Friday, April 18, 2025

 




✝️➕✝️➕✝️➕✝️➕✝️➕

 ዕለተ ዓርብ

✝️➕✝️➕✝️➕✝️➕✝️➕


➕ *ዓርብ ማለት መካተቻ መፈጸሚያ ማብቂያ ማለት ነው።* 


 *፩,* ✝️➕ እግዚአብሔር ፳፪ቱን ሥነፍጥረት ፈጥሮ የጨረሰበት ዕለት ነው። "እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።

እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአል"    ዘፍ ፪÷ ፪


 *፪* , ✝️➕አዳም አርባ ቀን የምድር ኑሮውን ጨርሶ ወደ ገነት የገባበት ዕለት  ነው ። "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው" ዘፍ ፪ ÷ ፲፭


 *፫,* ✝️➕ አዳም የገነት ኑሮውን ፈጽሞ የተባረረበት ዕለት ነው። "ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ"    ዘፍ ፫ ÷ ፳፫~፳፬


 *፬,* ✝️➕እስራኤል ፵ ዘመን መና ከደመና እየወረደላቸው ሲመገቡ ኑረው ርደተ መናው ተፈጽሞ የከነአንን ፍሬ መመገብ የጀመሩበት ዕለት ነው ። "ወዓርበ መና በፊንቆን እን 

እንጀራም በፊንቆን ቀረ የከነዓንንፍሬም መመገብ ጀመሩ" 


 *፭,* ✝️➕ *የክርስቶስ የሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጉዞ የነፍሳት አምሥት ሺኽ አምስት መቶ ዘመን ጉዞ ተፈጸመ "ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ “ተፈጸመ፡” አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ"* ዮሐ ፲፱÷፴


➡️ *ሲኦል ተነዋወጠች መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ* 

➡️ *ምድርን ያለጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት* 

➡️ *ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ* 

➡️ *ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ተወው ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወርዳ ከዚያው ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች ሲኦልንም በዘበዘች ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች* 

➡️ *ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ ነፍሱም በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ፈታች* 

           ሃይ አበ ዘአትና ፳፮ ÷ ፲፰~፳፩


 *፮,* ✝️➕ *በዕለተ ከእሑድ እስከ ዓርብ ተፈጥሮ በዕለተ ዓርብ ፍጻሜ ያገኘ ሥነ ፍጥረት በኅልፈት ፍጻሜ የሚያገኝ በዚህ እለት ነው ።* 

ወሶበ ተፈጸመ ኵሉ አሜሃ ለእሊአሁ ለኅሩያኒሁ ወለጻድቃኒሁ ደብተራ ብርሃን ይተክል ወመንጦላዕተ ብስሃን ይሰፍሕ ዘቦ ፯ቱ ምሥዋር 

ትርጕም፦ ሉሉ ከተፈጸመ በኋላ ያን ጊዜ ለመረጣቸው ለወዳጆቹ ለጻድቃኖቹ የብርሃን ድኖኳን ይተከላል ሰባት መሠወሪያ ያለው የብርሃን መጋረጃ ይዘረጋል 

       ቅዳሴ አትናቴዎስ  ፩÷ ፺፫


✝️➕✝️➕✝️➕✝️➕✝️➕

Saturday, April 5, 2025

ኒቆዲሞስ (የዐቢይ ጾም 7ኛ ሳምንት)




ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የምስራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዛ ስለነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻየሚያወጣቸው መሲህ ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ለብዙ ዘመናትበባርነት ቀንበር ስለደከመ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክሞ ነበር፡፡ መሲህ ቢመጣእንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ ሰራዊት አስከትሎ ነው ብለውያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ክርስቶስን መሲህ ነኝ ብሎ ሲመጣ ለመቀበልፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጦር ሳይዝ ሰራዊት ሳያስከትልእንዲሁ ባዶ እጁን አርነት ላወጣችሁ መጥቻለሁ እያለ ደጋግሞ ተናግሯልናነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው እስራኤላዊ የክርስቶስን መሲህነት ቢጠራጠርናባይቀበለውም፣ በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው  የተከተሉትም  ነበሩ፡፡ለዚህም  ትልቅ ማሳያ የሚሆነን ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለአይሁዳዊ ነው፡፡ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህን  ታላቅ ሰው ለማዘከርየዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሁድ በእርሱ ስም ሰይማ ታከብረዋለች ፡፡ ተከታዮቿምዕመናንም የእርሱን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለችታስተምራለችም፡፡  
ኒቆዲሞስ ማነው?
፩. ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው  ዮሐ 3-1

Saturday, May 1, 2021

ትንሣኤ ዘክርስቶስ - የክርስቶስ ትንሳኤ



ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው  ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ)÷ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውም)÷ በእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።

Tuesday, August 7, 2018

ፍልሰታ ኪዳነ ምህረት


«ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ»
ቅዱስ ያሬድ
click here For PDF
ፆመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ምእመናንን ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመሄድ አሊያም በአጥቢያቸው በመሰባሰብ እመቤታችን ለሐዋርያት በተለያዩ ጊዜያት ተገልጻ ሞትና ትንሣኤዋን የገለጸችበትን ሁኔታ ያስባሉ፡፡ ጌታም እናቱን መንበር አድርጎ ቀድሶ ማቁረቡን ይዘክራሉ በዚህ ወቅት በፆም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት ይማጸናሉ፡፡ ሁሉም እንደሚደረግላቸው ያምናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም «በእውነት ተነሥታለች» ብለው በደስታ የፆሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡
 ሞትና ትንሣኤዋ እንዴት ነው ቢሉ፡- የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡

Friday, September 9, 2016

የዘመን አቆጣጠር ባሕረ ሐሳብ -ክፍል 1


1. ባሕረ ሐሳብ ማለት ምን ማለት ነው?

ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽም የሐሳብ ባሕር ማለት ነው፡፡ በዓላት እና አጽዋማትን ለማውጣት የመደመር፣ የመቀነስ፣ የማባዛት ስሌትን ብቻ ሳይሆን ሐሳበ ፀሐይን፣ ሐሳበ ወርኅን፣ ሐሳበ ከዋክብትን ሐሳበ ዐበቅቴን ወዘተ አጠቃሎ የያዘ እንደ ባሕር የሰፋ በመሆኑ የሐሳብ ባሕር ተብሏል፡፡ የዘመን አቈጣጠር ማለት ስለማሕበራዊ ኑሮ ጠቄሜታና የሃይማኖት ተግባሮች ለማከናወን በሚያገለግል መልኩ ተፈጥሮአዊውን የወቅቶች ክፍፍል እርስ በርሳቸው የማመቻቸት ዘዴ ነው፡፡
ማርቆስ ወንጌላዊ

ሐሳበ ዘመን የዘመን አቆጣጠር ማለት ሲሆን የሐሳበ ዘመን ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ወይም ዓመተ ዓለም ማለት ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም የባሕር አዝዋሪቱ፣ መንገዱን፣ ጥልቀቱና ስፋቱ ረዥምና ሰፊ እንደሆነ የባሕረ ሐሳብ ትምህርትም መንገዱን ስፋቱ ልዩ ልዩ በሆነ የአጽዋማትና የሱባዔያት ምሥጢር የተሰናዳ ስለሆነ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር /የጊዜ ቀመር/ አንድ ዓመት በውስጡ ዐሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ አራቱ ክፍላተ ዘመን የሚባሉት፡-

1-    ክረምት - ከሰኔ 26 ቀን - መስከረም 25 ቀን፣

2-     መፀው /መከር/ - ከመስከረም 26 ቀን - ታኅሣሥ 25 ቀን፣

3-    በጋ /ሐጋይ/ - ከታኅሣሥ 26 ቀን - መጋቢት 25 ቀን፣

4-    ጸደይ /በልግ/ - ከመጋቢት 25 ቀን - ሰኔ 25 ቀን ናቸው፡፡


Wednesday, September 7, 2016

ቅዱስ ሩፋኤል ጦቢት እና ጦቢያ

ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2 ፡፡
በየዓመቱ ጳጉሜ 3 የቅዱስ ሩፋኤል መልአክ መታሰቢያ ነው ፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡

Saturday, February 27, 2016

ዐቢይ ጾም



በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ባሕልና ትውፊት  መሠረት በዘንድሮው ዓመት  ሰኞ የካቲት  28 2008 ( ማርች 7   2016 ) የሚጀመረው የጾም ወራት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው፣ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡





   ይህ ታላቅ የሆነው የጾማችን ወራት በተለያየ ስያሜ  ይጠራል፡፡
1. ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡

ሌሎች አጽዋማት ከቅዱሳን አበው የወረስናቸው የኑሮአቸው ፍሬዎች (ዕብ.13፤7) ሲሆኑ ይኼኛው ግን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ (ታላቅ) ይባላል፡፡ የጌታ ጾም ስለሆነ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሡበት፣ ድል የሚነሡበት ጾም ስለሆነም ዐቢይ ጾም ይባላል፡፡

Wednesday, January 7, 2015

የመገለጥ ሃይማኖት በአስተርእዮ

በዲያቆ ብርሃኑ አድማስ
የጥምቀት በዓል በጎንደር
ሃይማኖት የምንቀበለውና የምንጠብቀው እንጂ የምንሠራውና የምናሻሽለው አይደለም ከታኅሣሥ 29 ቀን ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት /ጊዜ/ ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ወራት/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በታኅሣሥ 29 ቀን የጌታችን ልደት ስለሆነ በዚህ አምላክ በሥጋ የተገለጠበት በዓል ይከበራል፡፡ ጥር 11 ቀን ደግሞ በጌታችን ጥምቀት የሥላሴ አንድነት ሦስትነት በይፋ የተገለጠበት ነው፡፡ ጥር 12 ቀን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ማስተማር በጀመረበት ጊዜ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ አምላክነቱን በይፋ የገለጠበት በዓል ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ዓበይት መገለጦች ወቅቱን በአጠቃላይ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተገለጠበትን መታሰቢያ አደረጉት፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን ትክክለኛ ሃይማኖት ከሚያሰኙት መሠረታዊ ነጥቦች ዋነኛውና ቀዳሚው የመገለጥ ሃይማኖት /Revealed Religion/ መሆኑ ነው፡፡