Saturday, November 22, 2014

ጾመ ነቢያት“መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።” ፩ቆሮ.፰፡፰ 

ዳግመኛም ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፡ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሰለጥንብኝም መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው” ብሏል።
‘አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፡፡’’ ኢዩ.፪፡፲፪ 

‘በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ፡፡ ጉባኤውንም አውጁ፡፡’’ ኢዩ.፪፡፲፭ 

ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ማለት ነው፡፡ ወይም ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጉመዠውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና አለው፡፡ ከጥንት ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ ዘጸ.፴፬፡፳፰ 

በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰውና ቁጣው የሚበርደው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ ዮና.፫፣፭-

በአዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ ማቴ.፬፡፪ ሉቃ.፬፣፪፡፡ በዚህም በስስት፣ በፍቅረ ነዋይና በትዕቢት የሚመጣብንን ጠላት ዲያብሎስን በጾም ድል እንደምናደርገው አሳይቶናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር ርኩስ መንፈስ በጾም የሚወገድ መሆኑን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ማቴ.፲፯፡ ፳፩፤ ማር. ፱፡፪፡፡ በመሆኑም ጾም ለእኛ ታላቅ ጸጋና ኃይላችን ነው፡፡

ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እያሉ ነበር። የሐዋ.፲፫፡፪ ይህም የሚያመለክተው ጾምና ጸሎት የማይነጣጠሉ መሆናቸውና ጾምን ከጸሎት ጋር ስናስተባብር መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀርበን ነው፡፡ በጾም የተዋረደ እና ለጸሎት የተጋ ሰውነት ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ የተዘጋጀ በመሆኑ እግዚአብሔር ያዘናል እኛም እንታዘዛለን፡፡ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ የሐዋ.፲፫፡፫፣ ፬፡፳፭፡፡ እነ ቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ክብር ያገኙት በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ማልደው ነው፡፡ የሐዋ.፲፡፳፡፡ ጾም እንኳን የጠበቅነውን ቀርቶ ያልጠበቅነውንና ፈጽሞም የማይገባንን ጸጋና ክብር የሚያሰጥ ነው፡፡

ስለዚህ ጾም ማለት አንድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በቀር ለማንም ወይም ለምንም የበላይ ኃይል ባርያ፣ ተገዥ ወይም አገልጋይ አለመኾኑን የሚያረጋግጥበት፣ በውስጡ ያሉትን የክፉው ወገን የኾኑትን የኃጢአት ጠንቆች አዳክሞ የበጐው ወገን የኾኑትን ጸጋዎች የሚያሰፍንበት፣ ማንኛውንም ዓይነት የነፍስ ፈተናና የሥጋ መከራ ተቋቁሞ የሚያሸንፍበት፣ ሃይማኖቱንና ምግባሩን የሚያጠናክርበት፣ የፍጹም ትዕግሥትና ተስፋ ባለቤት ለመኾን የሚበቃበት፣ የሥጋና የነፍስ አካላቱን በእውነተኛው ጤንነት የሚጠብቅበት ፍቱንና ኃይለኛ መሣርያ ነው ማለት ነው፡፡

በሕገ ልቡና ከነበሩ አበው አንሥቶ በዘመነ ኦሪት እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በተለያዩ ጊዜአት የነበሩት ቀደምት አበው፣ ነቢያት፣ ነገሥታት፣ ካህናት በጾምና በጸሎት ጽሙድ ሆነው እግዚአብሔር አምላካቸው በይቅርታ እንዲጐበኛቸው ኃይሉን እንዲያጐናጽፋቸው ተማጽነውታል፡፡ የመዳናቸውን ቀን በመጠባበቅ የአባታቸውን የአዳምን ርስት ይወርሱ ዘንድ ተስፋ በማድረግ በጾምና በጸሎት ያሳልፉ ነበር፡፡

የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ ከኃጢአት ቁራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ለአምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን ሥጋንና ቅቤን ወተትና ዕንቁላልን ማራቅ ታዟል፡፡ባልና ሚስትም በአንድ ምንጣፍ አይተኙም፡1ቆሮ.65፡፡ ‘ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ነዑድ ነው፣ክቡር ነው፡፡’’ እንደተባለ ጾመኛው ለምሳው ወይም ለእራቱ ያለወን ወጪ ነዳያንን እንዲረዳበት ለደኩማን ድርጅት ቢሰጥ ወይም በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን ቢመጸውት ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡

ጾም የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ ከኃጢያት ለመንጻት ስለራስ የታሰበውን ለነዳያን በመስጠት የሚጾም መሆኑን መረዳት አለብን ፡፡ ጾም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ነው፡፡ በዲዲስቅልያ 15 ‘ለሚያሳድዱህ ጹምላቸውተብሏል ፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዙትን በስደትና በምርኮ ያሉትንም በጾም ወራት ማስታወስና ስለ እነርሱ መጸለይ ይገባል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ክፉ ከማየት ክፉ ከመናገር እና ክፉ ከመስማትም ጥምር መጾም እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት የታነጸችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም መጾም የሚችል ሁሉም እንዲጾማቸው መጀመርያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የደነገገቻቸው የዓዋጅ አጽዋት አሏት፡፡ ከእነዚህም አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ 

“ጾመ ነቢያት /ጾመ ድኀነት” - ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሰ 28 ቀን ያለው ነው፡፡ ጾመ ነቢያት መባሉ ነቢያት ስለጾሙት፤ ጾመ ድኀነት መባሉ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ጠፍቶ ደኀንነት የተገኘበት ስለሆነ ነው። ይህን ጾም የምንጾመው ነቢያት በየዘመናቸው ስለመሲሕ መምጣት በናፍቆት በመጠባበቅ ይጾሙ ይጸልዩ ሰለነበር የእነርሱን አርአያ ተከትለን የክርስቶሰን ልደት ከማክበራችን ቀደም ብለን ይህን ጾም እንድንጾም በሐዋርያት ቤተክርስቲያን ሥርዐት ተሠርቷል፡፡ አጀማመሩ ስንክሳር መንፈቀ ኅዳር ስለሚል ጾሙ ኅዳር 15 ቀን ይጀምራል፡፡ ‘ወጥንተ ዚአሁ መንፈቀ ኅዳር ወፋሲካሁ በዓለ ልደት፡፡‘ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው በዓለ ልደት ነው እንዲል፡፡

በአጠቃላይ “ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጐ ምግባራት ሁሉ መጀመርያ፣ የጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው፣ የንጽሕና መገለጫ፣ የጸሎት ምክንያት እናት፣ የእንባ መገኛ መፍለቂያዋ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጐ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትደረግ መድኃኒተ ነፍስ ናት” ይላታል ሶርያዊው ቅዱስ ይስሐቅ /ማር.ይስሐቅ. አንቀጽ ፬፡ምዕ./፡፡

ጾም ወደ እግዚአብሔር ለተመለሰ ሕዝብ ምልክት ነው፡፡ ‘አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፡፡’’ ኢዩ.212፡፡ ‘በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ፡፡ጉባኤውንም አውጁ፡፡’’ ኢዩ.215፡፡ አዳም ከማዕረጉ የተዋረደው በመብል ምክንያት ነው፡፡ ዘፍ.31¬-24 ፡፡ ከይሁዳ ወደ ቤተል ተልኮ የነበረው የእግዚአብሔር ሰውም የተቀጣው አትብላ የተባለውን በመብላቱ ነው፡፡ 1ነገ.131¬-34 ፡፡ በአንጻሩም በአስቴር ዘመን አይሁድ ከእልቂት የዳኑት በመጾማቸው ነው፡፡አስ.416¬-17፡፡ ስለዚህ ጸሎት ከጾም ጋር ሲተባበር መልካም ነው ፡፡

 ‘ስለዚህም ነገር ጾምን፣ ወደ እግዚአብሔር ለመንን እርሱም ተለመነን፡፡እንዲል ዕዝ.823 ፡፡ የኃጢአትን ኃይል በጾም ለማድከምና ነፍስን ለማበረታታት ቅብአትነት ካላቸው ሥጋዊ ምግቦች መከልከል ተገቢ ነው፡፡ ‘ጉለበቶቼ በጾም ደከሙ ሠጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳእንዲል መዝ.10824፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ እና ዳንኤል የቤተ መንግሥትን የድሎት ምግብ ንቀው በጥሬ እና በውኃ ተወስነው በመጾማቸው ፊታቸው አምሮ ሥጋቸው ወፍሮ ተገኘ፡፡እግዚአብሔም በትምህርትና በጥበብ ሁሉ ዕውቀትን እና ማስተዋልን ሰጣቸው ፡፡ዳን.18-21፡፡ ለመብል ለመጠጥ መገዛት መንፈሳዊውን ሕይወት ማርከስ ነው፡፡‘ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ ፡፡’’ የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ዳን.፩፡፰ ጾመኞቹ ሦስቱ ወጣቶች ወደ እሳት፣ ዳንኤል ደግሞ ወደ አንበሶች ጉግጓድ ቢጣሉ ሁሉም ዳኑ፡፡ ዳንኤል በጾሙ ወራት ለአምሮት ለቅንጦት ከሚበሉ ምግቦች ይከለከል እንደ ነበር፤ “እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ ፡፡ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፡፡ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፡፡ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት (ቅቤ) አልተቀባሁም፡፡” በማለት በጾም ወቅት ከሁሉም መቆጠብ እንዳለብን ገልጿል። ዳን.፲፡፪

