Tuesday, September 9, 2014

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ

እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ

በሰላም በጤና አሸጋገረዎ
ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
ቅዱስ ሉቃስ ሀገሩ አንጾኪያ ነው፡፡ አስቀድሞ ከ72ቱ አርድእት ወገን የተቆጠረ ሲሆን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወርዶ ወነጌልን ሰብኳል ከሐዋርያወ ቅዱስ ጳውሎሰ ጋረ የተገናኘውም በዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የሕክምና ሙያ የነበረው ሲሆን ያጠናውም ከአቴናና እስክንድርያ ሊቃውንት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሙያው በተጨማሪ የሥነ ሥዕል ችሎታም እንደነበረው ይነገራል፡፡ ይህንን ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ባለው ሥዕላዊ አገላለጥ ከማንጸባረቁም ሌላ በእጁ የተሳሉ ሥዕሎች በተለያዩ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡

የቅዱስ ሉቃስ ስዕሎች እመቤታችን ልጇን አቅፋ ( ምስለ ፍቁር ወልዳ) የሳላቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ በተድባበ ማርያም ፤ በደብረ ዘመዶ ፤ በዋሸራ ፤በጅበላ ሲገኙ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል ፡፡

ቅዱስ ሉቃሰ የድንግልና ሕይወት የነበረው ወንጌላዊ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ደቀ መዝሙር በመሆን  አገልግሎታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ67 ዓ.ም. በሮማ በሰማዕትነት ሲያርፍ ሉቃስ ወደ ድልማጥያ መጣ፡፡ በዚያም በሽምግልና ዘመኑ ወንጌልን በመስበክ ላይ እያለ አይሁድና ካህናተ ጣዖት ተባብረው ትምህርቱን በመቃወም ተነሡበት፡፡ መስከረም 20 ቀን 68 ዓ.ም. አይሁድና አረማውያን ጉባዔ አድርገው ነገር በመሥራት ለሮም ንጉሥ ከሰሱት፡፡ በዚያን ዘመን ኔሮን እብደቱ ያየለበት ጊዜ በመሆኑ የቅዱስ ሉቃስን ከሮሜ ማምለጥና ወደ ድልማጥያ መምጣት ሲሰማ 200 ወታደሮችን ላከበት ቅዱስ ሉቃስም የሰዎችን መምጣት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ያሰተምራቸው የነበሩትን ምእመናን ወደየቤታቸው ላከና በድልማጥያ አጠገብ ወደሚገኘው ባሕር ተጠጋ፡፡

በባሕሩ አጠገብ አንድ ዓሣ አስጋሪ ቆሟል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዓሣ አስጋሪው ቀረበና ጨዋታ ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም ወንጌል ይሰብክለት ጀመር፡፡ ዓሣ አስጋሪውም ቅዱስ ሉቃሰ የሚነግረውን ሁሉ ሥራውን አቁሞ በደስታ ያዳምጠው ነበር፡፡ በመጨረሻ እንካ እነዚህ የሕወትን መገንድ ይመሩሃል አለና የያዛቸውን መጻሕፍት ሁሉ ሰጠው፡፡ ያም ዓሣ አስጋሪ እጅግ ተደስቶ ዕቃ በሚያስቀምጥበት ቦታ በክብር አኖራቸው፡፡

ቅዱስ ሉቃሰ መጽሐፉን ሰጥቶት ዘወር ሲል የኔሮን ወታደሮች ተረባረቡና ያዙት፡፡ ከዚያም ወደሮም ተወሰደና የኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ጥቅምት 22 ቀን አንገቱን ተሠይፎ በአሸዋ በተሞላ ከረጢት አስገብተው በተወለደ በ84 ዓመቱ ወደ ባሕር ወረወሩት፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱን ግን ያ ዓሣ አስጋሪ ለዚህ ትውልድ አትርፏቸዋል፡፡


የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃሰ በዓይኑ የተመለከተውን ከሐዋርያትም የሰማውን ጠንቅቆ በማሰብ 24 ምዕራፍ፣ 1149 ቁጥሮች የያዘ ወንጌል አበርክቶልናል፡፡ ወንጌሉን የጻፈው ከ58-60 ዓ.ም. ባው ጊዜ ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ በእሥር ላይ ባገኘው ዕረፍት መሆኑ ይነገራል፡፡

ወንጌሉ የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ሲሆን የተጻፈለትም ቴዎሎስ ለተባለ የመቄዶንያ /ግሪክ/ ባለሥልጣን ነው፡፡ ወንጌሉ የአሕዛብ ወንጌል እየተባለ ይጠራል፤ የተጻፈው ለእነርሱ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ፡-
§  እንደ አሕዛብ ልማደ ትረካን አብዝቶላቸዋል
§  ለአሕዛብ ሱባዔ የመቁጠር ትንቢት የመጠበቅ ልማደ ስለሌላቸው ከነቢያተ ትንቢት በብዛት አልጠቀሰም
§  የጻፈው በግሪክ ቋንቋ ስለሆነ የዕብራይስጥን ቃላት ተርጉሟቸዋል
§  አሕዛብ ከአማልክቶቻቸወ መኻል የፍቅር አምላክ የሚሏቸው አሉ፡፡

