Tuesday, October 15, 2013

በውኃ ላይ የታነፀው ይምርሐነ ክርስቶስ የ“ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተመራጭ መካነ ቅርስ” ሆነ





ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

ከዛጒዌ ስመ ጥር ነገሥታት አንዱ በነበሩት በንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ከተሠሩት ኪነ ሕንጻዎች አንዱ የኾነው ይምርሐነ ክርስቶስ፤ የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ 2014 ተተኳሪ መካነ ቅርስ (2014 World Monuments Watch) ሆኖ ተመረጠ፡፡
ፈንዱ መስከረም 28 ቀን 2006 .. ዋና /ቤቱ በሚገኝበት በኒው ዮርክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው÷ .. 2014 ዓለም በትኩረት ሊያውቃቸው፣ ሊጠብቃቸውና ለትውልድ ሊያስተላለፍላቸው ይገባል ካላቸው 41 አገሮች ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልዩ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ አንዱ ኾኖ መመረጡ ተገልጧል፡፡
ወርልድ ሞኑመንትስ ዎችበተሰኘው ፕሮግራሙ ለአደጋ የተጋለጡና ዝነኛ የቱሪስት መስሕብ የኾኑ ታሪካዊ ኪነ ሕንፃዎችንና ባህላዊ መካነ ቅርሶችን በማስተዋወቅ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመለገሥ ዘመን ተሻጋሪ እንዲኾኑ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ የሚያደርገው ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ፣ በዝርዝሩ ያካተታቸው የተመረጡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙና በአግባቡ እንዲጠበቁ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የዓለም ቅርሶች የፈንዱ ተጠቃሚ ሲኾኑ ከእኒህም መካከል ፈንዱ .. 1966 ሲቋቋም የክብካቤና ድጋፍ ሥራውን የጀመረባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመልክቷል።
የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ በዓለም አቀፍ ፈንዱ ተመራጭ እንዲኾን በመጠቆምና ለምርጫው የሚያግዙ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ለአዲስ አድማስ የገለጸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤና ልማት ማኅበር፤ መካነ ቅርሱ 2014 የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ ተመራጭ መኾኑ ኪነ ሕንጻውን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማልማት ዕድል ይሰጣል ብሏል፡፡ ቅርሶች ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያበረክቱ ዘንድ ራእይ የሰነቀው ሀገር በቀል ማኅበሩን ጨምሮ በቅርስ ክብካቤ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሥራ ሓላፊዎችና ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የብዙኀን መገናኛና ሌሎች አካላት ጋራ በመተባበር እንንዲንቀሳቀሱም ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡
ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት በሰሜን ወሎ ወግረ ስኂን በሚባል ቦታ ሰፊና ግርማ ሞገስ ባለው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ በውኃ ላይ እንደታነፀ የሚታመነውና ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ይምርሐ ክርስቶስ÷ በአገራችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን የቤተ መንግሥት ሕንጻ፣ በድንቅ ጥንታዊ ሥዕሎችና ንድፎች ያሸበረቀ ቤተ መቅደስ አሰናኝቶ የያዘ መካነ ቅርስ ነው፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ ያልፈረሱና ዕድሜ ጠገብ የሰው ዐፅሞች፣ የሀገር በቀል ዕፀዋት ጥቅጥቅ ደንና ማራኪ መልክአ ምድር የሚገኙበት ነው፡
  

ይምርሃነ ክርስቶስ

ከዳንኤል ዕይታዎች የተወሰደ
 





ወደ ይምርሃነ ክርስቶስ ለመድረስ ከላሊበላ ወደ ሰቆጣ የሚወ ስደውን መንገድ ይዘን ለ30 ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ ብል ብላ ከተባለችው ከተማ ደረስን፡፡ ከዚያም ዋናውን መንገድ ትተን ወደ ምሥራቅ ተገነጠልን፡፡ መንገዱ ወደ ይምርሃነ ክር ስቶስ ቱሪስቶችን ለማጓጓዝ እንዲረዳ በአካባቢው መስተዳድር የተጠረገ መንገድ ነው፡፡ ከብልብላ በኋላ 7 ኪሎ ሜትር እንደ ነዳን ጥንታዊውን የንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ ከተማ ዛዚያን በሩቁ አየናት፡፡ አሁን ለምልክት ከሚታየው እና የኢያቄም ወሐና ማኅበር በብረት ፍርግርግ ለማስታወሻ ካሠራው አነሥተኛ ጎጆ እና በዙርያው ካለው ዐጸድ በስተቀር ሌላ ምልክት አይታይበትም፡፡ቀሪውን ስድስት ኪሎ ሜትር ስናጠናቅቅ ከፊታችን ጥቅጥቅ ያለው ደን ገጭ አለ፡፡

1526 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው እና በተራራው ላይ የተዘረጋው ጥንታዊ ደን በሀገር በቀል ጽድ እና ወይራ የተሞላ ነው፡፡መነኮሳቱ ደኑን የተከለው ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ከመኪና ወርደን ባሕል እና ቱሪዝም ባሠራው የእግረኞች መንገድ በኩል ተራራውን መውጣት ጀመርን፡፡ጸጥ ባለው አካባቢ የአእ ዋፍን ድምጽ ብቻ ነው የምትሰሙት፡፡1ኪሎ ሜትር ያህል እየተጠማዘዛችሁ ተራራውን ትወጣላችሁ፡፡



የእግር መንገዱን አጠናቅቃችሁ ከተራራው ወገብ ስትደርሱ «ውግረ ስሂን» የሚባለውን ዋሻ ከሩቁ ታዩታላ ችሁ፡፡የወለል ስፋቱ 50 ሜትር በ38.75 ሜትር የሆነው ይህ ሰፊ የተፈጥሮ ዋሻ ዙርያው በቋጥኝ የታ ጠረ ነው፡፡በስተ ምዕራብ በኩል የዋሻው ከፍታ እስከ 7.7 ሜትር ይደርሳል፡፡በስተ ምሥራቅ በኩል ዋሻውን ውስጥ ለውስጥ እስከ አቡነ ዮሴፍ ተራራ የሚያገናኝ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንዳለው መነኮሳቱ ይናገራሉ፡፡ የገዳሙ ዲያቆናት ችቦ አብርተው የዋሻውን መጨረሻ ለማግኘት ገብተው ነበር፡፡ውስጥ ለውስጥ አራት ሰዓት ተኩል ያህል ከተጓዙ በኋላ ችቦው እያለቀባቸው ሲመጣ ጊዜ መመለሳቸውን የአካባቢው ሰዎች ይተርካሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውስጥ ለውስጥ መንገዱ መግቢያ በደለል እየተደፈነ ይገኛል፡፡በአስቸኳይ ጥናት ማድረግ ካልቻልን እንደተሠወረ የሚቀር ብዙ ታሪክ አለ፡፡

ዋሻው የታጠረበትን የ1979ዓም የብሎኬት አጥር አልፋችሁ ስትገቡ ዓይናችሁ ሊነቀልበት የማይችለውን የ12ኛው መክዘ ሥልጣኔያችንን ታያ ላችሁ፡፡

የቤተ መቅደሱ ድንቅ ጥበብ በውኃ ላይ ከመሠራቱ ይጀምራል፡፡ ዋሻው ውስጥ ተዘርግቶ የነበረው ሐይቅ በላዩ ላይ በእንጨት እና በድንጋይ ተረብርቦ ነው ቤተ መቅደሱ የተሠራው፡፡ የኋላ ዘመን ትውልድ አያምነንም ብለው አስበው ይመስለኛል ከሥሩ የሚገኘውን የውኃ አካል ለማየት እንዲቻል ስትገቡ በስተ ግራ በኩል በእንጨት በር የሚዘጋ ጉድጓድ ትተውልናል፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት እና በመጠ ኑም ማየት እንደሚቻለው በባሕሩ ላይ እንጨት፣ በእንጨቱም ላይ ሣር፣ በሣሩ ላይ ጭቃ፣ በጭቃውም ላይ ደረቅ አፈር፣ በአፈሩ ላይ ንጣፍ ድንጋይ ተደል ድሎ ነው የተሠራው፡፡ ወደ መቅደሱ ገብታችሁ በባዶ እግራችሁ ከቆማችሁ ቅዝቃዜው ይሰማችኋል፡፡

