Saturday, September 14, 2013

የዘመን አቆጣጠር ባሕረ ሐሳብ -ክፍል 5 -አበቅቴ እና መጥቅዕ

አበቅቴ እና መጥቅዕ
አበቅቴ የሚለው ቃል አፖክቴ ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ተረፈ ዘመን፣ ስፍረ ሌሊት ቁጥረ ሌሊት ማለት ነው። ተረፈ ዘመን የተባለበት ምክንያት ፀሐይና ጨረቃ በአንድ መስኮት ውስጥ የተፈጠሩ ሲሆን ዑደት በሚያደርጉ ጊዜ ግን በተለያየ ቀን ዑደታቸውን ይፈጽማሉ። በዚህም የተነሳ በመካከላቸው የቀናት ልዩነት የሚኖር ሲሆን ይህ ልዩነት አበቅቴ ወይም ተረፈ ዘመን ይባላል።
 የፀሐይ አንድ ዑደት 365 ቀን ከአስራ አምስት ኬክሮስ /ከስድስት ሰዓት/ ሲሆን የጨረቃ አንድ ዑደት ደግሞ 354 ቀን ከሃያ ሁለት ኬክሮስ ነው። ስለዚህ የጨረቃ ዑደት ፀሐይ ላይ ለመድረስ አስራ አንድ ቀን ይቀራታል። ይህ ቀሪ /አስራ አንድ/ አበቅቴ  እንግዲህ ጥንተ አበቅቴ አስራ አንድ ቢሆንም ይህ ቁጥር በየዓመቱ አስራ አንድ ቀን ስለሚጨምር ማለትም የጸሐይና የጨረቃ ዑደት በመጀመሪያው ዓመት አስራ አንድ ቢሆንም በሁለተኛው ዓመት የራሱ አስራ አንድና ያለፈው ዓመት አስራ አንድ ሲደመር ሃያ ሁለት ይሆናል። የሶስተኛው ዓመት አስራ አንድ ሲጨመር ሰላሳ ሶስት ይሆናል። ማንኛውም ቁጥር ከሠላሳ ከበለጠ በሠላሳ ይገደፋል ፡፡ስለዚህ ሠላሳ ሶስት በሠላሳ ሲገደፍ ወይም ለሠላሳ ሲካፈል አንድ ጊዜ ደርሶ ሶስት ይቀራል። ሶስት አበቅቴ ሆነ ማለት ነው። እንደዚህ በየዓመቱ አስራ አንድ እየጨመርን አበቅቴን ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን የብዙ ዓመታት በሆኑ ቁጥር በዚህ መልኩ ማውጣቱ ስለሚከብድ በቀላሉ የየዘመኑን ወይም እኛ የምንፈልገውን ዓመተ ምህረት አበቅቴ ማውጣት እንችላለን። ይህንንም በሶስት ዓይነት መንገድ ማውጣት ይቻላል።   
1ኛ. አበቅቴን በወንበር ማውጣት
ከዚህ ቀደም ስለ ወንበር ስንመለከት ወንበር የሚጠቅመው የየዘመኑን አበቅቴና መጥቅዕ ለማግኘት ነው ብለናል። ስለዚህ ወንበርን በጥንተ አበቅቴ አባዝተን የምናገኘውን ቁጥር በሠላሳ ገድፈን ወይንም ለሠላሳ አካፍለን የምናገኘው አበቅቴ ይሆናል። 

ምሳሌ 1.2007 አበቅቴ ስንት ነው?
በቅድሚያ ወንበሩን እናወጣለን። ወንበሩን ለማግኘት፦
5500 + 2007 = 7507 ዓመተ ዓለም
ዓመተ ዓለሙን ለዐቢይ ቀመር /532/ እናካፍላለን፤ 7507 ሲካፈል ለ532 14 ጊዜ ደርሶ 59 ይቀራል።
59 ለማዕከላዊ ቀመር /ለ76/ መካፈል ስለማይችል ለንዑስ ቀመር /ለ19/ እናካፍለዋለን። 
5919 ሲካፈል 3 ጊዜ ደርሶ 2 ይቀራል። አዋጅ አለን “አሐደ አዕትት ለዘመን - አንዱን ለዘመኑ ስጥ ወይም አስቀር” ይላል ስለዚህ ከሁለት ላይ አንድ ሲነሳ አንድ ይቀራል። የ2007 ወንበር አንድ ነው ማለት ነው። አበቅቴውን ለማግኘት ከጥንተ አበቅቴ ጋር እናባዛዋለን።
ጥንተ አበቅቴ 11 እና ወንበር ሁለቱን ስናባዛ /11 × 1/ = 11 ይሆናል። ስለዚህ የ2007 ዓ.ም አበቅቴ 11 ወጣ እንላለን።
2. አበቅቴን በአጭር መንገድ ማውጣት
አበቅቴን በአጭር መንገድ ማውጣት የምንችል ሲሆን ይኸውም የዘንድሮውን አበቅቴን አወቅነው ማለት የሚቀጥለውን ዓመት አበቅቴን እናውቀዋለን ማለት ነው። ምክንያቱም በጸሐይና በጨረቃ መካከል ያለው ልዩነት አስራ አንድ ነው ብለናል። ይህንን አስራ አንድ በየዓመቱ በአበቅቴው ላይ ብንደምረው የየዘመኑን አበቅቴ እናገኛለን ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ዓለም በተፈጠረበት በመጀመሪያው ዓመተ ዓለም አበቅቴ አስራ አንድ ነበር። በሁለተኛው ዓመት 22፣ በሶስተኛው ዓመት 33 /በሰላሳ ስንድፈው/ 3 ይቀራል፤ በአራተኛው ዓመት /3 + 11/ 14፣ በአምስተኛው ዓመት /14+11/ 25 ነው። ስለዚህ ያለፈውን ዓመት አበቅቴ ካወቅነው የዘንድሮን፣ የዘንድሮውን ካወቅነው የሚቀጥለውን ዓመት አስራ አንድ በመጨመር እናገኘዋለን ማለት ነው።
ምሳሌ 2፦2005ን ዓ.ም አበቅቴን ለማግኘት የ2004 ዓ.ም አበቅቴ ላይ አስራ አንድ እንደምራለን ማለት ነው።
በቅድሚያ ከላይ በቁጥር አንድ ላይ ባየነው መንገድ ማለትም በወንበር የ2004ን አበቅቴን እናግኝ! የ2004ን አበቅቴን በወንበር ለማውጣት በቅድሚያ ዓመተ ምህረቱንና ዓመተ ዓለሙን እንደምራለን። /5500
+ 2004 / = 7504
ይሆናል። ይህንን ለዐቢይ ቀመር /532/ እናካፍለዋን። 7504 ÷ 532 = 14 ጊዜ ደርሶ 56 ይቀራል። 56 ለማዕከላዊ ቀመር /ለ76/ መካፈል ስለማይችል ለንዑስ ቀመር /ለ19/ እናካፍለዋለን። 56 ÷ 19 = 2 ጊዜ ደርሶ 18 ይቀራል። አሐደ አዕትት ለዘመን - አንዱን ለዘመኑ ስጥ በሚለው አዋጅ ከ18 ላይ አንድ ስንቀንስ 17 ይቀራል። የ2004 ዓ.ም   ወንበር 17 ነበር ማለት ነው። ስለዚህ አበቅቴውን ለማውጣት ጥንተ አበቅቴን ከወንበር ጋር እናባዛዋለን /17 × 11/ 187 ይሆናል። 187ን በ30 ስንገድፈው ወይም ለ30 ስናካፍለው /187 ÷ 30/ = 6 ጊዜ ደርሶ 7 ይቀራል። ስለዚህ የ2004 ዓ.ም አበቅቴ 7 ነበር ማለት ነው። 
