Friday, February 24, 2012

ኪዳነ ምሕረት



ኪዳን የሚለው ቃል ‹‹ቃል›› ከሚለው ጋር እየተዛረፈ በብሉይ ኪዳን 280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳን ደግሞ 32 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ኪዳን›› ቃሉ ‹‹ተካየደ›› ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ምሕረት›› የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡

‹‹
ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ›› ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ (መዝ88.3) ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡

        በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃል ኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡

Sunday, February 19, 2012

ዘወረደ(የዐቢይ ጾም አንደኛ ሳምንት)



ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዐቢይ ጾም የመጀመሪያውን እሁድ ዕለት  “ዘወረደ” በማለት ትጠራዋለች።
እግዚአብሔር በገባዉ ቃልኪዳን መሰረት “…የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” እንዳለ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ የጠፋዉን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መዉረዱን የምናዘክርበት በዓል ነዉ። 

ሰዉ የተሰጠዉን የሞት ማስጠንቀቂያ ባለመጠበቁ ፍርድ ተፈርዶበት፣ መዊተ ስጋ መዊተ ነፍስ ነግሶበት፣ በህይወተ ስጋም እያለ በሞት ጥላ ስር የሚኖር እና በሞት ፍርሃት የታጠረ ነበር። ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይቶ የተስፋ ቦታዉን ለቆ ከዓለመ መላዕክት ወደ ዓለመ እንሰሳ ተጥሎ የፀጋ ልጅነቱን እና ክብሩን አጥቶ በባርነት ዉስጥ እኩያት ፍትወታት ሰልጥኖበት ይኖር ነበር። (መዝ፡- 18፡4-5) 

Sunday, February 12, 2012

ዐቢይ ጾም


በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሕልና ትውፊት  እና ሥርዓት መሠረት በዘንድሮው ዓመት በመጪው ሰኞ የካቲት 12 2004 ( 20 ፌብርዋሪ 2012 ) የሚጀመረው የጾም ወራት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው፣ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡

   ይህ ታላቅ የሆነው የጾማችን ወራት በተለያየ ስያሜ  ይጠራል፡፡
1. ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡

ሌሎች አጽዋማት ከቅዱሳን አበው የወረስናቸው የኑሮአቸው ፍሬዎች (ዕብ.13፤7) ሲሆኑ ይኼኛው ግን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ (ታላቅ) ይባላል፡፡ የጌታ ጾም ስለሆነ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሡበት፣ ድል የሚነሡበት ጾም ስለሆነም ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡


2. ጾመ ሁዳዴ ይባላል፡፡

ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት፣ የመንግሥት ርስት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ጊዜ፣ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ ዐዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ ይህንንም የጌታ ጾም የጌታ ወይም የጌታ ሁዳድ የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታልና ጾመ ሁዳዴ ይባላል፡፡