 የሥጋን ምኞት የዓይንን አምሮት ማሸነፍ እንዲህ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ሰዎች ጮማቸው፣ ማራቸው፣ እንጀራቸው፣ ወተታቸው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ “አድምጡኝ በረከትንም ብሉ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው፡፡ ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፡፡” ኢሳ. ፶፭፡፪ “ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፡ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” እንዲል፡፡ መዝ. ፻፲፰፡፻፫፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤልም “የእግዚአብሔር ቃል በአፌ ውስጥ እንደማር ጣፈጠኝ” ብሏል፡፡ ሕዝ.፫፡፫፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ሰይጣንን አሳፍሮታል፡፡ ማቴ፬፡፬ 

እኛም ዛሬ በጾም ወራት ብሉ የሚሉንን እንዲህ ልናሳፍራቸው ይገባል፡፡ በዚህ በመጨረሻው ዘመን መስቀልን የሚጠሉ ማለትም በመስቀል ላይ የተፈጸመውን ቤዛነት የሚንቁ መስቀልን የማያከብሩና የማይሳለሙ ነውር ኃጢአት ክብር የሚመስላቸው አሳባቸውን ምድራዊ ያደረጉ ሰዎች ሆዳቸውን ስለሚያመልኩ አይጾሙም፡፡ ፊል.፫፡፲፰

“ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው” ፩ቆሮ.፮፡፲፪¬-፲፫ እንግዲህ የማይጠቅመውን ነገር መተው ብልህነት ነው፡፡

በዕብራውያን መልዕክቱም “ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ልባቸሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም በዚህ የሚሠሩባት አለተጠቀሙምና፡፡” ዕብ.፲፫፡፱ በጊዜአችን ጾም አይጠቅምም የሚለው እንግዳ ትምህርት በመሆኑ በዚህ አንወሰድ። “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ ለእግዚአብሔር ደስ ያሰኛልና በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው፡፡ ሮሜ.፲፬፡፲፯

ይህ የሚያስተምረን የእግዚአብሔር መንግሥት በመብልና በመጠጥ እንደማትወረስ ነው፡፡ አንድም ቢፈጽሟት መንግሥተ ሰማያትን የምታወርስ፤ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ፍቅርን ሰላምንና እምነትን እንጂ መብልን እና መጠጥን አትሰብክም ማለት ነው፡፡ አንድም በመብል በመጠጥ ለጸና ሰውነት መንግሥተ ሰማያት የተባለች ወንጌል አትስማማውም ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን ሰዎች እስከ ዘለዓለሙ በሰዎች ዘንድ የሚመሰገኑት በጾምና በጸሎት ተወስነው ሰውነታቸውን ለመብል ሳይሆን ለክርስቶስ በማስገዛት ደስ በማሰኘታቸው ነው፡፡

ወገኖቼ ጾም አይጠቅምም ብለን ለመብል ለመጠጥ ከምንጓጓ ይልቅ ብሉ ተብለን የታዘዝነውን የክርስቶስን ሥጋ እንብላ። ደሙንም እንጠጣ ይህ የዘላለም ሕይወት ይሆነናል፡፡ ዮሐ.፮፡፶፫ አንዳንዶች ዛሬ አባቶች ማቅ ለብሰው አመድ ላይ ተኝተው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሠሩልንን ሥርዓት በመናቅ በፈቀድኩት ጊዜ መጾም እችላለሁ ይላሉ፡፡ ዳሩ ግን መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚጓዙበት ሰፊ ጎዳና ሳይሆን ጠባብ ነው፡፡ ማቴ.፯፡፲፫ እንኳን ለመንፈሳዊው ሥርዓት ለሥጋዊውና ለዓለማዊው ሥርዓት እንኳን እንድንገዛ ታዘናል፡፡ “ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፡፡” እንዲል፡፡ ፩ኛጴጥ. ፪፡፲፫ 

ምንጭ፡¬- (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣መዝገበ ታሪክ ፩፣እንዲሁም የኢ///ቤተክርስቲያን ታሪክ ከሚለው ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ መጽሐፍ የተወሰደ)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

 
 

4 comments:

 1. "Kalehiwot yasemalin !!!"

  ReplyDelete
 2. ቃለ ኅይወትን ያሰማልን

  ReplyDelete
 3. ወንድሜ ዲያቆን መላኩ ቸሩ አምላክ ረጅም እድሜአና ጤና ይስጥልን ። ለኛም ሰምተን የምንተግብርበት ብሩህ ልቦና ይስጠን ።አሜን!

  ReplyDelete
 4. K.Hyiwot Yasemalin!

  ReplyDelete