በባሕሩ ላይ የተረበረበው እንጨት በምን መሠረት ላይ ቆመ በእውነትም እንጨት ከሆነ ለአንድ ሺ ዓመታት እንዴት ቆየ? ተመራማ ሪዎችን የሚፈልጉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡




የይምርሃነ ክርስቶስ ቤተ መቅደስ ውቅር አይደለም፡፡ጥንታዊው የኢትዮጵያውያን የሥነ ሕንፃ ጥበብ የተንፀባረቀበት ግንባታ ነው፡፡ ውጫዊ ስፋቱ 12.22 በ9.54 ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ያለው ከፍታ ደግሞ 5.88 ሜትር ያህላል፡፡ ከዕጽዋት፣ ከወጥ ድንጋዮች እና ከኖራ መሰል ነገር የተሠሩ 26 መስኮቶች ዙርያውን አስውበውታል፡፡ እነርሱም በሰሜን 8፣ በምሥራቅ 6፣ በደቡብ 7፣ በምዕራብ 5 ናቸው፡፡ ጠቢቡ አምስት ስድስት፣ ሰባት እና ስምንት ቁጥሮችን በቅደም ተከተ ላቸው የመረጠበት ምክንያት ምን ይሆን? ከ26ቱ መስኮቶች መካከል 22ቱ ሲከፈቱ አራቱ ግን አይከፈቱም፡፡ የአንዱ መስኮት ዲዛይን ከሌላው መስኮት ዲዛይን ስለሚለያይ ለሃያ ሁለቱ መስኮቶች ሃያ ሁለት ዓይነት ዲዛይን ነው የምናየው፡፡ የዘመኑ ጠቢባን ጥበባቸውን ለማሳየት ምን እንደተጠበቡ ያመላክታል፡፡

ቤተ መቅደሱ ደቃቅ፣ መጠናቸው የተመጣጠኑ ጥቋቁር ድንጋዮች በጭቃ እየተጣበቁ ነው የተገነባው፡፡ እንዴት ይሆን ጭቃ እና ድንጋዩን አቡክተው ያጣበቋቸው? የጭቃው ግንባታ ለ25 ሳሜትር ያህል ወደ ላይ ከተጓዘ በኋላ በአራት መዓዝን የተጠረበ ወጥ እንጨት ይገባበታል፡፡ እንዲህ እያለ ድንጋይ፣ ጭቃ እና እንጨት በጥበብ ተስማምተው ይምርሃነ ክርስ ቶስን ለሺ ዓመት ያህል አቁመውታል፡፡ እኔን የገረመኝ ነገር ቢኖር ዛሬ ዛሬ በስሚንቶ እና በድንጋይ የተሠሩት ሕንፃዎቻችን ዓመት ሳይሞላቸው ሲሰነጠቁ ጭቃውን ከድንጋይ እና እንጨት ጋር አዛምደው ይህንን ያህል ዘመን ያቆዩበት ጥበብ ምን ይሆን? የሚለው ነው፡፡ እንዲህ እየተያ ያዘ የተገነባው ግድግዳ ኖራ በሚ መ ስል ነጭ ነገር ከውጭ እና ከውስጥ ተለስኗል፡፡ የልስኑ ንጣት እና የእንጨቱ ወርቃማ ቀለም ለቤተ መቅደሱ ውጫ ዊ ገጽታ ዓይን እንዳይነቀል የሚያደርግ ውበት ሰጥቶታል፡፡
 
