Sunday, October 7, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 2


የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
  የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን  አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

Thursday, October 4, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 1

የጾም ትርጓሜ
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ - ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ አንድም ጾም ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ይህም ኃጢአቱን ለማስተሰረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥራም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ፍት.ነገ.ፍት. መ. አንቀጽ 15፣564፡፡ በዚህ መሠረት ጾም ማለት ከጥሉላተ መባልዕት /ሥጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል እንዲሁም የአልኮል መጠጦች/ መታቀብ ነው፡፡
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለፈቃደ ሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ ሰው ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት ስንቅ ነው፡፡ ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣ የጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው፣ የጸሎት ምክንያት /እናት/፣ የእንባ መገኛ ምንጭ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡ /ማር. ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/፡፡

Monday, September 24, 2012

መስቀሉ የት ነው ያለው? ክፍል 2

መስቀሉ እንዴት ጠፋ? ከዳንኤል ክብረት
የሀገራችን ሊቃውንት እና መዛግብት መስቀሉ እንዴት እንደ ጠፋ የሚተርኩት ታሪክ የጥንታውያኑን መዛግብት የተከተለ ነው፡፡ በመስከረም 16 እና 17 የሚነበበው ስንክሳራችን የጌታችን መስቀል በጎልጎታ በጌታችን መቃብር እንደነበረ ይተርክልናል፡፡ አይሁድ በመስቀሉ እና በመቃብሩ የሚደረገውን ተአምር አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውንም ያትታል፡፡ እስከ 64 ዓም አይሁድ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ በ64 ዓም አካባቢ ግን አይሁድ ራሳቸውን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ዐመጽ ጀመሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