Friday, July 27, 2012

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ


 
......«ሐምሌ 22 ቀን 1928  ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። .........

በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።
ከዚያም ከቅኔው ዐውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩ ሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አሔዱ።

Wednesday, July 25, 2012

ቁልቢ ገብርኤል



 ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 461 /. ርቀት ላይ በምዕራብ ሐረርጌ ሀበገረ ስብከት ጋራ ሙለታ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የዚህን ደብር አመሠራረት በተመለከተ በብዙ ሊቃውንት የሚተረከው የሚከተለው ነው፡፡
በዘጠነኛው //. ዮዲት ጉዲት ተነሥታ አብያተ ክርስቲያናትን ስትመዘብር፣ ክርስቲያኖችን ስትገድልና መጻሕፍትን ስትቆነጻጽል ንጉሥ አንበሣ ውድም በአኩስምና በአከባቢዋ የነበሩ ታቦታትንና ንዋያተ ቅዱሳትን በመያዝ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ዝዋይ መጣ፡፡
40 ዓመታት ስደት በኋላ አንበሣ ውድም ወደ አኩሱም ሲመለስና የንዋያተ ቅዱሳት ቆጠራ ሲደረግ ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል በዝዋይ መቅረቱ ታወቀ፡፡ ከኤርትራ ደብረ ሲና ማርያም የመጡት አባ ሌዊ የተባሉ አባት ታቦቱን ለማምጣት ከንጉሡ አስፈቅደው ወደ ዝዋይ መጡ፡፡

Friday, July 20, 2012

ቤተክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች ? ክፍል 3



በማቴዎስ 09¸ 06-2 እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብሎ ለጠየቀው ኦሪታዊ ባለጸጋ እንኳ የሙሴን ትእዛዝ እንዲጠብቅ አዘዘው፡፡ ፍጹም እንዲሆን ቢፈልግ ርግጥ በትሩፋት ላይ ትሩፋት ለመጨመር ቢፈልግ ሀብቱን ለነዳያን ሰጥቶ እሱን ቢከተለ የሚሻለው መሆኑን አልሰወረም፡፡ እነሱ የሚጠቅሱትን ሙሴም ስለርሱ የጻፈ ስለርሱ የተነበየ መሆኑን ነግሯቸዋል፡፡ በፖለቲካም ለቄሣር ግብር አትስጡ ብሎ ሕዝቡን ያሳምጻል ተብሎ ከመከሰሱ በፊት “ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል ወይስ አይገባም?" ብለው በተንኮል ቢጠይቁት “የመንግሥታችሁን ለመንግሥታችሁ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏቸዋል፡፡
 እንደተገለጠው ለሮማ መንግሥት ግብር የሚሰበስቡ የመንግሥት ተወካዬች በጴጥሮስ በኩል ስለግብር ጉዳይ አንድ ጥያቄ አንሥተው ነበር፡፡ ጥያቄውም “መምህራችሁ ግብር ይከፍላልን” የሚል ነበር፡፡ ጌታም ይህን ጥያቄ ሰምቶ ምንም እንኳ አስገባሪ እንጂ ገባሪ አለመሆኑን ባይደብቃቸውም የነሱን የተንኮል ጥያቄ ባጭሩ ለመቅጨት ወዲያው ከባሕር ዓሣን ከዓሣ የወርቅ እንክብል አስገብሮ እንዲሰጣቸው ተማሪው ጴጥሮስን አዞታል፡፡