ሐዋርያዊትና
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ
ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ያጠመቃችኋቸው፡፡›› (ማቴ. 28÷19)
ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ
በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡
ይህንን የወንጌል
ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም
ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ
ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም ‹‹ምን
እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38)፡፡
2006 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር |