ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማታ ማታ እየወጣ የሚያድርባት፣ሐሙስ ሌሊት በይሁዳ በኩል ለአይሁድ ተላልፎ የተሰጠባት፣ሐዋርያት ስለ ነገረ ምጽአት ጠይቀው የተረዱባት፣ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ጌታችን ያረገባት ተራራ -ደብረ ዘይት።
ዐርገ የሚለው የግዕዝ ግስ ዐረገ፣ወጣ በሚሉት የአማርኛ ቃላት የሚፈታ ሲሆን ዕርገት የሚለው ስምም ማረግን፣ መውጣትን፣አወጣጥን ያመለክታል።(አ.ኪ.ክ መ.ቃ)
ዕርገት ማለት መውጣት ወይንም ከፍ ከፍ ማለት ነው። ይኸውም ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መሄድን ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነው ኤልያስ ሳይሞት በሕይወት እያለ በእሳት ሰረገላ ላይ ተቀምጦ ወደ ሰማይ ማረጉን ይነግረናል። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ማረጉን የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ቅዱስ ዳዊት «አምላክ በዕልልታ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ» በማለት በትንቢት መነጽርነት ተመልክቶ በመንፈስ ዘምሯል። ይህም ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በአርባኛው ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቢታንያ ይዟቸው ሄዷል።ሉቃ 24፡50 ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ በተለያየ ቦታ ተገልጾ ታይቷቸዋል። ትምሕርትም አስተምሯቸዋል። «ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ዐርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግስት ነገር እየነገራቸው በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ህያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው»ሐዋ 1:3። በነዚህ ቀናት ውስጥ ጌታችን ሥርዓትን አስተምሯቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ትምሕርት ኪዳን ብላ ትጠራዋለች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያት የነገራቸው መጽሐፈ ኪዳን ይባላል ፡፡
ጌታችን በእውነት እንዳረገ ይኽም ሊታመን የማይችል እንዳልሆነ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያስረዳል።
ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሄደ፡ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፤ሥጋው አልተለወጠምና። ሃይ.አበው ዘዮሐ.አፈ.ክፍል 13 ቁጥር 15
አንቃዕድዎተ ዐይን
ወዘንተ እንዘ ይብሎሙ ተለዐለ ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ ወተሠወረ እምአዕይንቲሆሙ። የሐዋ. 1፥9
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ የወጣው በርህቀት(በመራቅ) እንጂ በርቀት (ቀ-ጠብቆ ይነበብ፤ረቂቅ በመሆን) አይደለም።ይኽም ማለት አስቀድሞ የተዋሐደውን ሥጋ አርቅቆ ፣ግዙፍነቱን አጥፍቶ ሳይሆን ከመለኮቱ ጋር በተዋሕዶ አንድ የሆነው ግዙፍ ሥጋ ግዝፈቱን ሳይለቅ ከዐይን በመራቅ፣ከፍ ከፍ በማለት፣ ወደ ሰማይ በመውጣት ነው።
በትምህርቱ የተጽናኑ፣በተአምራቱ የተማረኩ፣ ትዳራቸውን፣ ወላጆቻቸውን፣ ሃብታቸውን፣ ሥልጣናቸውን፣… የተዉለት ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር አብሮአቸው የቆየ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ሲለያቸው በናፍቆት ተይዘው ወደ ሰማይ ሲወጣ ትኩር ብለው ተመለከቱት። ያሳያቸውን ፍቅር፣ሑሩ ወመሃሩ በማለት ያዘዛቸውን አገልግሎት እንዴት እንደሚወጡት እያሰቡ ትኩር ብለው ተመለከቱት።
ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁ
ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁ
ከዕለተ አርብ ስቅለት በፊት በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ለደቀ መዛሙርቱ ካስተላለፈው መልዕክት ውስጥ አንዱ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን የሚያመላክት ነበረ። ‹‹ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ››ዮሐ 14፣3 ብሏቸዋል። እርሱ በአካል ስለሚለያቸው የሐዘን ሰሜት እንዳይሰማቸው የሚያጽናና መንፈስ እንደሚልክላቸው ከሞቱ አስቀድሞ «አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል»ዮሐ 14፣26 ብሎ ነግሯቸዋል። እነዚህ የጌታችን ንግግሮች ለደቀ መዛሙርቱ የስንብት ንግግሮች ብቻ ሳይሆኑ የማረጋጊያና ተስፋ ጭምር የሚሰጡ ነበሩ። ለጊዜው ተለይቷቸው ቢሄድም እንደማይተዋቸው ያሳየበት የፍቅሩ መገለጫዎች ነበሩ። እስከ መጨረሻው እንደማይተዋቸውም ‹‹እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ››ማቴ 28፡19 በማለት ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ቀጥሎ ለሚነሱ የቃሉ አገልጋዮች ቃል ገብቶላቸዋል።
እጆቹን አንስቶ ባረካቸው
ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደብረ ዘይት ይዟቸው ወጣ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ወንጌልን ሰብኮ ሌሊት ያድር የነበረው በደብረ ዘይት ነበር። ይህ ስፍራ ስለዳግም ምጽአቱ ለደቀ መዛሙርቱ ትምሕርት የሰጠበት ቦታ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ሥፍራ ሊያርግ ሲል «በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግስትን ትመልሳለህን?» ሐዋ 1:6 ሲሉ ጠይቀዋል። ይህም ገና ከምድራዊና ከስጋዊ አስተሳሰብ ገና ያልወጡ መሆናቸውን ያሳየናል። ጌታችን መድኃኒታችን ከምድራዊ አስተሳሰብና ከስጋ መንፈስ እንዲላቀቁ «እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ እናንተ ግን ኃይልን ከላይ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ» ሉቃ 24፣49 ብሏቸዋል። «ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ። ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ» በማለት ተስፋቸውን ብሩኅ አድርጐታል።
