Sunday, April 8, 2012

ሥርዐተ ሰሙነ ሕማማት ... (ክፍል አንድ)


ሥርዐት ምንድን ነው?

          “ወንድሞች ሆይ፡ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዐት አልሔድንምና። “ (2 ተሰ. 3 6)

           ሥርዐት የሥነ ፍጥረት ሕይወት ምሕዋር፣ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ነው። የመዓልቱ በሌሊት፣ የሌሊቱ በመዓልቱ በመሠልጠን ሥርዓተ ዑደትን እንዳይጥስና የመዓልቱ በመዓልቱ የሌሊቱ በሌሊት እየተመላለሰ ዕለታዊ ግብሩን እንዲያከናውን ማንኛውንም ፍጡር ፈጣሪው በሥርዐት አሰማርቶታል። (መዝ. 10519-24)  

          
በተለይ መንፈሳዊያን ልዑካን መንፈሳዊውን ተልእኮ ያለ ሥርዓትና ያለ ሕግ ማካሔድ እንደማይችሉና እንደማይገባም ሐዋርያው አስተማረ። ያለ ሥርዐት ከሚካሔድ ወንድም ተለዩአለ። ስለሆነም በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ እሴቶች ከዚህ ኃይለ ትምህርት የተገኙ መሆናቸውን እያሰብን በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ የሕማማት ሥርዐቶችን ቀጥለን እንመለከታለን።

Saturday, April 7, 2012

ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት



              በዐቢይ ጾም ከሠርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለ መሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጣብ፣ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ 

አለመሳሳም
              በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጠን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት፣ አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሠመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ አያንሾካሾኩእንስቀለውአንግደለውብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያነን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡

             ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝእኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙትብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንንሰላም ለኪብሎ ነው ያታለላት፣ የዲያቢሎስ እና የይሁዳ ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኸው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ሥርወ መሠረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል ይቀጥላልም፡፡