Saturday, June 7, 2014

በዓለ ሃምሳ

ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡ ይህ በዓል ጌታችን በሚያርግበት ጊዜ ደቀመዛሙርቱን አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እሰከ ትለብሱ ኃይለ እም አርያም ሉቃ 2449 ብሏቸው አርጎ ነበር፡፡ተናግሮ የማያስቀር ነውና ባረገ በ10ኛው በተነሣ በ50ኛው ቀን ጰራቅሊጦስን ሰዶላቸዋል ፡፡
ጰራቅሊጦስ ማለት ፡-
1/ ናዛዚ(አጽናኝ) ማለት ነው ከመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች አንዱ ያዘኑትን የተጨነቁትን በተለያየ ነገር ውስጥ ገብተው ግራ የተጋቡትን ሁለ ሰለሚያጽናና ናዛዚ ይባላል ፡፡
2/ከሣቲ (ምስጢር ገላጭ) ማለት ነው የተደበቀውን የሚገልጥ የረቀቀውን የሚያገዝፍ የተሰወረውን የሚያሳይ በመሆኑ ከሣቲ ( ምስጢር ገላጭ) ይባላል ፡፡
3/መጽንኢ (የሚያጸና) በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ገብተው የሚባዝኑት ለመውደቅ የተፍገመገሙትን እንዳይወድቁ የሚደግፍና የሚያጸና በመሆኑ መጽንኢ (የሚያጸና) ይባላል ፡፡

4/መንጽሂ (የሚያነጻ) ማለት ነው በኃጢአት የወደቁትን ከኃጢአታቸው የሚያነጻቸው ነውና መንጽሂ (የሚያነጻ) ይባላል ፡፡
5/ መሠተሰርየ (ይቅር ባይ )ማለት ነው በኃጢአት የወደቁትን የበደሉትን ተጸጽተው ንሰሃ ሲገቡ ይቅር የሚል በመሆኑ መሠተሰርይ ይቅር ባይ ይባላል ፡፡
6/መስተፈሥሔ (ደስታን የሚሰጥ ) ማለት ነው የተጨነቁት፤ ያዘኑትን፤ያለቀሱትን እንባቸውን የሚያብስና ደስታን የሚሰጥ በመሆኑ መስተፈሥሔ (ደስታን የሚሰጥ) ይባላል  ፡፡
በአጠቃላይ ጰራቅሊጦስ ማለት መንፈሰ ጽድቅ ፤መንፈሰ ሕይወት ፤ባሕርያዊ እስትንፋስ ፤ አካላዊ ሕይወት ፤አካላዊ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡
ለምንድን ነው  ቆይቶ በአረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን የላከላቸው ቢሉ ፡-
Ø    10ኛ መዓረግ የተቀመጥን እኛ ነበርንና ወደ ክብራችን ወደ መዓረጋችን እንደመለሰን ለማጠየቅ ነው
Ø    ዳግመኛም 10ሩን ቃሊት ቢጠብቁ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጥ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡
ሐዋርያት ድንግል ማርያምን ይዘው  በሚጸልዩበት  በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ‹ወአስተረአይዎሙ ልሳናተ እሳት ክፋሊት ከመ እሳት ዘይትከፈል ›በእሳት አምሳል የተከፋፈለ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው የሚያውቁት ጸንቶላቸው የማያውቁት ተገልጾሊቸው ሁሉም ከሚያውቁት ቋንቋ በተጨማሪ የማውቁት ቋንቋ ተገልጾላቸዋል ፡፡
በአጠቃላይ ሐዋርያት የሰባ ሁለት  ቋንቋ ባለቤት ሆነው በአደባባይ ስለአምላካቸው በድፍረት መስክረዋል ፤ ስለ እውነት ሲሉ በአደባባይ መከራን ተቀብለዋል ፤ ፈሪዎች የነበሩት ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታጠቃቸው እሳቱን ፤ግርፋቱን፤ስደቡን የሰይፍ ስለቱን ባለመፍራት እራሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ የላይኛው ቤታቸውን አሳምረዎል ፤ ዛሬም በክብር የወርቅ መዝገብ ላይ ሰማቸውን አጽፈዋል ፤ ክብራቸው ይህ ብቻ ሳይሆን አምላካችን በሚመጣበት ወቅት በ12 ነገደ እስራኤል ላይ ለመፍረድ ይመጣሉ፡፡
እንግዲህ በዓለ ጰራቅሊጦስ እኛ ክርስቲያኖች የምናከብረው እንደ ሐዋርያት ምስጢር እንዲገለጥልን ፤እንዲያረጋጋን ፤ይቅር እንዲለን ፤እንዲያጽናናን ፤ደሰታን እንዲሰጠን ነውና ሁላችንም ከዚህ በረከት የታደልን እንድንሆን በዓሉን በንጽሕና በቅድስና ሆነን፤ነጭ ልብስ ለብሰን፤በሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ቅዳሴ በማስቀደስ ፤በዕለቱ በጎ ስራ በመሰራት ልናከብረው ይገባል፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን -  አሜን፡፡

7 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን ወንድማችን አያሳጣን ቃለ ህይወት ያሰማልን ወንድማችን አያሳጣን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን!

    ReplyDelete
  3. Kale hiwot yasemalin. Egziabher yitebkilign.

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን ዲያቆን መላኩ::

    ReplyDelete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን ! ወኀድማችን ፤ አገልጋያችን ዲያቆን መላኩ አዘዘ
    ው።

    ReplyDelete
  6. Amen kale hiweten yasemalen ,tsegawen yabzaleh yeagelgelot gizehen yebarek.

    ReplyDelete