እጆቹንም አንስቶ ባርኳቸው ወደ ሰማይም ዐረገ
«ወደ ሰማይ ዓረግህ ምርኮን ማረክህ» መዝ 67፡18 የሚለው የትንቢት ቃል እነሆ ጌታችን ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ተፈጸመ። የሰው ልጅ ሁሉ ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፉ በሰይጣን አገዛዝ ሥር ወድቆ በምርኮኝነት ተይዞ ነበር። አሁን ግን የሰይጣን ወጥመድ ተሰበረ። የሰው ልጅ ከምርኮኝነት ተላቆ ነጻ ወጣ። ጌታችንም ሰይጣንን ድል አድርጐ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ዋና ዓላማ ፈጽሞ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ። «ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖር የሰው ልጅ ነው» ዮሐ 3፡13 የሚለው ቃል ተፈጸመ። «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን»ፊሊ 3፡20 ሲል ሐዋርያው ተናገረ። ከምድራዊው ሕይወት ይልቅ ሰማያዊ ሕይወትን እንዲመለከት አደረገው።
ነቢር በየማነ አብ
ነቢር በየማን -በቀኝ መቀመጥ በመጽሐፍ ቅዱስ አገባብ መሠረት ዕሪናን(በሥልጣን አንድ መሆንን) ያመለክታል።በመለኮቱ የእግዚአብሄር አብ ልጅ፣ በትስብእቱ(ሥጋን በመዋሐዱ) የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ።ማር.16፥19
ይኽ ስለ መለኮት የተነገረ አይደለም፤በመለኮቱስ ከአብ ሥልጣን ዝቅ ያለበት የዐይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ የለምና።ነገር ግን ከተዋሕዶ በፊት ደካማ፣በደለኛ እና ውርደት ይስማማው የነበረው የእኛ ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ ጸጋን የሚያድል፣እውነተኛ ፍርድን የሚያደርግ፣ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ነው።
ዕርገተ ልቡና
ሲጸልዩም ሆነ ሲናገሩ፣ሲጾሙም ሆነ ሲመገቡ፣ሲሠሩም ሆነ ሲያርፉ የአምላክዎን ውለታ በማሰብ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ለምን ያህል ደቂቃቆች ያርጋሉ(ይመሰጣሉ)?
ሐዋርያት ጌታችን በአካለ ሥጋ አብሮአቸው እያለ ያዘዛቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ በመታመን አደራቸውን እንደተገበሩ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ያለን ምዕመናንም ጌታችን በበረት በመወለድ፣የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ የሰጠንን የትሕትናን አደራ፤ወደ ግብፅ በመሰደድ፣በመስቀል በመቸንከር ያሳየንን መከራን የመቀበል አደራ፤አልአዛርን ከሙታን በማንሣት፣ራሱም በገዛ ሥልጣኑ ከሙታን በመነሣት የነገረንን ትንሣኤ ዘጉባኤን ተስፋ የማድረግ አደራ በሐሳባችን እያረግን ፣ልባችንን ከፍ ከፍ እያደረግን ክርስቲያናዊ ምግባራትን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረን በመያዝ ልንጠብቀው ይገባል።
እኛም በላይ በሰማይ ያለውን ዘለአለማዊ ሕይወት እያሰብን በሐይማኖት ጸንተን ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን እንድንኖር ጥበቡንና ማስተዋሉን እግዚአብሔር ያድለን አሜን!
ወንድሜ ሆይ ማስተዋሉን የሰጠህ የድንግል ማሪያም ልጅ ይክበር ይመስገን::ከእድሜ ረጅሙን:ከጤና ብዙውን ይስጥህ:: በርታ ::
ReplyDeleteGOD bless you Mele!!!
ReplyDeletekale hiwet yasemaln ke baile ergetu Bereket ykfelh
ReplyDeleteበጣም ጥሩ የተዋህዶ ትምህርት ነው እኛ የምንፈልገው ቃለ እግዚአብሔርን ከሚስጢሩ ሳይፋለስ ያለውን ነው እንጂ የማንንም ልቅምቃሚ ቃርሚያ ትምህርት አንፈልግም ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ምሁራን ልጆች አሏት እጅግ በጣም ጥሩ መልእክት ነው ቢቻል ደግሞ በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ ልጆች ለማስተማር ወደ እንግሊዘኛ እየተተረጎመ ቢሰጥ ጥሩ ነው እንደሚደረግ ተስፋ አደርጋለሁ
ReplyDeleteThank you for all the writings and teachings you have given us on this blog. I apologize that I am writing in English because I don't have an Amharic Font. I was wondering if you could provide us with St Yared's Mezmur from "Degua" for each Sunday of the whole year just like you have been doing during the great lent. We have been trying to find a way to get the written document in Ge'ez as well as Amharic so that we can use it here in Holly Trinity church in Los Angeles CA.
ReplyDeleteKeep me in your prayer
Kale hiywot yasamalin manigisita samayatin yawarisilin tsagawun yabizalin.
ReplyDeleteAmen
Wonidimachin Ejig baxam Asitamar Timirit new ETHIOPA OETHODOX TEWAHIDO .LA ZALALAM TINUR Egnam ba Eminatachin tsanitan Edininor EGIZABHER AMILAKI yiridan AMEN AMEN AMEN !!!!