“ዘይሁብ
መርሐ ርቱዐ ለቤተ ክርስቲያን -
ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ”
በዲያቆን
ያረጋል አበጋዝ
ቤተ ክርስቲያን የምንላት ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹምና ከማይነገር ፍቅሩ የተነሣ ሰው እስከ
መሆን፣ ሰው ሆኖም በዚህ ዓለም ከኃጢአት በስተቀር እንደ ሰው መኖርን፣ ከዚያም በቀራንዮ ቅዱስ ሥጋውን እስኪቆርስላትና ክቡር
ደሙን እስኪያፈስላት ድረስ የደረሰላትና የመሠረታት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ "ወነአምን በአሐቲ ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት" የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል መሠረትነት
በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት በምእመናን አካልነት የተመሠረተች ጉባኤ ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስንል የዚህ ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን
(ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣ ...) እና ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡
በሰማይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ) የዚህ ዓለም ጣጣቸውን ጨርሰው የሄዱ፣ ድል አድርገው የድል አክሊላቸውን ለመቀበል
እርሱ የወሰነውን ጊዜ የሚጠባበቁ ቅዱሳን ኅብረት ስለሆነች አትናወጽም፤ ስለሆነም ሊቃውንት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ድል
አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን (Church Triumphant) ይሏታል፡፡ ገና በዚህ ዓለም በጉዞና በፈተና ላይ ያለችውን የአንዲቷ
ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችውን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ደግሞ ገና በተጋድሎ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን (Church
Militant) ይሏታል፡፡


