Sunday, April 7, 2013

ገብር ኄር - የአብይ ጾም 6ኛ ሳምንት



 ይህ ሳምንት የዐብይ ጾም ስድስተኛው ሳምንት ሲሆን እንደሌሎቹ ሰንበታትና ሳምንታት ሁሉ ይህም ሳምንት የራሱ የሆነ መጠሪያ አለው:: ገብር ኄር ይባላል:: ትርጓሜውም በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው::በዚህ ሳምንት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈው መልእክት ከባለፈው ሳምንት/ደብረ ዘይት/ የቀጠለ ነው:: የዐብይ ጾም አምስተኛው ሳምንት /ደብረ ዘይት/ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚታሰብበት  ሲሆን ይሄኛው ሳምንት ደግሞ ነቢዩ ዳዊት “እስመ አንተ ትፈድዮ ለኵሉ በከመ ምግባሩ/አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህና/ መዝ 61፡12 እንዳለ ጌታ ዳግም ሲመጣ ለሁላችንም እንደ ሥራችን ዋጋችንን እንደሚከፍለን የምናስብበት ሳምንት ነው::
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ስለ ዳግም ምጽአቱና ስለሚሆነው ምልክት ሲጠይቁት በመጀመሪያ በ70 ዓ ም አካባቢ የሚሆነውን የኢየሩሳሌምን ጥፋት ከዚያም በኋላ እሱ ዳግም ሲመጣ የሚሆኑትን ምልክቶች ከነገራቸው በኋላ ከዚሁ ጋር አያይዞ የእርሱን መምጣት ተከትሎ የሚሆነውን ክስተት በሦስት ምሳሌዎች ለጊዜው ለደቀመዛሙርቱ በመጨረሻ ግን ለሁላችንም እንዲሆን ነግሮናል::
የመጀመሪያው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመውን የጌታውን አደራ በሚገባ በመወጣቱ በጌታው ዘንድ በተመሰገነው በልባሙ ባሪያ ምሳሌነት ለመልካም የሚተጉ ሰዎችን አስደሳች ፍጻሜ፣ እንደዚሁም በተቃራኒው የጌታውን አደራ ችላ በማለት የማይገባ ሥራ በመሥራት ጊዜውን ባባከነው ክፉ ባሪያ ምሳሌነት የቸልተኞችን አስከፊ ፍጻሜ የሚያሳየው ነው (ማቴ 24፡45-51)::
ሁለተኛው የሙሽራውን መምጣት በዝግጅት ይጠብቁ በነበሩ በአምስቱ ብልሆች ደናግላን ምሳሌነት የዝግጁዎችን ስኬታማ ፍጻሜ፣ እንደዚሁም ባልተሟላ ዝግጅት የሙሽራውን መምጣት ሲጠባበቁ በነበሩ በአምስቱ ሰነፎች ደናግላን ምሳሌነት ማስተዋልና ጥንቃቄ በጎደለው ሕይወት የሚኖሩ ሰዎችን ፍጻሜ የሚያሳየው ነው ፡፡ (ማቴ 25፡1-13)
ሦስተኛው ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በተለየ መልኩ በዚህ ሳምንት በይበልጥ የሚታሰቡ ከጌታቸው ዘንድ መክሊትን የተቀበሉ ባሮችን ታሪክ የያዘው ምሳሌ ነው::