Tuesday, December 27, 2011

ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ


የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን



የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ስቴ ወረዳ የሚገኝ ነው ፡፡

በዐጼ አድያም ሰገድ ኡያሱ ዘመነ መንግሥት የተተከለዉ ጥንታዊዉና ታሪካዊዉ ደብረ ሃማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በሦስት ታላላቅ ጉባኤያቱ የታወቀ ነበር፡፡
1. በብሉይና ሐዲስ ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ
2. በቅኔ ቤተ ጉባኤ
3. በድጓ ቤተ ጉባኤ
በሦስቱም አብያተ ጉባኤያት ታላላቅ ሊቃዉንትን ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲያበረክት የቆየዉ ይህ ታሪካዊ ቦታ እስከ 1950ዎቹ ሦስቱም ጉባኤያት የነበሩት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን የቅኔ ጉባኤ ቤቱ ታጥፎ የትርጓሜ መጻሕፍቱና የድጓ ጉባኤዎቹ ግን አሁንም ሳይታጎሉ የሚሰጥበት ቦታ ነዉ፡፡

        ቤተ ክርስቲያኑ በንግሥተ ንግሥታት ዘዉዲቱ ዘመን በጥሩ ሁኔታ በዘመናዊ መንገድ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ወዲያዉኑ ጠላት (ጣልያን) ወደ ሀገራችን በመግባቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑ ተቃጠለ፤ በቦታዉ የነበሩት ታላላቅ ሊቃዉንትም ሰማዕትነት ተቀበሉ፡፡
ከጣሊያን ወረራ በኋላ እንደገና በቦታዉ ላይ የትርጓሜ መምህር በነበሩትና በኋላ ከመጀመሪያዎቹ ጳጳሳት አንዱ በነበሩት የጥንቱ አቡነ ሚካኤል ( የቅዳሴ ትርጓሜን አዘጋጅተዉ ያሳተሙት) አሳሳቢነትና አስተባባሪነትም ጭምር በንጉሡ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ እንደገና አሁን በሚታየዉ መልኩ ተሠርቶ በእግዚአብሔር ቸርነት ተጠናቀቀ፡፡
ይህ አሁን ያለዉ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ መሠረቱ ሲጣል ራሳቸዉ ንጉሠ ነገሥቱ እቦታዉ ድረስ የሄዱ ሲሆን በጊዜዉ በቦታዉ ላይ ቅኔዉንና ትርጓሜ መጻሕፍቱን አንድ ላይ አድርገዉ ያስተምሩ የነበሩት እጅግ ስመ ጥር የነበሩት የኔታ ኃይለ ጊዮርጊስ የነበሩበት ዘመን ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በድጓ ቤት ያሉትን ሳይጨምር 450 በላይ የቅኔና የትርጓሜ መጻሕፍት ተማሪዎች የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡
በጊዜዉ የግብጽ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ካልዓይ
ይህ አሁን ያለዉ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሞ በሚመረቅበት ጊዜ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ባይገኙም በጊዜዉ የግብጽ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ካልዓይ፣ የኋላዉ ፓትርያርክ የዚያን ጊዜዉ ጳጳስ አቡነ ቴዎፍሎስና ታላቁ አቡነ ዮሐንስ ከሌሎች የጊዜዉ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና ሊቃዉንተ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተገኝተዋል፡፡
በወቅቱ በቦታዉ በመማር ላይ የነበሩት ብዙዎቹ በወቅቱ የነበረዉን ርቃቄና መንፈሳዊነት የሠለጠነበትን ፍልስፍናዊ የትምህርት ጊዜ በማስታወስ ጊዜዉን ደብረ ሃይማኖት ካልዕት እስክንድርያ የነበረችበት ጊዜ ያደርጉታል፡፡ አንዳንዶች ግን ከዚያም በፊት ቢሆን እንዲሁ እጅግ ስመ ጥር የሆኑ ሊቃዉንት የነበሩበትና መንፈሳዊ ፍልስፍና ርቃቄ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የሚሠጥበት በመሆኑ ከጥንት እስካሁን ካልዕት እስክንድርያ ናት ይሏታል፡፡
ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ ካቶሊኮች ገብተዉ ከወጡበት የጥንቱ ጊዜ በኋላ መልኩን ቀይሮ የቤተ ክርስቲያን ሊቃዉንትን ሲያበጣብጥ የቆየዉ የቅባትና የጸጋ ሰርጎ ገብ ፈጽሞ ካልረገጣቸዉ የሰሜን ኢትዮጵያ የትርጓሜ ትምህርት ቤቶች አንዱ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ነዉ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ
2ኛው ፓትርያርክ

ቦታዉ ለቅርቧ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ያበረከታቸዉ ሊቃዉንት እጅግ ብዙዎች ናቸዉ፡፡ ከቀዳሚዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ ከሆኑት ከብጹነ አቡነ ሚካኤል ጀምሮ እነ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ አቡነ ኤልያስ (አሁን ስዊድን ያሉት) የኋላዉ አቡነ ኤልያስ (የቀለም ቀንዱ) ተጠቃሾች ሲሆኑ ከሊቃዉንቱም እነ ርዕሰ ደብር ጥዑመ ልሣን፣ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ ሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ፣ መልአከ ሰላም መርዓዊ ተበጀ፣ተቆጥረዉ የማያልቁ የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የቅኔና የዜማ ሊቃዉንትን አፍርቷል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ባለፉት ሃምሳ ዐመታት ዉስጥም በቦታዉ ብሉይና ሐዲስን በማስተማር፣ የተጣሉትን ከማስታረቅ ጋር በብህትዉና በመኖር የሚታወቁት መጋቤ ሐዲስ ኃይለ ሚካኤል ብዙ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ያገለገሉበት ሲሆን እርሳቸዉ በዕርጅና ማስተማሩን ሲያቆሙ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሐዲሳቱን ከእርሳቸዉ ብሉያቱን ደግሞ ጎንደር ዐቢየ እግዚእ ከየንታ ፀሐይ የተማሩት የንታ ሐረገወይን ተተክተዉ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
 የደብሩ አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ሃይማኖት ሲሳይ አሰፋም በቦታዉ ላይ ድጓዉን በማስተማር ከሃያ አምስት ዐመት በላይ ኖረዉበታል፡፡
ቦታዉ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ከመሆኑም በላይ ከጥንት ጀምሮ እጅግ ብዙ ሕመምተኞች (ብዙ የእስልምና ተከታዮችን ጨምሮ) የሚፈወሱባት የኪዳነ ምሕረት ጸበል ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቆርቆሮዉ አርጅቶ በማፍሰስ ላይ ከመሆኑም በላይ ሌሎቹንም ጨምሮ 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚጠይቅ እድሳት እንደሚያስፈልገዉ በባለሞያ ወጪው የተጠናዉ ጥናት ያመለክታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኘዉ ገጠር ዉስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሌሎቻችንን በተለይም በቦታዉ ላይ በመማርና ከተማሩት አገልግሎት በማግኘት ላይ ያለነዉን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኘዉን ታሪካዊዉን ቦታ በመርዳት እንደ ቀድሞዉ ሁሉ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለዉን አስተዋጥኦ ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡

 ይህን ታላቅ ሥራ ወደ ፍጻሜ ለማድረስም በመጭዉ እሁድ ታኅሣሥ 22 ቀነ 2004 . . በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተዛግጅቷል፡፡ በዕለቱ ክቡር ሊቀ ሊቃዉንት ዕዝራ ሐዲስ የሚያስተምሩ ሲሆን ሌሎች ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮችም ይቀርባሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑን ማገዝ ለሚፈልጉ ሁሉ ሁለት መንገዶች ተዘጋጅቷል፡፡ የመጀመሪያዉ ለሁሉም ሰዉ እንዲሆን የተዘጋጀዉ ባለ 30 ብር ካርድ ለጉባኤዉ እንደ መግቢያ ጭምር የሚያገለግለዉ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ በጉባኤዉ ላይ በመገኘትም ሆነ ከዚህ ዉጭ በዐይነትም ሆነ በገንዘብ በመርዳት ታሪካዊ ሓላፊነታቸዉን እንዲወጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ለበለጠ መረጃ
+251 911 68 93 22 ለዲ/ ብርሃኑ አድማስ 
+251 911 10 95 84 ለመ/ ቸሬ አበበ መደወል ይችላሉ፡፡
እግዚአብሔር በአባቶቻችን እግር የምንተካ 
የአባቶቻችን ልጆች ያድርገን  - አሜን  ፡፡

5 comments:

  1. መድኌኒዓለም ይርዳችሁ::ከባህር ማዶ ላለንም ከበረከቱ ይድረሰን መላ በሉ::

    ReplyDelete
  2. ዲ/ን መላኩ እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልህ!
    ይህን ታሪክ ለማወቅ ሁሌም እጓጓ ነበር እና ዛሬ በሚገባ ፈትፍተህ ስላጎረስከኝ ቸሩ አምላካችን የህይወትን ቃል ያሰማልኝ!!!

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልህ!
    ታኅሣሥ 22 ቀነ 2004 ዓ. ም. ??

    ReplyDelete
  4. Amen!!! Kale hiwot yasemalin! Betena beselam yitebikilin!

    ReplyDelete