......«ሐምሌ 22 ቀን 1928 ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ
ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና
አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ
ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። .........
በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ
ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ
መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው
በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ
ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን
ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።
ከዚያም ከቅኔው ዐውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ።
በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩ
ሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ
ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አሔዱ።