ለምሣሌ፡- ለግሪኮቸ ቬነስ የፍቅር አምላካቸው ናት፡፡ ከዚህ ውጪ ያትን ቁጡ፤ ቶሎ የሚፈርዱ፤ ቀንበር የሚያበዙ አድርገው ስለሚያምኑ እጅግ በጣም ይፈሩአቸዋል፡፡ ወንጌላዊው ሉቃሰ ይህንን የአረማውያንን ልማደ ስለሚያውቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በልዩ ልዩ ሁኔታ ገልጦላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ለጠፋው ልጅ አባቱ ያሳየውን የምሕረት ፍቅር /15፤11-82/፣ ጌታ ለዘማዊቷ ያሳየውን ርኅራኄ /23፤7/
§  ከዚህም ሌላ ጌታችን ለድኾችና ለተጠሉት የሚራራ አምላክ መሆኑን በወንጌሉ ገልጧል፡፡ ለምሳሌ፡- የአልዓዛርና የነዌ ታሪክ /16፤19-31/
§  ቅዱስ ሉቃስ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ዘንድ ሰባኬ መነፈስ ቅስ ይባላል፡፡ /1፤35፣ 12፤12፣ 4፤1፣11፤13/ ስለመንፈስ ቅድሱ ጸጋ ደግሞ ደጋግሞ ገልጧል
§  ሰባኬ ጸሎትም ይባላል፡፡ ስለ እመቤታችን፣ ስለ ኤልሳቤጥ፡፡ 1፤3-56 ስለማርያም እንተ እፍረት 7፤38-50 እና ስለ የናይኗ ሴት 7፤11-17 ጽፏልና፡፡

የቅዱስ ሉቃሰ ወንጌል በአገላለጡ ከሌሎች ይለያል፡፡ አቀራረቡ ሥዕላዊ መግለጫን የተከተለ ነው፡፡ ሠዓሊነቱ በመጻሕፍቱም ላይ ተንፀባርቋል፡፡ እንዲሁም በሌሎች ወንጌላት የሌሉ ታሪኮችን አስፍሯል፡፡

1.     የዘካርያስና ኤልሳቤጥ፣ 1፤5-25
2.    የእመቤታችን ብሥራት እና የጌታችንን መወለድ 1፤26-56
3.    የጠፋው በግ፣ 15፤3-7
4.    የጠፋው ድሪም፣ 15፤8-10
5.    የጠፋው ልጅ፣ 15፤11-32
6.    አልዓዛርና ነዌ፣ 16፤19-31
7.    ርኅሩኅ ሳምራዊ፣ 10፤29-37
8.    የኒቆዲሞስና አንዳንድ ሊቃውንት ከቀለዮጳ ጋረ የነበረው ሰው ሉቃስ ነው ብለው ይተረጉማሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ግን ኒቆዲሞሰ መሆኑ ተመዝግቧል፡፡ ግብረ ሕማማት 1 ገጽ 451 የቀለዮጳ፣ 24፤13-35፡፡ እነዚህ ታሪኮች በሉቃስ ወንጌል ባቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

የሐዋርያት ሥራ
የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ከ1-34 ዓ.ም. ያለውን የክርስትና ታሪክ ካሰፈረ በኋላ ቀጣዩንና ከ34-58 ዓ.ም. ያለውን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ጽፏል፡፡

ከምዕራፍ 1-8 ያለው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በኢየሩሳሌም የሚያሳይ ሲሆን ከምዕራፍ 9-12 ያለው ታሪክ ደግሞ በእስጢፋኖስ ሰማኝትነት በተነሣው ስደት የተበተኑት የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ልጆች በአካባቢው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ከምዕራፍ 13 ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች ተከትሎ የጻፈውና ክርስተና በታናሿ እኪያር በአውሮፓ እንዴት እንደተሰበከ የሚያሳየው ክፍል ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው የሮም እሥራቱ በቁም እሥር ላይ ሆኖ ወንጌልን እንዲሰብክ ተፈቅዶለት በነበረ ሰዓት በሮም ከሚኖሩ አይሁድ ጋር በ58 ዓ.ም ስለሃይማኖት ያደረገውን ውይይት ተርኮ ያጠናቅቃል፡፡

ወንጌላዊው ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው በ58/በ59 ዓ.ም/ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ዓመተ ምሕረት በኋላ የተከናወኑትን ለምሳሌ በ60 ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስን መፈታት ዘግይቶም በ64 ዓ.ም. የደረሰውን የሮማ መቃጠልና የአይሁድን ዓመፅ በመጽሐፉ ስላልገለጠው ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃሰ ሐዋርያው ጳውሎስን ተከትሎ ታሪኩን ሲያሰባስብ ከኖረ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ሲታሠር ዕረፍት በማግኘቱ አጠናቅሮ በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀት ለቴዎፍሎስ ልኮለታል፡፡

ሉቃሰ ዘላሕም፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅዱስ ሉቃስ ለምን በላም እንሚመሰል ሲናገር፣ የመድኃኒታችንን መሥዋዕትነት ሐዲስዋ እምቦሳ በወለደች በንጹሕ ላም ፍሪዳ መስሎ ይናገራልና ይለዋል፡፡ እንዲሁም በከብቶች በረት መወለዱን ስለሚናገርና ታረኩም የላም ወተት ለሕፃን ልጅ ቀላል ምግብ እንደሆነ ሁሉ ለአዲሰ አማኝ ቀለል በሎ የቀረበ ስለሆነ በላም ተመስሏል፡፡




10 comments:

  1. Amen enquan abro aderesen !!! I thank you so much for let me know about saint Luke.

    ReplyDelete
  2. Kale hiwot yasemalen MELKAM AMET YADERGELEN!

    ReplyDelete
  3. kale hiwot yasemalen .

    ReplyDelete
  4. KALEHIWOT YASEMALN ,MELKAM ADDIS ZEMEN YIHUNLIHI

    ReplyDelete
  5. Kale hiwoten yasemalen . Sele kidus Lukas endawke seladerkgn .

    ReplyDelete
  6. Egeziabehier yestelen. Endet neh?

    ReplyDelete
  7. egizabiher yibarikachu

    ReplyDelete
  8. እግዚአብሔር ይስጥልን

    ReplyDelete
  9. እግዚአብሔር ይስጥልን

    ReplyDelete