በምዕራብ እና በምሥራቅ ሁለት ሁለት ፎቆችን ያዘለው ሕንፃ ወለሉ እጅግ ለስላሳ በሆኑ ድንጋዮች ንጣፍ የተሠራ ነው፡፡ እጅግ የሚያስደንቀውን ሌላ ጥበብ የሚያዩት ደግሞ ወደ በሩ ስትዞሩ ነው፡፡ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠራው በር፣ ከግድግዳው ጋር አንድ ሺ ዘመን በሆናቸው ብሎኖች እየታሠረ በታጣፊ ብረት ተያይዟል፡፡በዚያ ዘመን እንጨት ሠርስረው የሚገቡ ብሎኖችን የመሥራት ጥበብ ነበረን ማለት ነው? በሩን ለመዝጋት ከእንጨት የሠሩት ጥንታዊ ቁልፍ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ የቁልፉ መግቢያ ቀዳዳ እንደ ዘመ ናዊው ቁልፍ የተገለበጠ ቅል ቅርጽ አለው፡፡ በዚያ ዘመን የነበረውን የቁልፍ ቴክኖሎጂ የታሪክ ምሥክር ሆኖ ያሳየናል፡፡

የቤተ መቅደሱን ውስጣዊ ጥበብ ለማየት ከአንድ ወር በላይ ይፈጃል ባይ ነኝ፡፡ የዘመኑ ጠቢባን ያለ ጥበብ ያለፉት አንድም ክፍት ቦታ አይገኝም፡፡ጣራው፣ ግድግዳው፣ ወለሉ፣ ዓምዶቹ በሮቹ እና መስኮቶቹ ሁሉ አንዱ ከሌላው የማይገናኝ ጥበብ ፈስሶበታል፡፡ የመቅደሱ መካከለኛ ቦታ ከተጠረበ እና ለስላሳ ከሆነ እንጨት የተገጣጠመ ሲሆን ክብ ሆኖ የታነፀ ነው፡፡ ውስጡ በመንፈሳዊ ሥዕሎች ያጌጠ ሲሆን የሚዘጋው በመጋረጃ ነው፡፡

የቤተ መቅደሱን ጣራ የተሸከሙት ዓምዶች በባለሞያ ከተጠረቡ ለስላሳ፣ ጠንካራ፣ ሰፋፊ እና ከባድ ከሆኑ የከበሩ ድንጋዮች የታነጹ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ዓምድ ልዩ በሆነ ሐረግ እና ሥዕል የተጌጠ ነው፡፡ የአንዱ ዓምድ ዲዛይን በምንም መልኩ ከሌላው ጋር አይያያዝም፡፡ የቅድስቱ ጣራ በስምንት ክፍል የተከፈለ እ ያንዳንዱ ጣራ የራሱ የሆነ ልዩ ዲዛይን እና ሥዕል አለው፡፡ አሁን አሁን ከአቧራ እና ከክብካቤ እጦት የጣራው ላይ ድንቅ ሥዕሎች እና ቅርጾች እየደበዘዙ ናቸው፡፡

በጣራው ውስጣዊ ገጽታ ከጣራው ጋር ተያየዘው ወደ ታች በወረዱ አራት መዓዝን በሆኑ ሁለት የእንጨት ገመዶች የተን ጠለጠሉ ዕንቁዎች አሉ፡፡ ከሁለቱ በአንደኛው ገመድ ላይ የተንጠለጠሉትን ዕንቁዎች በ1986 አካባቢ ሌቦች የወሰዷቸው ሲሆን እንዳይታወቅ ተመሳሳይ ነገር ተክተውበት ነበር፡፡
ውሳጣዊውን ክፍል ስታዩ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ዘጠና፣ አርባ አምስት እና አንድ መቶ ሰማንያ ዲግሪዎችን ጠብቀው የጣራውን ክበብ፣ የዓምዶቹን መዓዝን እና የመስኮ ቶችን ቅርጽ ለመሥራት የተጠቀሙበት የጂ ኦሜትሪ ጥበብ ምን ይሆን? ምናለ ሕንፃውን እን ዳገኘነው ሁሉ ጥበቡንም አብረን ባገኘው? ያሰኛ ችኋል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ሕንፃ ከማነፃቸው በፊት ዲዛይኑን በምን ሠሩት? ጣራውን ሲያንፁ የተጠቀሙበት የመደገፊያ እና የኮንክሪት ጥበብስ ምን ይሆን?

ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሁለት ጥንታውያን የእንጨት ሳጥኖች ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ ለዕቃ ማስቀመጫነት በሚጠቀሙባቸው እነዚህ ሳጥኖች ላይ የሚታየው ቅርጻ ቅርጽ እና በሕንፃው ጣራ ላይ የሚታየው ቅርጻ ቅርጽ ተመሳሳይነት አለው፡፡ እንደ እኔ ግምት ከሆነ እነዚህ ሳጥኖች የሕንፃው ንድፍ የተቀመጠባቸው ሳጥኖች ይመስሉኛል፡፡ ጠቢቡ ሕንፃውን ሲያንፀው ምናልባት በእንጨቱ ላይ የሠራውን ዲዛይን እየተከተለ ይሆናል፡፡

ከቤተ መቅደሱ ጎን ያለው፣ዛሬ በዕቃ ቤትነት የሚያገለግለው እና ይምርሃነ ክርስቶስ በቤተ መንግሥትነት ይጠቀምበት ነበር የሚባለው ሕንፃ ግን እጅግ ተጎድቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ አቧራውን እንኳን በዘመናዊው የአቧራ መጥረጊያ ማሽን በአንድ ቀን ማስለቀቅ በተቻለ ነበር፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ከአሥር ዓመታት በኋላ የምና ገኘው አይመስለኝም፡፡

ይምርሃነ ክርስቶስ በ939 ዓም አካባቢ ተወልዶ በ1036ዓም አካባቢ ያረፈ የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ነው፡፡ የነገሠው በ996 ዓም አካባቢ ሲሆን ቤተ መቅደሱን ያነፀው በ1018 ዓም አካባቢ መሆኑ ይነ ገራል፡፡ የላሊበላ አብያተ መቅደስ ተጠናቀቁበት ከሚባ ለው ዘመን 1193 ዓም ጋር ስናስተያየው ቢያንስ የሰባ ዐመት ቅድሚያ አለው ማለት ይቻላል፡፡

ይምርሃነ ክርስቶስን የሥነ ሕንፃ፣ የአርክቴክቸር እና የአርኬዎሎጂ ባለሞያዎች ሊጎበኙት ለዛሬው ሥራችን የሚጠቅምም ሀገራዊ ጥበብ ሊሸምቱበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የባለ ሞያዎችን ጥናት እና ምላሽ የሚፈልጉ አያሌ ጥበቦች የፈሰሱበት ሕንፃ ነው፡፡ በተለይም ቦታው ዋሻ ውስጥ በመሆኑ እና ከተራራ ግርጌም በመደበቁ ከብዙዎቹ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተርፎ ታሪኩን እንደያዘ ይገኛል፡፡በመሆኑም ከአካባቢው የተሻሉ መረጃ ዎችን ይሰጣል ባይ ነኝ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአካባቢው ታሪክ እና ቅርስ ትኩረት በመስጠት መንገዱን ለማ ሠራት፣ አካባቢውን ለመጠበቅ፣ለማስተዋወቅ እና ለመከባከብ የክልሉ ባሕል እና ቱሪ ዝም የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነው፡፡

6 comments:

  1. THANKS DN MELAKU BETAM DES YILAL

    ReplyDelete
  2. ዲ/ን መላኩ በርታልን ፤ እንደናንተ አይነት ፤ ለዝች ዘር ፈ ብዙ ችግር ላለባት ቤተክርስቲያናችን በጣም ያስፈልጋታል።የድንግል ልጅ ይርዳሕ!

