለአመነበት ቀኒቱ «አልዓዛር» ተብላ ትታሰባለች፡፡ ዮሐ. 11-38-46

ኃሙስ
 የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና «የአዳም ኀሙስ» ተብላ ይኸው ትከበራለች፡፡ ሉቃ. 24-25-49

ዐርብ
 በክርስቶስ ደም ተዋጅታ በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ በመሆኗ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ዐርብ «ቤተ ክርስቲያን» ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ. 26-26-29 የሐ. ሥራ. 20-28 ይህች ዕለትም እንደ ዕለተ ኀሙስ ሦስት ስያሜዎች አሏት፡፡ ይኸውም እንደኛው ከሆሳዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን አርባው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት፣ በመሆኗ በቤተ ክርስተያን «ተጽዒኖ» ስትባል በሕዝቡም ዘንድ በሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤው ከባዱን ሥራ ስለሚያቆምባት «የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ» ትባላለች፡፡
- ሁለተኛውም በመጀመሪያ የሰው አባትና እናት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፣ ኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም መከራ ተቀብሎ ስለተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለፈጸመባት «ዕለተ ስቅለት አማናዊቷ ዐርብ» ትባላለች፡፡
- ሦስተኛውም ይኸው በሰሙነ ትንሣኤው ያለችው ደግሞ «ቤተ ክርስቲያን» ትባላለች ማለት ነው፡፡

ቀዳሚት
 በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበይባት «የቁራ ገበያ» የገበያ ጥፊያ ስትባል በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ለአገለገሉት በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ የትንሣኤው ዕለት ገና ከሌሊቱ ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው በመገሥገሣቸው ትንሣኤው ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መልካም መታሰቢያ ሆና «አንስት» ተብላ ትጠራለች፡፡ ሉቃ. 23-27-33 24-1-01 ማቴ. 25-1-11
የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ...« ዳግም ትንሣኤ »
በዚች ሰንበት ከላይ እንደተጠቆመው የትንሣኤው ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ በር ገብቶ በመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎም ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ የጌታችንን መነሣትና እንደተገለጸላቸው በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ዐየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን «ሰምቼአለሁ» ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ ምክንያቱን ለይቶ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኀኔዓለም ክርስቶስ ልክ እንደመጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ «ሰላም ለሁላችን ይሁን» በማለት በመካከላቸው ቆመ፤ ቶማስንም «ያመንክ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ» ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደፍላጎቱ በመረዳቱ «ጌታዬ አምላኬ ብሎ መስክሮ» አመነ፡፡
- እንግዲህ ይህ የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ «ዳግም ትንሣኤ» ተብሎ ሰንበቱ ይጠራበታል፤ ይከበርበታል፡፡ ዮሐ. 20-24-30

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


2 comments:

  1. ቃለ ሔይወት ያሰማልን! አግዚአቢሔር በወደደ ይሕን ግሩም ትምሕርተ ወንጌል ፤ ጀማሪ ሳትሆን ጨራሽ እንድትሆን የድንግል ልጅ አይለይሕ ። በርታ!

    ReplyDelete
  2. Lij Melaku endemin senebetk?. Silemigbu ejig enameseginalen. Kale hiwot yasemalin.

    ReplyDelete