እንግዲህ የ2005ን አበቅቴ ለማግኘት የ2004 አበቅቴ ላይ አስራ አንድ መደመር ነው ብለናል። ስለዚህ የ2004 አበቅቴ 7 ነው፤ 7 ላይ 11 ስንደምር 18 ይሆናል። የ2005 ዓ.ም አበቅቴ አስራ ስምንት ነው ማለት ነው።
ምሳሌ 3፦ ከላይ የ2007 ዓ.ምን አበቅቴን በምሳሌ አንድ ላይ አግኝተናል። ይኸውም 11 ነው። እንግዲህ የ2008 ዓ.ምን አበቅቴ ለማግኘት ደግሞ ያለፈው ዓመት አበቅቴ ላይ አስራ አንድ መደመር ነው። ስለዚህ የ2007 ዓ.ም አበቅቴ 11 ከሆነ የ2008 ዓ.ም አበቅቴ 11 ጨምረንበት 22 ይሆናል ማለት ነው።
ማስታወሻ
ዘመን ሲቆጠር በጸሐይ ብቻ ሳይሆን በጨረቃም ይቆጠራል። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ስለ አዕዋዳት ስንማር አንድ አውደ ዓመት የሚባለው በጸሐይ 365 ቀን ከ15 ኬክሮስ ሲሆን በጨረቃ ደግሞ 354 ቀን ከ22 ኬክሮስ ነው። በወርም ደረጃ አንድ ወር የሚባለው በጸሐይ ሙሉ 30 ቀናት ሲሆን በጨረቃ ግን አንድ ጊዜ 30 እንድ ጊዜ ደግም 29 ይሆናል። ይህም ማለት ስድስት ወራት ሙሉ ሠላሳ ቀናት፤ ስድስት ወራት ደግሞ ሃያ ዘጠኝ ቀናት ማለት ነው። ወደ ቀናት ስንመነዝረው 6 ×30 = 180 እና 6 × 29 = 174 ይሆንና ሁለቱ ሲደመር /180 + 174/ 354 ይሆናል። ይህም የጨረቃ አንድ አውደ ዓመት ማለት ነው። ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ እስከ ዛሬ ማለትም 2005 ዓ/ም ድረስ ስንት አውደ ጨረቃ እንደ ሆነ ማወቅ ይኖርብናል። 
ይህንን ለማወቅ አንድ አውደ ጸሐይ 365 ቀናት ነው። በሁለቱ መካከል ማለትም በፀሐይና በጨቃ መካከል የአስራ አንድ ቀን ልዩነት አለ ብለናል።እነዚህ አስራ አንድ ቀናትን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ሰብስበን ለአውደ ጨረቃ /ለ354/ ብናካፍለው የመሬትን ዕድሜ በጨረቃ እናገኘዋለን ማለት ነው።
አሁን ያለነው በፀሐይ 2005 ዓ.ም ነው። ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ካለው ዘመን /5500/ ጋር ስንደምረው 7505 ዓመተ ዓለም ይሆናል። ይህም የዓለም ዕድሜ በፀሐይ ማለት ነው። የጨረቃን ለማግኘት በእያንዳንዱ ዓመት ላይ ጨረቃ ፀሐይ ላይ ለመድረስ 11 ቀናት ስለሚቀራት እነዚህን ቀናት ስንሰበስባቸው 7505 × 11 = 82᎖555 ይሆናል። ይህንን ለዓውደ ጨረቃ ስናካፍለው /82᎖555 ÷ 354/ = 233 ዓመት ሆኖ 73 ይቀራል። ይህም ማለት 233 ዓመት ከ73 ቀናት ማለት ነው። በፀሐይና በጨረቃ መካከል ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የ233 ዓመት ከ73 ቀናት ልዩነት አለ ማለት ነው። ይህንን 233 ዓመት ዓመተ ዓለሙ ጋር ስንደምረው /7505 + 233/ = 7738 ዐውደ ጨረቃ ይሆናል። ወይንም የመሬት ዕድሜ በጨረቃ 7738 ዓመተ ጨረቃ ነው ማለት ነው::

1.3 አበቅቴ ተረፈ ዘመን ነው ስንል ምን ማለት ነው?
እንደሚታወቀው አበቅቴ በጨረቃና በፀሐይ መካከል ባለ የጉዞ ልዩነት ጋር የተያያዘ ነው። አበቅቴን ተረፈ ዘመን ነው ስንልም ጨረቃ ጉዞዋን ፈጽማ ካቆመችበት ቀን አንስቶ ፀሐይ ጉዞዋን እስከምትፈጽምበት /ጳጉሜን አምስት/ ቀን ድረስ ያሉት ቀናት ተረፈ ዘመን ወይም አበቅቴይባላሉ። እነዚህ ቀናት ለሚቀጥለው ዓመት አበቅቴ ይሆናሉ። 

ለምሳሌ፦ ጨረቃ የ2003 ዓ.ም ጉዞዋን የፈጸመችው ነሐሴ 28/ 2003 ዓ.ም ነው። ስለዚህ ከነሐሴ ሃያ ዘጠኝ ቀን ጀምሮ እስከ ጳጉሜን አምስት ቀን ያሉ ቀናት ሰባት ናቸው። ይህ ሰባት ተረፈ ዘመን ሲሆን ለሚቀጥለው ዓመት ማለትም ለ2004 ዓ.ም አበቅቴ ይሆናል ማለት ነው።
ይህንን ያገኘነው ከላይ ከዚህ ቀደም ሲል ዓውደ አበቅቴ ወይም ንዑስ ቀመር ስንመለከት በአስራ ዘጠኝ ዓመት አንድ ጊዜ ፀሐይና ጨረቃ በተፈጠሩበት ኆኅት /መስኮት/ ውስጥ በተራክቦ ያድራሉ ብለናል። ይህ ማለት በዚህን ዓመት ፀሐይና ጨረቃ ዑደታቸውን በአንድ ላይ ስለሚጀምሩ በመካከላቸው የሚኖር ልዩነት የለም ማለት ነው። ስለዚህ አበቅቴው አልቦ ወይም ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ዓመት ፀሐይና ጨረቃ ዑደታቸውን መስከረም አንድ ቀን ይጀምራሉ።
          ለምሳሌ በ1987 ዓ.ም ወንበሩ ዜሮ ስለነበር አበቅቴው አልቦ ወይም ዜሮ ነበር። ከዚህ ዓመት ጀምሮ በእንድ አውደ ጨረቃ ወይም 354 ቀን እያዞርን ብንመጣ በ2003 ዓ.ም ጨረቃ ጉዞዋን ነሐሴ 27/2003 ዓ.ም ትፈጽማለች። ስለዚህ ከነሐሴ 29 ቀን ጀምረን እስከ ጳጉሜን አምስት ቀን ያሉት ሰባት ቀናት የ2004 ዓ.ም አበቅቴ ነበር ማለት ነው።
አበቅቴ ዜሮ ከሆነበት ቀን አንስቶ አስራ አንድ ቀን እየደመርን ብንመጣም የየዘመኑን አበቅቴ ማግኘት እንችላለን። ይህ አበቅቴ ሁልጊዜ በየአስራ ዘጠኝ ዓመት ተመሳሳይ ነው። አስራ አንድ ጥንተ አበቅቴ መሆኑን ወይም በፀሐይና በጨረቃ መካከል ያለ የአንድ ዓመት ልዩነት መሆኑ መረሳት የለበትም። ከዚህ ቀጥለን የአንድ አውደ አበቅቴ ወይም የአስራ ዘጠኝ ዓመት አበቅቴን እንመለከታለን

1.1987 ዓ.ም አበቅቴ ዜሮ ነበር። 
2. በ1988 ዓ.ም 0 + 11 = 11
3.1989 ዓ.ም 11 + 11 = 22
4. 1990 ዓ.ም 22 + 11 = 33 ፤ በ30 ስንገድፈው አበቅቴው 3 ይሆናል።
5. 1991 ዓ.ም 3 + 11 = 14 
6. 1992 ዓ.ም 14 + 11 = 25
7. 1993 ዓ.ም 25 + 11 = 36 ፤ በ30 ስንገድፈው አበቅቴው 6 ይሆናል።
8. 1994 ዓ.ም 6 + 11 = 17
9. 1995 ዓ.ም 17 + 11 = 28
10.1996 ዓ.ም 28 + 11 = 39 ፤ በ30 ስንገድፈው 9 ይሆናል።
11.1997 ዓ.ም 9 + 11 = 20
12. 1998 ዓ.ም 20 + 11 = 31 ፤ በ30 ስንገድፈው 1 ይሆናል።
13. 1999 ዓ.ም 1 + 11 = 12
14. 2000 ዓ.ም 12 + 11 = 23
15. 2002 ዓ.ም 23 + 11 = 34 ፤ በ30 ስንገድረፈው 4 ይሆናል።
16. 2002 ዓ.ም 4 + 11 = 15 
17. 2003 ዓ.ም 15 + 11 = 26
18. 2004 ዓ.ም 26 + 11 = 37 ፤ በ30 ስንገድፈው 7 ይሆናል።
19. በ2005 ዓ.ም 7 + 11 = 18 
በ2006 ዓ.ም 18 + 11 = 29 ይሆናል
አበቅቴው ሃያ ዘጠኝ ከሆነ መጥቅዕ አንድ ይሆናል። እዚህ ጋር አንድ አዋጅ ወይም የሐዋርያት ትዕዛዝ አለን። ይኸውም “ወኢይኩን አሐደ መጥቅዕ ለዘመን - ለዘመን አንድ መጥቅዕ አይሁን” ስለሚል አንድ መጥቅዕ አይሆንም። መጥቅዕ ደግሞ አንድ ከሆነ በዚህ ዘመን አበቅቴው አልቦ ወይም ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። እንዲሁም ከላይ እንዳየነው በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ፀሐይና እና ጨረቃ በተራክቦ ስለሚያድሩ ከ1987 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ያለው ዓመት አስራ ዘጠኝ ሲሆን አንድ አውደ አበቅቴ ያበቃል። በ2006 ዓ.ም እንደገና ተመልሶ አበቅቴው ዜሮ ይሆንና ሌላኛው አውደ አበቅቴ ዑደት ይጀምራል። በሌላም መንገድ ማለትም ወንበር በምናወጣበት መንገድ የ2006 ዓ.ም ወንበርን ብናወጣ ወንበሩ ዜሮ ነው የሚሆነው። ወንበሩ ዜሮ ከሆነ ደግም አበቅቴውም ዜሮ ይሆናል።

2007 ዓ.ም ጀምሮ አበቅቴው አስራ አንድ በመሆን ከላይ ባየነው መንገድ አስራ ዘጠኝ ዓመት እስከሚሞላው ድረስ በተመሳሳይ መልኩ ይቀጥላል።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ጨረቃ ጉዞዋን የምትፈጽምበትን ቀን ለማወቅ ያለፈውን ዓመት ጉዞዋን ካቆመችበት ጀምረን ለ354 ቀናት እንቆጥራለ። ይህንንም በአጭር መንገድ መቁጠር የምንችል ሲሆን የጨረቃ ወርኃዊ ዑደት አንድ ጊዜ 29 አንድ ጊዜ 30 ቀን ነው። ይህንን በአስራ ሁለት ወራት ብናባዛው 354 ቀናት ይሆናል። አንድ ጊዜ 29 አንድ ጊዜ 30 የምናደርግበት ምክንያት እንደሚታወቀው በሳይንሱ “the moon rotates around the sun twenty nine and half days – ጨረቃ በፀሐይ ዙሪያ ሃያ ዘጠኝ ከግማሽ ቀናት ትዞራለች” ይላል። በቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ግማሽ ቀን የሚባል አቆጣጠር የለም። ሃያ ዘጠኝ ቀናት ሞልቶ ከሚቀጥለው ሰከንድ ጀምሮ ወደሚቀጥለው ቀን ይቆጠራል እንጂ ለብቻው ግማሽ ቀን አይባልም። ስለዚህ ሃያ ዘጠኝ የሚለው ለብቻው ይቆጠርና የቀረው ግማሽ ቀን ከሚቀጥለው ወር ግማሽ ቀን ጋር አብሮ ይደመርና ሙሉ ሠላሳ ቀናት ይሆናል።
 በዚህ መሰረት ጨረቃ አንድ ወር 29 ቀናት በሚቀጥለው ወር 30 ቀናት በማድረግ ለአስራ ሁለት ወራት ስትመላለስ 354 ቀናት ይሆናል። ይህ ማለት ስድስት ወራት 29 ቀናት /6 × 29 =  174/፤ ስድስት ወራት ደግሞ ሙሉ ሰላሳ ቀናት /6 × 30 = 180/ ሲሆን በድምሩ /174 + 180/ 354 ቀናት ይሆናል። ይህንን በምሳሌ መመልከት ተገቢ ስለሆነ ከላይ ፀሐይ የ2003 ዓ.ም ጉዞዋን ነሐሴ 28/ 2003 ዓ.ም ፈጽማ የ2004 ዓ.ም ጉዞዋን ነሐሴ 29/ 2003 ዓ.ም ጀምራለች ብለናል። የሚቀጥለውን ዓመት ማለትም የ2005ን አበቅቴ በተረፈ ዘመን ለማግኘት በቅድሚያ ከነሐሴ 29 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምረን ለ354 ቀናት በመዞር የምትፈጽምበትን ቀን እናገኛለን።

ምሳሌ፦
1. ከነሐሴ 29 አስከ መስከረም 22 /ጳጉሜን ጨምሮ/         29 ቀን ይሆናል፤
2. ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 22                    ሙሉ 30 ቀን ይሆናል፤
3. ከጥቅምት 23 እስከ ህዳር 21                                 29 ቀን ይሆናል፤
4. ከህዳር 22 እስከ ታህሳስ 21                            ሙሉ 30 ቀን ይሆናል፤
5. ከታህሳስ 22 እስከ ጥር 20                                    29 ቀን ይሆናል፤
6. ከጥር 21 እስከ የካቲት 20                              ሙሉ 30 ቀን ይሆናል
7. ከየካቲት 21 እስከ መጋቢት 19                                    29 ቀን ይሆናል።
8. ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዚያ 19                         ሙሉ 30 ቀናት ይሆናል።
9. ከሚያዚያ 20 እስከ ግንቦት 18                                     29 ቀናት ይሆናል።
10. ግንቦት 19 እስከ ሰኔ 18                                    ሙሉ 30 ቀናት ይሆናል።
11. ከሰኔ 19 እስከ ሐምሌ 17                                           29 ቀናት ይሆናል።
12. ከሐምሌ 18 አስከ ነሐሴ 17                                ሙሉ 30 ቀናት ይሆናል። 

እንግዲህ ጨረቃ የ2004 ዓ.ም ጉዞዋን ነሐሴ
28/ 2003 ዓ.ም ጀምራ ከ354 ቀናት በኋላ ነሐሴ 17/2004 ዓ.ም ፈጽማለች። ስለዚህ ከነሐሴ 18 ጀምሮ እስከ ጳጉሜን አምስት ቀን ያሉ ቀናት ተረፈ ዘመን ይባላሉ። ከነሐሴ 18 እስከ ጳጉሜን አምስት ድረስ 18 ቀናት ናቸው። ስለዚህ 18 ለቀጣዩ  ዓመት ማለትም ለ2005 ዓ. ም አበቅቴ ነው ማለት ነው። ይህንን ቁጥር ከላይ አበቅቴን ለማግኝት በተጠቀምንባቸው መንገዶች ሁሉ የ2005 ዓ.ም አበቅቴ 18 እንደሆነ ተመልክተናል።

ምንጭ፡-
1.        የባሕረ ሐሳብ መጽሐፍ ከመጽሐፈ ሰዓታት
2.      አሥራት ገ/ማርያም፣ የዘመን አቆጣጠር፣ 1987 ዓ.ም.
3.      አቡሻኸር መጽሐፍ፣ 1962 ዓ.ም.
4.      ሐመር መጽሔት
5.  የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሀሳብ /የዘመን አቆጣጠር/ 



8 comments:

  1. እንኮን በደሕና ተመለሰክ ። በርታ!

    ReplyDelete
  2. መሌ እንደዚህ አይነት የተጠቀጠቀ እውቀት ይዘህ ብቻዬን ብለህ አለመቀመጥህ የሚያስመሰግን ነው ግን አንድ ጥያቄ አለኝ አብዛኛው ሙስሊም ወንድሞቻችን የኢትዬጵያን አቆጣጠር የማይቀበሉት ወይም ደስ የማይላቸው ይመስኛል እና በዓላችንን ወይም አቆጣጠራችንን የጋራ እንደሆነ ማስዳት ይቻል ይሆን?

    ReplyDelete
  3. kale hiwoten yasemalen

    ReplyDelete
  4. Melakeu, Endet neh? Minalbat Kastawoskegn Abren Temirenal Arat Killo (Melaku, how are you? If you remember me we were in the same batch in 1994 at AAU science Faculty and then you joined your own faculty. Thank you for your good information that I was in need to know about this information.) May God Bless you

    Tamiru

    ReplyDelete
  5. Amlak yibarkeh wendem ! telek sera new eyeserahew yalehew .pls Keep it up !

    ReplyDelete
  6. Kale Hiwot Yasemalin Melye! Egziabher birtatun yistih!

    ReplyDelete
  7. Thank you very much. God bless you!

    Now, how can we calculate the holidays?

    Thanks again.

    ReplyDelete