አበቅቴ እና መጥቅዕ
አበቅቴ የሚለው ቃል አፖክቴ ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ
ሲሆን ተረፈ ዘመን፣ ስፍረ ሌሊት ቁጥረ ሌሊት ማለት ነው። ተረፈ ዘመን የተባለበት ምክንያት ፀሐይና ጨረቃ በአንድ መስኮት
ውስጥ የተፈጠሩ ሲሆን ዑደት በሚያደርጉ ጊዜ ግን በተለያየ ቀን ዑደታቸውን ይፈጽማሉ። በዚህም የተነሳ በመካከላቸው የቀናት
ልዩነት የሚኖር ሲሆን ይህ ልዩነት አበቅቴ ወይም ተረፈ ዘመን ይባላል።
የፀሐይ አንድ ዑደት 365 ቀን ከአስራ አምስት ኬክሮስ /ከስድስት ሰዓት/
ሲሆን የጨረቃ አንድ ዑደት ደግሞ 354 ቀን ከሃያ ሁለት ኬክሮስ ነው። ስለዚህ የጨረቃ ዑደት ፀሐይ ላይ ለመድረስ አስራ አንድ
ቀን ይቀራታል። ይህ ቀሪ /አስራ አንድ/ አበቅቴ እንግዲህ ጥንተ
አበቅቴ አስራ አንድ ቢሆንም ይህ ቁጥር በየዓመቱ አስራ አንድ ቀን ስለሚጨምር ማለትም የጸሐይና የጨረቃ ዑደት በመጀመሪያው
ዓመት አስራ አንድ ቢሆንም በሁለተኛው ዓመት የራሱ አስራ አንድና ያለፈው ዓመት አስራ አንድ ሲደመር ሃያ ሁለት ይሆናል።
የሶስተኛው ዓመት አስራ አንድ ሲጨመር ሰላሳ ሶስት ይሆናል። ማንኛውም ቁጥር ከሠላሳ ከበለጠ በሠላሳ ይገደፋል ፡፡ስለዚህ
ሠላሳ ሶስት በሠላሳ ሲገደፍ ወይም ለሠላሳ ሲካፈል አንድ ጊዜ ደርሶ ሶስት ይቀራል። ሶስት አበቅቴ ሆነ ማለት ነው። እንደዚህ
በየዓመቱ አስራ አንድ እየጨመርን አበቅቴን ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን የብዙ ዓመታት በሆኑ ቁጥር በዚህ መልኩ ማውጣቱ
ስለሚከብድ በቀላሉ የየዘመኑን ወይም እኛ የምንፈልገውን ዓመተ ምህረት አበቅቴ ማውጣት እንችላለን። ይህንንም በሶስት ዓይነት
መንገድ ማውጣት ይቻላል።
1ኛ. አበቅቴን በወንበር ማውጣት
ከዚህ ቀደም ስለ ወንበር ስንመለከት ወንበር የሚጠቅመው የየዘመኑን አበቅቴና መጥቅዕ ለማግኘት ነው
ብለናል። ስለዚህ ወንበርን በጥንተ አበቅቴ አባዝተን የምናገኘውን ቁጥር በሠላሳ ገድፈን ወይንም ለሠላሳ አካፍለን የምናገኘው
አበቅቴ ይሆናል።