Friday, July 20, 2012

ቤተክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች ? ክፍል 3



በማቴዎስ 09¸ 06-2 እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብሎ ለጠየቀው ኦሪታዊ ባለጸጋ እንኳ የሙሴን ትእዛዝ እንዲጠብቅ አዘዘው፡፡ ፍጹም እንዲሆን ቢፈልግ ርግጥ በትሩፋት ላይ ትሩፋት ለመጨመር ቢፈልግ ሀብቱን ለነዳያን ሰጥቶ እሱን ቢከተለ የሚሻለው መሆኑን አልሰወረም፡፡ እነሱ የሚጠቅሱትን ሙሴም ስለርሱ የጻፈ ስለርሱ የተነበየ መሆኑን ነግሯቸዋል፡፡ በፖለቲካም ለቄሣር ግብር አትስጡ ብሎ ሕዝቡን ያሳምጻል ተብሎ ከመከሰሱ በፊት “ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል ወይስ አይገባም?" ብለው በተንኮል ቢጠይቁት “የመንግሥታችሁን ለመንግሥታችሁ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏቸዋል፡፡
 እንደተገለጠው ለሮማ መንግሥት ግብር የሚሰበስቡ የመንግሥት ተወካዬች በጴጥሮስ በኩል ስለግብር ጉዳይ አንድ ጥያቄ አንሥተው ነበር፡፡ ጥያቄውም “መምህራችሁ ግብር ይከፍላልን” የሚል ነበር፡፡ ጌታም ይህን ጥያቄ ሰምቶ ምንም እንኳ አስገባሪ እንጂ ገባሪ አለመሆኑን ባይደብቃቸውም የነሱን የተንኮል ጥያቄ ባጭሩ ለመቅጨት ወዲያው ከባሕር ዓሣን ከዓሣ የወርቅ እንክብል አስገብሮ እንዲሰጣቸው ተማሪው ጴጥሮስን አዞታል፡፡ 

በዚያም ሆነ በዚህ ለጥላቻ ማጉሊያ ብለው እንጂ የጠበቁትማ ለቄሣር ግብር እንዳይሰጥ የሚከለክለውን የፖለቲካ መሲሕ አልነበረምን በመሲሕ ላይ ይሙት በቃ የሚያሰኝ ኃጢአት አልተገኘበትም፡፡ ሞቱ የሥርየት እንጂ የቅጣት ሞት አይደለምና በመጀመሪያ በአይሁድ ሊቃነ ካህናት ጉባኤ በኋላም ሮማ መንግሥት ተወካይ በጲላጦስ አደባባይ በዋለው ችሎት ይሙት በቃ ተፈረደበት፡፡ ሞቱም በመስቀል ላይ ነበር፡፡ በመስቀል ላይ እንዳለው በግፍ የሰቀሉትን ሰዎች ተቆጥቶ ማጥፋት ፈንታ “አባ ሥረይ ሎሙ እስመ ኢየአምሩ ዘይገብሩ፤ አባቴ ይቅር በላቸው የሚሠሩትን አያውቁምና” ብሎ ያች ሰዓት የምሕረትና የይቅርታ ሰዓት መሆኗን ነገረን፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ሰውን የቱን ያህል እንደሚወድና እንደሚታገሰው ያሳያል፡፡ ጌታ ይህን የምሕረት ቃል በተናገረ ጊዜ አዳም ከበደለ ጀምሮ የሰው ልጆች እንዳይገቡበት ተዘግቶ የነበረው የገነት በር ተከፈተ፡፡ በሰይጣን ቁራኝነት ተግዘው ለነበሩ ነፍሳትም በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ግዕዛነ ነፍስን ሰበከላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የምእመናን አንድነት መሠረት ተጣለ፡፡ ይህችውም ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ ሦስት መዐልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ሲፀነስና ሲወለድም የእናቱን ማሕተመ ድንግልና አልለወጠምና፡፡ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አበሰረን፤ ለትንሣኤያችን በኩር ሆነ፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ከፍ ብሎ በአራት ቀን ዝቅ ብሎ በሁለት ቀን ያልሆነበት በሦስት ቀን የሆነበት ምክንያት አለው፡፡ ይኸውም ዕብራውያን አንድ ሰው ፍጹም መሞቱን የሚረዱት በሞተ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በመቃብር የቆየው ሦስት መዐልት ሦስት ሌሊት ጌታ የተቀበረው ዐርብ ከአሥራ አንድ ሰዓት ከሰዓት በኋላ ድረስ ያለው የቅዳሜ መዐልትና ሌሊት ነው፡፡ ቅዳሜ ከአሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ያለው እሑድ ነው፡፡ አንዱም ሰዓት ቢሆን ከላይ እንደተገለጠው የዕለቱን ሰዓቶች ያሟላል፡፡ ጌታም የተነሣው እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ስለሆነ ሦስት መዐልት ሦስት ሌሊት ማለት ይህ ነው፡፡ 
ከተነሣም በኋላ ለደቀመዛሙርቱ አንዳንድ ጊዜ እየተገለጠ ሲታያቸው አርባ ቀን ያህል ቆየ፡፡ በትንሣኤው ስለተገኘው ድል የማበረታቻ ትምህርትን አስተምሯቸዋል፤ በንፍሐት ሥልጣነ ክህነት ሹሟቸዋል፡፡ በተነሣ በአርባ ቀኑ ወደ ሰማይ አረገ፤ በዚህም ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እልክላችኋለሁ፤ እስከዚያው ግን ከኢየሩሳሌም እንዳትወጡ ብሎ ትእዛዙን አዟቸው ተስፋውን ነግሯቸው አረገ፡፡ ባረገ በአሥረኛው በተነሣ በሃምሳኛው ቀን በገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት በአንድ ላይ ተሰብስበው እንዳሉ መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው፡፡ ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብልየት ታደሱ በአእምሮ ጎለመሱ፡፡ ፍሩሓን የነበሩ ጥቡዓን ሁነው ፈርተው የካዱትና እየተንቀጠቀጡ ጥለውት የሸሹትን የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም የማያወላውሉ ሆኑ፡፡ ትንሣኤውንም ለመመስከር በየአደባባዩ መሯሯጥ ሆነ፡፡ የአይሁድ ቁጣና ተግሣጽ አልመለሳቸውም፡፡ እንዲያውም ተገፈው ተገርፈው ሲመለሱ የንጉሥ ማለፊያ ቀምሶ እንደወ ባለሟል ደስ ይላቸው ነበር፡፡
የእግዚአብሔር ጥሪ ለመልካም አድራጊዎች ብቻ ሳይሆን ክፉ አድራጊዎችም ከክፋታቸው በንሰሐ ቢመለሱና በክርስቶስ ቢያምኑ ለማዳን ጊዜው ያላለፈ መሆኑንም ጠንክረው አወጁ፡፡ ይህም የቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ይህን ኹሉ ጥብዓትና እምነት ያገኙት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ስለሆነ የኋላ ሊቃውንት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉባትን ዕለት “የቤተክርስቲያን የልደት ቀን” ናት ብለዋታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ባይታደሱ ለክርስቶስ ትንሣኤ ምስክር ለመሆን ባልበቁም ነበር፡፡ “የቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት” ብለዋታል ሁሉንም የሚያነጻ ሁሉንም የሚቀድስ መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠበት ቀን ነበርና፤ በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን የጀመረችው መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ 
የቤተክርስቲያን መመሥረት ያስፈለገበት ምክንያት በቅዱሳት መጻሕፍትና በአበው ትውፊት አማካይነት በአጭሩ ከዚህ በላይ ተዘርዝሮ እንደተገለጠው ነው፡፡

Wabi :የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
ብጹእ አቡነ ጎርጎርዮስ
አዲስ አበባ 1978


3 comments: