Monday, April 30, 2012

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ


ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን በሃይማኖት ምክንያት የተገደለ፣ መከራ የደረሰበት ሰማዕት ይባላል። (ሐዋ.22፡20) የመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት ሐዋርያትና አርድዕት ናቸው።
ቅዱሳን ሰማዕታት የሚባሉት “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ስገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” በማለት በዓላውያን ነገሥታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት የመሰከሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።
በእሳት ተቃጥለዋል፣ በውኃ ተቀቅለዋል፣ በሰይፍ ተመትረዋል፣ በመጋዝ ተተርትረዋል፣ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል (መንኩራኩር የሚባለው በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ዘመናዊ የወፍጮ መሳሪያ ነው።)፣ እንደከብት ቆዳቸው ተገፏል፣ ወደጥልቅ ባህር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ከሃይማኖታቸው አላፈገፈጉም፤ እንዲያውም ሌሎች “እኔ በእነርሱ አምላክ አመልካለሁ” እንዲሉ አድርገዋቸዋል።

Saturday, April 21, 2012

ዳግም ትንሣኤ



ጌታችን በተነሣበት ዕለት የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ተሰብስበው ሳለ ጌታችን በመካከላቸው ቆመና "ሰላም ለእናንተ ይሁን "አላቸው፡፡ የነበሩበት ቤት በሩም መስኮቱም ተቆልፎ ስለነበር ደቀ መዛሙርቱም በጣም ደነገጡ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  "አትፍሩ እኔ አምላካችሁ ነኝ" ብሎ የተወጋ ጎኑን እና የተቸነከሩ እጆቹን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ጌታ ከሞት መነሣቱን አመኑ፡፡ ደቀመዛሙርቱንም(ተማሪዎቹንም) ሕዝቡን እንዲያስተምሩ ላካቸው፡፡

Thursday, April 19, 2012

ፋሲካ - የፋሲካ በግ - ትንሣኤ



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
 በዲ/ ብርሃኑ አድማስ
እሥራኤልን ከግብጽ እየመራ የወጣው ሙሴ ሕዝቡን ከግብጽ ይዞ መውጣት ይቻለው ዘንድ የታዘዘው ታላቁ ትእዛዝ ፋሲካን በግብጽ ማክበር ነበር፡፡ ፋሲካ የሚባል በዓል ከዚያ በፊት ኖሮም ተከብሮም አያውቅም ነበርና በዝርዝር ማድረግ የሚገባቸዉ ሁሉ ተነገራቸዉ፡፡ ቀኑ በእነርሱ አቆጣጠር በአቢብ ወር በዐሥራ አራተኛዉ ቀን ይከበራል፡፡ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ጠቦት በግ  ይመርጣሉ፡፡ በምድረ በዳ ሲመሽ ያርዱታል፡፡ ደሙን ወስደዉ የቤታቸዉን በር ሁለት መቃኖችና ጉበኑን ይረጩታል፡፡ ሥጋውን በሌሊት በእሳት ጠብሰው ይበሉለታል፡፡ ጥሬውንና በውኃ የተቀቀለዉን አይበሉም፡፡ የተረፈውን ሌሊቱን በእሳት ያቃጥሉታል፡፡በፍጥነት ይበሉታል፡፡ ከዚያ በኋላ ለሰባት ቀን የቂጣ በዓሉን ያደርጋሉ፡፡ ቂጣዉም ምንም እርሾ ያልገባበት ይሆናል፤ …./ዘፍ 12 1-36/፡፡