Wednesday, September 11, 2013

የዘመን አቆጣጠር ባሕረ ሐሳብ -ክፍል 4 -ወንበር

ወንበር
በዓላትንና አጽዋማትን ለማውጣት ከሚያስፈልጉን ነገሮች ውስጥ አንዱ መጥቅዕ ሲሆን በዓላትና አጽዋማት የሚያድሩባቸውን ሌሊት የሚያሳውቀን ደግሞ አበቅቴ ነው። አበቅቴና መጥቅዕ በየዘመኑ የሚቀያየሩ ስለሆነ ሁልጊዜ ማለትም በየዓመቱ የየዘመኑን አበቅቴና መጥቅዕ ማውጣት ይኖርብናል። እንግዲህ ወንበር እነዚህን አበቅቴንና መጥቅዕን የምናወጣበት ቁጥር ነው። ወንበር የሚለው ስያሜ የተገኘው አበቅቴም ሆነ መጥቅዕ /ለበዓላትና ለአጽዋማት መገኘት ወሳኙ የሆኑ ነገሮች/ የሚገኝበት ከመሆኑም በላይ ዓመቱን ሙሉ ቀሚ በመሆን የሚያገለግል ቁጥር ስለሆነ ነው።
ንበር እንዴት ይወጣል?
ወንበርን በተለያየ መንገድ ማውጣት የምንችል ሲሆን ሊቃውንት አባቶቻችን እንደ ዛሬው የሂሳብ መቀመሪያ መሳሪያዎች ሳይኖሩ የሂሳብ ስሌቶችን የሚሰሩት በቃላቸው ነበር። አሁንም አብዛኛዎቹ በቃላቸው ነው የሚሰሩት። ለምሳሌ አንድን ትልቅ ቁጥር ለሆነ ቁጥር ማካፈል ቢፈልጉ /ለምሳሌ 7450ን ለ532 ለማካፈል/ የሚጠቀሙት እንደኛ ካልኩሌተር ሳይሆን በቃላቸው ነው የሚያካፍሉት። በዚህን ጊዜ ይንን ትልቅ ቁጥር ለማካፈል የተለያዩ መንገዶችነ ይጠቀማሉ። ስለዚህ ይህንን የአባቶችን ትውፊት መተው ተገቢ ስላልሆነ እንዲሁም አንዱም መንገድ በመሆኑ እንመለከተዋለን። ሌላው ደግሞ ዘመኑ የሰጠንን አጭር መንገዶችንም መጠቀሙ ለስራችን ቅልጥፍና የሚሰጠው በመሆኑ በዘመናዊ መንገድ በማለት እንመለከተዋለን።
እንደ አበው ሊቃውንትም ሆነ በአሁኑ ሰዓት በቀላሉ ለማውጣት በቅድሚያ ዓመተ ምህረትንና ዓመተ ፍዳን መደመራችንን መርሳት የለብንም። ዓመተ ፍዳ እንደሚታወቀው የሚለዋወጥ አይደለም፤ ሁልጊዜም ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ዓመተ ምህረቱ በየዓመቱ እየጨመረ ስለሚሄድ ሁለቱ በአንድ ላይ መደመር አለባቸው። ተደምሮ የተገኘው ቁጥር ዓመተ ዓለም ወይም የዓለም ዕድሜ ይባላል። ይህንን ዓመተ ዓለም በዐቢይ ቀመር፣ በማእከላዊ ቀመር እና በንዑስ ቀመር በመግደፍ /በማካፈል/ የዘመኑን ወንበር እናገኛለን ማለት ነው። 
ምሳሌ 1፦2005 ዓመተ ምህረትን ወንበር ለማግኘት በቅድሚያ ዓመተ ምህረቱን ከዓመተ ፍዳ ጋር እንደምራለን።
  ዓመተ ፍዳ  ሲደመር  ዓመተ ምህረት 
   5500 + 2005 = 7505 /”ሰባት ሺህ አምስት መቶ አምስት ዓመተ ዓለም/ ይሆናል።
አሁን ሊቃውንቱ ዓመተ ዓለሙን በየቤቱ ይከፍሉታል። የሺህ ቤቱን፣ የመቶ ቤቱን የአስር ቤቱንና የአንድ ቤቱ ለየብቻቸው ይቀመጣሉ። በዚህም መሰረት፦ 7000 ፣ 500 ፣ 5 ይሆናሉ።
ዐቢይ ቀመር 532 ፣ማዕከላዊ ቀመር 76፣ ንዑስ ቀመር 19 ናቸው። ከላይ በየቤቱ ያስቀመጥናቸውን ቁጥሮች እንደ ቅደም ተከተላቸው እናካፍላቸዋለን። ማለትም ሰባት ሺህን ለዐቢይ ቀመር /532/ ተካፍሎ የሚቀረውንና አምስት መቶን በመደመር ለማዕከላዊ ቀመር /76/፣ አሁንም ከዚህ የቀረውንና አምስትን በመደመር ለንዑስ ቀመር /19/ ማካፈል ነው። 
7000 ÷ 532 = 13 ጊዜ ደርሶ 84 ይቀራል። ይህንን ቀሪ እና 500ን በመደመር ለማእከላዊ ቀመር እናካፍላለን።
 500 + 84 = 584
584 ÷ 76 = 7 ጊዜ ደርሶ 52 ይቀራል። ይህንን ቀሪ እና 5ን በመደመር ለንዑስ ቀመር ይካፈላል።
5 + 52 = 57
57 ÷ 19 = 3 ጊዜ ደርሶ ዜሮ ይቀራል። ይህ የሚቀረው ቁጥር ተረፈ ዘመን ይባላል። እዚህ ጋር አንድ አዋጅ አለን።
አዋጅ፦ “አሐደ አዕትት ለዘመን - ለዘመኑ አንድ ቀንስ”
ይህ ማለት ከቀሪው ላይ አንድ በመቀነስ ለዘመኑ ስጥ ማለት ሲሆን የዚህ ምክንያቱ ሊቃውንቱ እንደሚሉት “ስለተጀመረ ተቆጠረ ስላላለቀ ታተተ ወይም ተቀነሰ” በዓላትንና አጽዋማት የሚወጡት መስከረም አንድ ቀን ነው።  እንደትላንት ጳጉሜን አምስት ሆኖ በሚቀጥለው ቀን ዓመቱን መቁጠር እንጀምራለን። ለምሳሌ በዚህ ዓመት ጳጉሜን 5/2004 ብለን ውለን በማገስቱ ግን 2005 ብለናል። ስለዚህ ዓመቱ ስለተጀመረ 2005 ብለን ቆጥረናል። ዓመቱ ግን ገና ለ365 ቀናት ይቆያል። በመስከረም አንድ ላይ ሆነን የምናወጣቸው በዓላት እንኳን ከቆይታ በኋላ የሚከናወኑ ናቸው። ስለዚህ አባቶች እንዳሉት ዓመቱን ስለጀመርነው ቆጥረነዋል ነገር ግን ገና ስላላለቀ ማለትም ለማለቅ ብዙ ቀናት ስለሚፈጅ እዚህ ጋር አንድ እንቀንሳለን ማለት ነው።
በላይኛው ምሳሌ ላይ ቀሪው ዜሮ ሆኗል። ከዜሮ ላይ ደግሞ የሚቀነስ ነገር የለም። ለአሁኑ በሌላ ምሳሌ ነገሩን እናዳብረው።
ምሳሌ 2፦2007ን ወንበር ለማውጣት በቅድሚያ ከዓመተ ፍዳ ጋር እንደምረዋለን።
5500 + 2007 = 7507 ይሆናል። ይህንን በየቤቱ እንከፋፍለዋለን። 7000፣ 500፣ 7 ይሆናል:፡ 
ሀ. 7000ን ለዐቢይ ቀመር /532/ እናካፍለዋለን። 13 ጊዜ ደርሶ 84 ይቀራል
ለ. 500ን እና 84 ደምረን ለማዕከላዊ ቀመር /76/ እናካፍለዋለን። 584 76 ሲካፈል 7 ጊዜ ደርሶ 52 ይቀራል።
ሐ. 7ን እና 52 ደምረን ለንዑስ ቀመር /19/ እናካፍለዋለን። 5919 ሲካፈል 3 ጊዜ ደርሶ 2 ይቀራል። 
እንግዲህ በአዋጃችን መሰረት ማለትም አሐደ አዕትት ለዘመን - አንዱን ለዘመኑ ስጥ በሚለው መሰረት ከቀሪው ላይ አንድ እንቀንሳለን። ቀሪው 2 ሲሆን አንድ ስንቀንስ አንድ ይቀራል። ስለዚህ በ2007 ዓ ዓመተ ምህረት አንድ ወንበር ወጣ ይባላል።
ወደ መጀመሪያው ምሳሌ እንሂድና ቀሪው ዜሮ ነው የሆነብን። ስለዚህ ቀሪው ዜሮ ከሆነ ደግሞ አንድ ስንቀንስ ዕዳ /negative/ ነው የሚሆነው። በዚህን ጊዜ ወንበር የለንም ማለት ነው። ይህ በየአስራዘጠኝ ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚመጣ ሲሆን አንድ አውደ አበቅቴ /19 ዓመት/ ተፈጽሞ ሌላ አውደ አበቅቴ ሊጀምር ነው ማለት ነው። ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት አበቅቴው ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም ስለ አዕዋዳት ስንማር አውደ አበቅቴ 19 ነው ብለናል። 19 የሆነውም ጸሐይና ጨረቃ በተፈጠሩበት መስኮት የሚገናኙበት ነው። አበቅቴ ደግሞ በፀሐይና ጨረቃ ዙረት ምክንያት የሚመጣ ልዩነት ነው። ምክንያቱም ፀሐይ የምትዞረው 365 ቀን ሲሆን የጨረቃ ዐውድ የሚያበቃው ደግሞ በ354 ቀን ነው በዚህ ዑደት መካከል ያለው ልዩነት 11 /አስራ አንድ/ ነው። ይህ አስራ አንድ የመጀመሪያው አበቅቴ ወይም ልዩነት ነው። ለዚህ ነው ድሜጥሮስ ከሌሊቱ 23 ሱባዔ በመግባት አስራ አንድ ጥንተ አበቅቴን ያገኘው።
ስለዚህ በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ግን በአንድ መስኮት ስለሚገናኙ ያን ጊዜ አበቅቴ አይኖርም። አልቦ አበቅቴ ወይም ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ከሚሆንበት አንድ ዓመት ቀድሞ ደግሞ የአበቅቴ ፍጻሜ ይሆናል ማለት ነው። የአበቅቴ ፍጻሜ የሚሆነው ደግሞ ዘንድሮ /በ2005/ ነው። ለዚህ ነው ወንበሩ ከዜሮ ያነሰው። ዜሮ እንኳን አልሆነም ምክንያቱም ወንበር የምንለው ከተረፈ ዘመኑ ላይ አነድ ተቀንሶ ዜሮና ከዜሮ በላይ ሲሆን ነው። አሁን ግን ተረፈ ዘመኑ ራሱ ዜሮ ሆኗል። ከዜሮ ላይ ደግሞ አንድ ብንቀንስ ከዜሮ ያነሰ ወይም ኔጌቲቭ ነው የሚሆነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ አበቅቴና መጥቅዕ እንዴት ይገኛል? የሚል ጥያቄ በአዕምሯችን መምጣቱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም የወንበር ጥቅም አበቅቴና መጥቅዕን ማስገኘት እንደ ሆነ መግቢያችን ላይ አስቀምጠናል። ይህንን ስለ አበቅቴ ስንነጋገር እንመለስበታለን። ይቆየን!    

በሚቀጥለው ስለ አበቅቴ እና መጥቅዕ በተመለከተ እናቀርባለን፡፡

ምንጭ፡-
1.        የባሕረ ሐሳብ መጽሐፍ ከመጽሐፈ ሰዓታት
2.      አሥራት ገ/ማርያም፣ የዘመን አቆጣጠር፣ 1987 ዓ.ም.
3.      አቡሻኸር መጽሐፍ፣ 1962 ዓ.ም.
4.      ሐመር መጽሔት
5.  የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሀሳብ /የዘመን አቆጣጠር/ 

No comments:

Post a Comment