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን በጣም ደስ ይላል.ረጅም እድሜ እና ጤና ይስጥልን የአገልግሎት ግዜያችሁን ያርዝምልን ዲያቆን መልአኩ እና ዲያቆን ዳንኤል

    ReplyDelete
  4. ዛሬም ቢሆን ካፈርና ከቆረጥ ሺህ ዓመት የሚቆዩ ህንጻዎች ብዙ ገንዘብ ሳይወጣ መስራት ይቻላል። በተለይ አንድ በጣም አየደነቀኝ ያለው በየአካባቢው ከፍተኛ ወጪ አየወጣባቸው ብዙ ሳይቆዩ የሚሰነጣጠቁና ንድፋቸውም ብዙ ኢትዮጵያዊ የማይመስሉ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። በርግጥ ለባለሙያዎቹ በሲሚንቶ ማስራት ቀላልና ጊዜ ቆጣቢ ነው። አላዋቂ ሳሚ አንዳልባል አንጂ ለቅለትና ውበት ብቻ ተብሎ ዘለቄታ የሌለውና አካላዊ ጥቅም የሌለውን ግዙፍ ህንጻ ከመስራት መጠኑ አነስተኛ የሆነና አንደ ይምርሃነ ክርስቶስ ከዘመናት ዘመናት የሚቆይ የቤተክርስቲያን ህንጻ ቀስ አያሉ በምአመናኑ ጉልበት (በአብዛኛው በሰው ጉልበት የሚሰራ ሥራ ነውና) ቢሰራ በረከቱ ቢጨምር አንጂ አይቀንስም። በተለይ በዛሬው ጊዜ አነዚህ የህንጻ ግንባታ ዘዴዎች (ለዘመናት ብዙ ስልጣኔን ያሳለፉ ግን ቀላልና ጊዜ በማይፈጀው ሲምንቶና ሌሎች ብልጭልጭ ነገሮች የተተኩ) በመረጃ መረቡ አማካይነት ሌሎች የሰሩትን ማየትና በቀላሉ ልንማራቸው የምንችል በመሆኑ ቤተክርስትያኗና ምአመናኑ ለዚህ አትኩሮት ሊሰጡ ይገባል ባይ ነን። ሌላው ነገር የተዘነጋ የቤተክርስቲያኗ ሥራ የአካባቢን ተፈጥሮዋዊ ሀብት የመንከባብከብ ሥራ ነው። በርግጥ ሙከራዎች አሉ። ነገርግን አንዚህ ሙከራዎች ከልብ ባለመሆናቸው ውጤቱ አመርቂ አይደለም። በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ምንም አንክዋን ድሮ አባቶቻችን የተከሉት ዛፎች አንዳሉ ቢሆኑም ውስጣቸው በዛፎቹ መሃከል ብንመለከት አፈሩ ተጋልጦና ተሸርሽሮ በረሃ ሆኗል። የዛፎቹ ስርም አግጦ ከመውደቅ በግዚአብሄር ኃይል የቆሙ ይመስላሉ። የዚህ ዋናው ምክንያት ምንም አንክዋን ከአብያተክርስትያናቱ ቅጥር ግብ ውጪ ያለው መሬት መለወጥ ቢሆንም፣ በግቢው ያለውን አፈር ከመሸርሸር በመከላከልና (ሰርዶ ሳርና ቁጥቅዋጦ በመትከል) በዝናብ የመጣ ውሃ አዛው ተጠራቅሞ ወደመሬት አንዲሰርግ በማድረግ መጠበቅ ይቻላል። ይህም ትምህርት መአመናኑን አንድያስተምሩበት ለቀሳውስቱና ለድያቆናቱ ሊሰጥ የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም አንዚህ አውቀቶች ለቤተክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን በተለይ አብዛኛው ድሃ የሆነውንና በአካባቢ ተፈጥሮ መበላሸት በድርቅና ረሃብ አይተጎዳ ላለው ገበሬ የሕይወት ለውጥ ያመጣለታልና።
    ስለነዚህ ዘዴዎች ለማወቅ permaculture ወይም permaculture building ብለው ጎግልን ይጠይቁ።

    ReplyDelete
  5. ከቆረጥ የሚለው ከኮረት ተብሎ ይነበብልኝ

    ReplyDelete
  6. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete