1. ባሕረ ሐሳብ ማለት ምን ማለት ነው?
ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽም የሐሳብ ባሕር ማለት ነው፡፡ በዓላት እና አጽዋማትን ለማውጣት የመደመር፣ የመቀነስ፣ የማባዛት ስሌትን ብቻ ሳይሆን ሐሳበ ፀሐይን፣ ሐሳበ ወርኅን፣ ሐሳበ ከዋክብትን ሐሳበ ዐበቅቴን ወዘተ አጠቃሎ የያዘ እንደ ባሕር የሰፋ በመሆኑ የሐሳብ ባሕር ተብሏል፡፡ የዘመን አቈጣጠር ማለት ስለማሕበራዊ ኑሮ ጠቄሜታና የሃይማኖት ተግባሮች ለማከናወን በሚያገለግል መልኩ ተፈጥሮአዊውን የወቅቶች ክፍፍል እርስ በርሳቸው የማመቻቸት ዘዴ ነው፡፡
ማርቆስ ወንጌላዊ
|
ሐሳበ ዘመን የዘመን አቆጣጠር ማለት ሲሆን የሐሳበ ዘመን ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ወይም ዓመተ ዓለም ማለት ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም የባሕር አዝዋሪቱ፣ መንገዱን፣ ጥልቀቱና ስፋቱ ረዥምና ሰፊ እንደሆነ የባሕረ ሐሳብ ትምህርትም መንገዱን ስፋቱ ልዩ ልዩ በሆነ የአጽዋማትና የሱባዔያት ምሥጢር የተሰናዳ ስለሆነ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር /የጊዜ ቀመር/ አንድ ዓመት በውስጡ ዐሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ አራቱ ክፍላተ ዘመን የሚባሉት፡-
1-
ክረምት - ከሰኔ 26 ቀን - መስከረም 25 ቀን፣
2-
መፀው /መከር/ - ከመስከረም 26 ቀን - ታኅሣሥ 25 ቀን፣
3-
በጋ /ሐጋይ/ - ከታኅሣሥ 26 ቀን - መጋቢት 25 ቀን፣
4-
ጸደይ /በልግ/ - ከመጋቢት 25 ቀን - ሰኔ 25 ቀን ናቸው፡፡