ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማታ ማታ እየወጣ የሚያድርባት፣ሐሙስ ሌሊት በይሁዳ በኩል ለአይሁድ ተላልፎ የተሰጠባት፣ሐዋርያት ስለ ነገረ ምጽአት ጠይቀው የተረዱባት፣ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ጌታችን ያረገባት ተራራ -ደብረ ዘይት።
ዐርገ የሚለው የግዕዝ ግስ ዐረገ፣ወጣ በሚሉት የአማርኛ ቃላት የሚፈታ ሲሆን ዕርገት የሚለው ስምም ማረግን፣ መውጣትን፣አወጣጥን ያመለክታል።(አ.ኪ.ክ መ.ቃ)
ዕርገት ማለት መውጣት ወይንም ከፍ ከፍ ማለት ነው። ይኸውም ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መሄድን ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነው ኤልያስ ሳይሞት በሕይወት እያለ በእሳት ሰረገላ ላይ ተቀምጦ ወደ ሰማይ ማረጉን ይነግረናል። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ማረጉን የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።


