Friday, December 30, 2011

በዓለ ልደቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት


አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ  ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ . ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ ማለት ነው፡፡ አባታቸውየቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲያስተምሯቸው አካባበቢያቸው ደግሞ በዘመኑ የነበሩ ልጆች ይማሩ የነበረውን ፈረስ መጋለን፣ ቀስት መወርወርን፣ እርሻን እና አደንን አስተምረዋቸዋል፡፡
ደብረሊባኖስ ገዳም     
በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለክህነት መጠራት በዚህ ዓለም ትዳር መሥርቶ፣ የዓለሙንም ሥራ ሠርቶ መኖር አያስፈልግም ከሚልፍልስፍና የመነጨ አይደለም፡፡ 8ኛው መክዘ ጀምሮ በሀገሪቱ የመንፈስ መቀዛቀዝ ይስተዋል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ነው የተክለሃይማኖት የጥሪ ምክንያት፡፡

 ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ሃይማኖት» አለው ፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ ፡-
«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይየመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»/ገድለ ተክለ ኃይማኖት ምዕ ፳፰   - 
ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡
      አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ዕረፍት በኋላ ቅስናን ከአቡነ ቄርሎስ ተቀብለው በጽላልሽ አካባቢ በክህነት ከአባታቸው ጋር አገልግለዋል፡፡ አባታቸው ሲያርፉ በወንጌሉ ማንም ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር  ያለውን ሁሉ ትቶ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝያለውን በመከተል ሀብታቸውን ለድኾች መጽውተው ለወንጌል ስብከት ወጡ፡፡የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ከመሄዳቸው በፊት ቅስናን ተቀብለው በሸዋ እና በዳሞት ማገልገላቸውን ይገልጣል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዳሞት እና በሸዋ ካገለገሉ በኋላ መጀመርያ ደቡብ ወሎ ቦረና ወደ ነበረው ወደ ደብረ ጎል ገዳም ገብተው አሥር ዓመት (12 የሚልም አለበትምህርት እና በሥራ አሳልፈዋል፡፡ በዚያም ዋሻ ፈልፍለው አስደናቂ ሕንፃ ሠርተው ነበር፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-

«
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብምዕ ፲፩  ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
«ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
«
የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩  ፴፫ /ምዕ ፲፩  ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን  የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
«ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
«
ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡

ደብረሊባኖስ ገዳም
     ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚለው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሐይቅ የገቡት በሠላሳ ዓመታቸው ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን በሸዋ እና በወላይታ ያገለገሉት ገና  መሆኑን ነው፡፡ 1216 ዓም አካባቢ ወደ ሐይቅ የገቡት አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሐይቅ ከመመንኮሳቸው በፊት ሰባት ዓመት ከመነኮሱም በኋላ ሦስት ዓመት በትምህርት  በሥራ እና በአገልግሎት ቆይተዋል፡፡
ሐይቅ እስጢፋኖስ በዚያ ዘመን እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ያለ ዩኒቨርሲቲ ነበረ፡፡ወደዚያ የሚገባ ሁሉ ሦስት ነገሮችን ይማራል፡፡ ትምህርት፣ የጥበበ እድ ሥራ እና ሥርዓተ ምንኩስና፡፡ ትምህርቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን መላ ትምሀርት ያካትታል፡፡ የሞያ ትምህርቱም መጻፍ፣ መደጎስ፣ ሕንፃ ማነጽ፣ ልብስ መሥራት፣ እርሻ፣ የከብት ርባታ እና የሥዕል ሥራን ይመለከታል፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ጽሙድ እንደ ገበሬ ቅኑት እንደበሬ እንዲሆኑ ሥርዓተ ምንኩስናን ይማራሉ፡፡
      በእነዚህ ትምህርቶች የታነፁት መነኮሳት ከገዳሙ ሲወጡ ዛሬ የፒኤች  ተማሪ ዴዘርቴሽን እንደሚያቀርበው የተማሩትን ጽፈው አንድ የብራና መጽሐፍ አዘጋጅተው ይወጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቅ ከስምንት መቶ መነኮሳት በላይ በአንድ ጊዜ የሚማሩባት በመጻሕፍትም የበለጸገች ዩኒቨርሲቲ ነበረች፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እዚህነው አሥር ዓመታትን ያሳለፉት፡፡
       ከሐይቅ ወጥተው በዘመኑ በሥርዓተ ምንኩስና እና በትምህርት ብሎም በጥበበ እድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ ነበረው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ፡፡ በዚያም ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ሥርዓተ ምንኩስና እና ጥበበ እድ ሲማሩ ሰባት ዓመት አሳለፉ፡፡ ያነጹት ፍልፍል ድንጋይ ዋሻ፣ መጻሕፍት ሲጽፉ ቀለማቸውን ያስቀምጡባቸው የነበሩትን ሽንቁሮች ዛሬም በደብረ ዳሞ ማየት ይቻላል፡፡
ቀሪዎቹን አምስት ዓመታት ሌሎችን የትግራይ ገዳማት እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ቆይተው ከሸዋ በወጡ በሃያ ሁለት ዓመት እድሜያቸው ሃምሳ ሁለት ሲሆን ለበለጠው ክብር እና ርእይ በግብጽ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ተሻገሩ፡፡ ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ በሐይቅ በኩል አድርገው ደብረ ጎልን ተሳልመው በሚዳ እና በመርሐ ቤቴ በኩል ወደ ሸዋ በመምጣት ከዮዲት ዘመን በኋላ  በመንፈሳዊ ሕይወት የተጎዳውን ሸዋን እና ደቡብ ኢትዮጵያን በመዘዋወር ለአሥርዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተግተው በማስተማራቸው የተኛው ሁሉ ነቃ፣ የደከመው በረታ፣የጠፋውም ተገኘ፡፡ በስብከታቸው እንደገና ለነቃው ለመካከለኛው እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሐዋርያትን ለማፍራት እንዲችሉ አንድ ገዳም ለመመሥረትና ደቀ መዛሙርትን ለማስተማር አሰቡ፡፡ እናም ወደ ደብረ አስቦ ገዳም ገቡ፡፡ ቦታውን አስተካክለው እና ከደብረ ዳሞ እና ከሐይቅ የተከተሏቸውን ጥቂት ደቀ መዛሙርት ይዘው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ልክ እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሁሉ ሦስቱን ነገሮች ያካተተ አገልግሎት ጀመሩ፡፡ምንኩስና ትምህርት እና ሥራ፡፡ መነኮሳቱ መንፈሳዊ ትምህርት ይማራሉ፤ በሕገ ገዳም ይመራሉ፤ ለራሳቸው እና ለአካባቢው ሕዝብ ርዳታ የሚሆን እርሻ ያርሳሉ፡፡
ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ገዳማቸውን አደራጅተው፣ ስብከተ ወንጌልንም አስፍተው አስፍተው ሰያደ ላድሉ በሕይወታቸው የመጨረሻ ዓመታት ወደ ደብረ አስቦ ዋሻ ገብተው በአንድ እግራቸው ጾም እና በጸሎት ተወሰኑ፡፡ በጸሎት ብዛትም እግራቸውን በማጣታቸው ስለ ክብራቸው ከእግዚአብሔር ክንፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡
         ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
          አቡነ ተክለ ሃይማኖት አገልግሎታቸውን ፈጽመው ነሐሴ ሃያ አራት ቀን 1287 ዓም በ99 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታህሳስ ፳፬ ቀን ደግሞ በዓለ ልደታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡

 ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡

ዋቢ   ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
       የዳንኤል እይታዎች www.danielkibret.com

13 comments:

  1. አሜን ኢንጅነር ቃለህይወት ያሰማልን የጻድቁ በረከት በሁላችንም ላይ ይደር!!!
    ሳሙኤል ዘ ጎንደር(GC)

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን !!! ያገልግሎት ጌዜህን ይባርክልን !! ወንድማችን በርታ ሰለቤተክርስቲያናችን ታሪክ ፡ ታላላቅ አባቶች ገድል እና ስለ ትውፊተ ቤተክርስቲያን እያሳወቅሀን ነውና በርትልን !

    ReplyDelete
  3. Yetsadiku Abatacjin redeat bereket yideribin. Kale hiwot yasemalin.

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. wendemachin sel betecristanachen betam eyasaweken ena eygelestkel new Egeziabher yagelgelote zemenhen yabzale berta Kalh eywet yasemha

    ReplyDelete
  6. yetsadiku bereket ena tibeka behulachinim lay yider AMEN!!
    Ruth SouthDakota

    ReplyDelete
  7. ዲያቆን መልአኩ
    ፈጣሪ ዕውቀቱን ያብዛልህ።

    ReplyDelete
  8. ቃለ ህይወት ያሰማልን !!! ያገልግሎት ጌዜህን ይባርክልን !! ወንድማችን በርታ ሰለቤተክርስቲያናችን ታሪክ ፡ ታላላቅ አባቶች ገድል እና ስለ ትውፊተ ቤተክርስቲያን እያሳወቅሀን ነውና በርትልን !

    ReplyDelete
  9. ቃለ ህይወት ያሰማልን!

    ReplyDelete
  10. Amen kalhiwot yasmlne

    ReplyDelete