ሕዝቡ በጠቅላላ ገበሬውም ሆነ ነጋዴው የመንግሥትም ባለሥልጣን በሚሠራው ሥራ ሁሉ ባለጸጋ ስለነበር የሮም ግዛት ተወዳዳሪ የሌላት ታላቅ አገር ነበረች፤ ታዲያ ምን ያደርጋል እነዚህ ሁሉ ሀብታት ለሕዝቡ ደስታና ውስጣዊ ዕረፍትን ሊያገኙለት አልቻሉም፡፡ ሁልጊዜ በአካባቢው ከሚሰማው የሽብርና የሁከት ድምጽ የተነሳ ባልታሰበ ቀን እንደመስሳለን በሚል ቀቢጸተስፋ ገዝቶት ነበር፤ ያመልኳቸው ከነበሩ ጣዖታትም አንዳችም የተስፋ ድምጽ አልነበረም፡፡ በቀቢጸ ተስፋ ባሕር ውስጥ ገብቶ የሚማቅቀውና መውጣትም የተሳነው አማኛቸውን ሊያረጋጉት አልቻሉም፡፡
ዳዊት እንደተናገረው ዓይን እያላቸው የማያዩ፤ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፤ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ አፍ እያላቸው የማይናገሩ፤ እግር እያላቸው የማይሄዱ ግዑዛን ናቸውና፡፡ ከዚህም የተነሣ ማለት የሚያመልኳቸው ጣዖታት ሊያረጋጓቸውና ሊረዷቸው ስላልቻሉ ሕዝቡ “አማልክቶቻችን የዋሃንና ግድ የለሾች ናቸው” እያሉ በጣዖታቱ ይዘብት ነበር፡፡ የሰው ልጅ ሥልጣኔም በክፋትና በደግነት መካከል የለውን ልዩነት ለማመልከት አልቻለም፡፡ በዚህም አኳኻን ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕድል ምንም የተስፋ ጭላንጭል አልነበረም፡፡ ሰው በተፈጥሮው ከወዴት መጣሁ? ወዴትስ ነው የምሔደው? ብሎ ራሱን በራሱ የመጠየቅና የመመርመር ስጦታ ያለው ባለአእምሮ ፍጡር ስለሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ሁልጊዜ በፊቱ ይደቀኑበታል፡፡ ነገርግን ለነዚህ ጥያቄዎች ከውስጥ ከራሱም ሆነ ከውጭ ከሌላ አጥጋቢ መልስ ስላላገኘ ከላይ እንደገለጥነው የደስታና የኑሮ ጣእሙንና ምሥጢሩን ሊያውቀው አልቻለም፡፡ በሮም ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚኖር ሁሉ በዚህ ሁኔታ በቀቢጸ ተስፋ ስለተሞሉ እነሱም ሆነ ሥርዓተ ማኅበራቸው ጠባቂ እንደሌለው መርከብ አቅጣጫው የማይታወቅ ሆነ፡፡ ሕዝቡን ለማስደሰት በሮም የቴያትር ሰገነት ላይ የሚቀርበው የጨዋታ ዓይነትም እንኳ ደም መፍሰስና መደባደብ ስለነበር በጨለማ ላይ የዛፍና የገደል ጥላ ሲጨመር ጨለማው እንደሚጸና ሰቀቀኑን አባብሶት ነበር፡፡

