ሰማዕት
ማለት ምስክር ማለት ሲሆን በሃይማኖት ምክንያት የተገደለ፣ መከራ የደረሰበት ሰማዕት ይባላል። (ሐዋ.22፡20) የመጀመሪያዎቹ
የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት ሐዋርያትና አርድዕት ናቸው።
ቅዱሳን
ሰማዕታት የሚባሉት “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ስገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” በማለት በዓላውያን
ነገሥታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት የመሰከሩ ናቸው። በዚህም
ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣
ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።
በእሳት
ተቃጥለዋል፣ በውኃ ተቀቅለዋል፣ በሰይፍ ተመትረዋል፣ በመጋዝ ተተርትረዋል፣ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል (መንኩራኩር የሚባለው
በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ዘመናዊ የወፍጮ መሳሪያ ነው።)፣ እንደከብት ቆዳቸው ተገፏል፣ ወደጥልቅ ባህር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ
መከራ ውስጥ ከሃይማኖታቸው አላፈገፈጉም፤ እንዲያውም ሌሎች “እኔ በእነርሱ አምላክ አመልካለሁ” እንዲሉ አድርገዋቸዋል።