Sunday, April 7, 2013

ገብር ኄር - የአብይ ጾም 6ኛ ሳምንት



 ይህ ሳምንት የዐብይ ጾም ስድስተኛው ሳምንት ሲሆን እንደሌሎቹ ሰንበታትና ሳምንታት ሁሉ ይህም ሳምንት የራሱ የሆነ መጠሪያ አለው:: ገብር ኄር ይባላል:: ትርጓሜውም በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው::በዚህ ሳምንት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈው መልእክት ከባለፈው ሳምንት/ደብረ ዘይት/ የቀጠለ ነው:: የዐብይ ጾም አምስተኛው ሳምንት /ደብረ ዘይት/ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚታሰብበት  ሲሆን ይሄኛው ሳምንት ደግሞ ነቢዩ ዳዊት “እስመ አንተ ትፈድዮ ለኵሉ በከመ ምግባሩ/አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህና/ መዝ 61፡12 እንዳለ ጌታ ዳግም ሲመጣ ለሁላችንም እንደ ሥራችን ዋጋችንን እንደሚከፍለን የምናስብበት ሳምንት ነው::
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ስለ ዳግም ምጽአቱና ስለሚሆነው ምልክት ሲጠይቁት በመጀመሪያ በ70 ዓ ም አካባቢ የሚሆነውን የኢየሩሳሌምን ጥፋት ከዚያም በኋላ እሱ ዳግም ሲመጣ የሚሆኑትን ምልክቶች ከነገራቸው በኋላ ከዚሁ ጋር አያይዞ የእርሱን መምጣት ተከትሎ የሚሆነውን ክስተት በሦስት ምሳሌዎች ለጊዜው ለደቀመዛሙርቱ በመጨረሻ ግን ለሁላችንም እንዲሆን ነግሮናል::
የመጀመሪያው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመውን የጌታውን አደራ በሚገባ በመወጣቱ በጌታው ዘንድ በተመሰገነው በልባሙ ባሪያ ምሳሌነት ለመልካም የሚተጉ ሰዎችን አስደሳች ፍጻሜ፣ እንደዚሁም በተቃራኒው የጌታውን አደራ ችላ በማለት የማይገባ ሥራ በመሥራት ጊዜውን ባባከነው ክፉ ባሪያ ምሳሌነት የቸልተኞችን አስከፊ ፍጻሜ የሚያሳየው ነው (ማቴ 24፡45-51)::
ሁለተኛው የሙሽራውን መምጣት በዝግጅት ይጠብቁ በነበሩ በአምስቱ ብልሆች ደናግላን ምሳሌነት የዝግጁዎችን ስኬታማ ፍጻሜ፣ እንደዚሁም ባልተሟላ ዝግጅት የሙሽራውን መምጣት ሲጠባበቁ በነበሩ በአምስቱ ሰነፎች ደናግላን ምሳሌነት ማስተዋልና ጥንቃቄ በጎደለው ሕይወት የሚኖሩ ሰዎችን ፍጻሜ የሚያሳየው ነው ፡፡ (ማቴ 25፡1-13)
ሦስተኛው ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በተለየ መልኩ በዚህ ሳምንት በይበልጥ የሚታሰቡ ከጌታቸው ዘንድ መክሊትን የተቀበሉ ባሮችን ታሪክ የያዘው ምሳሌ ነው::

በሦስቱም ምሳሌዎች ላይ የምናያቸው ተመሳሳይ ነገሮች አሉ:: ልባሙንም ሆነ ክፉውን ባሪያ በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ጌታ ደናግላኑ የሚጠብቁት ሙሽራ እንዲሁም ለአገልጋዮቹ መክሊትን የሰጠው መንገደኛው ሰው እንደሚመጡ በተናገሩት መሠረት ሁሉም መጥተዋል:: እንደዚሁም ከመጡ በኋላ ሁሉም መምጣታቸውን ሲጠባበቁ ለነበሩ ሰዎች የሚገባቸውን ዋጋ ሰጥተዋቸዋል::
በቅዱስ ወንጌል ላይ እንደተገለፀው አንድ መንገደኛ ሰው መንገድ ከመጀመሩ በፊት ለአገልጋዮቹ ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደየአቅማቸው ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊትን ሰጥቷቸው ሄደ:: አምስት እና ሁለት መክሊት የተቀበሉት በታዘዙት መሠረት በተቀበሉት መክሊት አትርፈው ጌታቸውን ሲጠብቁት አንድ መክሊት የተቀበለው ግን በተቀበለው መክሊት ለማትረፍ ከመውጣትና ከመውረድ ይልቅ መክሊቱን ቀብሮ ጌታውን ይጠብቅ ነበር::
የአገልጋዮቹ ጌታም ከሄደበት ሲመለስ አገልጋዮቹን የሰጣቸውን መክሊት ምን እንዳደረጉበት ጠየቃቸው:: ሁለቱ አገልጋዮች (አምስት እና ሁለት የተቀበሉት) በተሰጣቸው መክሊት ማትረፋቸውን ሲናገሩ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን እንዲሠራበት የተሰጠውን መክሊት እንደቀበረው ተናገረ:: መቅበሩም ብቻ ሳይሆን “አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ሰለፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ” በማለት በጌታው ላይ የማይገባ ንግግርን ተናገረ:: የአገልጋዮቹ ጌታም አደራቸውን ጠብቀው በተሰጣቸው መክሊት ለማትረፍ የደከሙትን አገልጋዮች በጥቂቱ በመታመናቸው በብዙ ሲሾማቸው መክሊቱን የቀበረውን ያንን ሀኬተኛ ባሪያ ግን በተግሳፅ ወደ ውጪ (ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ) እንዲያወጡት አዘዘ:: ማቴ 25፡14-30::
በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ሁለት ነገሮችን እናስተውላለን::
1. እነዚያ አገልጋዮች እያንዳንዳቸው ከጌታቸው ዘንድ መክሊትን ተቀብለዋል:: የአገልጋዮቹ ጌታም አስቀድሞ ለአገልጋዮቹ መሥሪያ መክሊትን ሰጥቷቸዋል:: ትርፉን የጠየቃቸው አስቀድሞ ሥራ ለመጀመር የሚጠቅማቸውን መክሊት ከሰጣቸው በኋላ ነው:: አስቀድሞ ምንም ሳያደርግላቸው ድንገት ትርፍ አልጠየቃቸውም:: ነገር ግን ሁሉም እኩል መክሊትን አልተቀበሉም:: ከላይ እንደተገለፀው የተቀበሉት አንደኛው አምስት አንደኛው ሁለት ሌላኛው ደግሞ አንድ መክሊትን ነው:: ይሄም የሆነው ያለ ምክንያት አልነበረም:: የአገልጋዮቹ ጌታ በእንደዚህ ያለ መልኩ መክሊቱን ያከፋፈላቸው አገልጋዮቹ ያለ ጭንቀት መሥራት በሚችሉበት አቅም ልክ ተቀብለው ውጤታማ እንዲሆኑ ነበር:: ስለዚህ የአገልጋዮቹ ጌታ“ለአያንዳንዱ እንደ ችሎታው” ማቴ 25፡15 ተብሎ እንደተገለጸ ለአገልጋዮቹ የአቅማቸውን ያህል እንጂ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን አልሰጣቸውም:: ጠቅለል ባለ መልኩ እነዚያ አገልጋዮች በመጀመሪያ ከጌታቸው ዘንድ በአቅማቸው ልክ መክሊትን ተቀብለዋል:: የተጠየቁትም ትርፍ እንደ አቅማቸው በተቀበሉት መክሊት መጠን ሊያተርፉት የሚችሉትን ያህል ብቻ ነው::

2. በዚህ የወንጌል ክፍል የምንመለከተው ሌላው ነገር የአገልጋዮቹ ጌታ ከሄደበት ሀገር ሲመለስ አገልጋዮቹ በመክሊቱ ምን እንደሰሩበት ጠይቋቸዋል:: መክሊቱን ለአገልጋዮቹ ካከፋፈለ በኋላ ረስቶት አልቀረም:: እያንዳንዳቸውን ጠይቋቸዋል:: መጠየቁም በመክሊቱ ምን እንዳደረጉበት ሰምቶ ብቻ ለማለፍ አልነበረም:: ነገር ግን መጀመሪያም ቢሆን ለአገልጋዮቹ መክሊቱን የሰጣቸው እንዲያተርፉበት እንጂ ተቀብለው የትም እንዲጥሉት ባለመሆኑ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሰሩበት የጠየቃቸው የመክሊቱን ውጤት ለማየት ካለው ጥልቅ ፍላጎት ነው:: ምክንያቱም የመክሊቱ ባለቤት ለአገልጋዮቹ በፈቃዱ የራሱን ሀብት የሰጣቸው እንደተጠቀሰው እንዲያተርፉበት ነው:: በዚህም ምክንያት ከሄደበት ሀገር ሲመለስ የእያንዳንዳቸውን ትርፍ ጠየቃቸው:: 
የዚህ ምሳሌያዊ ታሪክ ዋና ዓላማ ከጌታ ዳግም ምጽአት በኋላ የሚሆነውን ለእኛ መጠቆም ስለሆነ በዚሁ መልኩ መረዳት ይኖርብናል:: በመክሊቱ ባለቤት ጌታ የተመሰለው እግዚአብሔር ነው:: ከጌታቸው ዘንድ መክሊትን የተቀበሉ አገልጋዮች ደግሞ የእኛ የሰው ልጆች ምሳሌዎች ናቸው:: እነዚያ አገልጋዮች በኋላ የሚጠየቁበት መክሊትን በአቅማቸው ልክ ከጌታቸው እንደተቀበሉ እኛም ጌታ ዳግም ሲመጣ የምንጠየቅበት በአቅማችን ልክ ከጌታችን የተቀበልነው መክሊት (ጸጋ) አለ::
የአንዱ ጸጋ ማሰተማር ሲሆን የሌላኛው ደግሞ መማር ሊሆን ይችላል እንደዚሁም የአንዱ ጸጋ መቀደስ ሲሆን የሌላኛው ማስቀደስ ይሆናል ወዘተ:: ምንም እንኳን የእያንዳንዳችን ጸጋ የተለያየ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ጸጋን ያልተቀበለ ሰው ግን የለም::ስለዚህ ሁሉም እንደተሰጠው ጸጋ መጠን ኃላፊነት አለበት:: ስለዚህ ጌታ ዳግም ሲመጣ እያንዳንዳችንን በሰጠን ጸጋ ምን እንደሰራንበት ይጠይቀናል:: 
እዚህ ላይ እያንዳንዳችን በተሰጠን ጸጋ ምን እንደሠራንበት ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ እንደሚጠይቀን ማስተዋል ይገባናል:: በተሰጠው ጸጋ ያልሠራበት ሰው በምንም ዓይነት ምክንያት ከተጠያቂነት አያድነውም:: ምክንያቱም ከአምላካችን የተቀበልነው ጸጋ ውጫዊ ተጽእኖዎችን መቋቋም የምንችልበት ኃይላችን ነው::
ስለዚህ እግዚአብሔር በቸልተኝነታችን ለሚያጋጥመን ውድቀት ምክንያትን ብናቀርብ አይቀበለንም:: ይሄንን በቀዳማዊው ሰው አዳም ማየት እንችላለን:: አዳም የአምላኩን ሕግ እንዲተላለፍ ያደረገችው ረዳት ትሆነው ዘንድ የተሰጠችው ሔዋን እንደሆነች ተናግሯል:: ሔዋንም በተራዋ በእባብ አመካኝታ ነበር:: እግዚአብሔር ግን የሁለቱንም ምክንያት አልተቀበላቸውም:: ነገር ግን እግዚአብሔር ምክንያታቸውን ያልተቀበላቸው ያቀረቡት ምክንያት ሀሰተኛ በመሆኑ አልነበረም:: ምክንያቱም አዳምን ሔዋን እንዳሳተችው ሔዋንን ደግሞ እባብ እንዳሳተቻት አይቷል:: ነገር ግን እግዚአብሔር የአዳምንም ሆነ የሔዋንን ምክንያት ያልተቀበለው የውድቀታቸው ዋነኛ መንስኤ የመጣባቸውን ፈተና መቋቋም የማይችሉ ደካማ ፍጡራን ሆነው ሳይሆን ከእርሱ የተቀበሉትን ጸጋ (ፈተናዎቹን ድል መንሳት የሚችሉበትን ኃይል) ከንቱ በማድረጋቸው እንደሆነ ስለሚያውቅ ነበር:: ስለዚህ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለውድቀት የተዳረጉት ጸጋቸውን (ኃይላቸውን) መጠቀም ባለመቻላቸው ወይንም መክሊታቸውን ስለቀበሩ ነበር::
በዚህም ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ ችላ እንዳንል ለማነቃቃት በየዓመቱ በዚህ ሳምንት የእነዚህን አገልጋዮች ታሪክ ታስታውሰናለች:: ይህም ብቻ ሳይሆን የአገልጋዮቿ ፍጻሜ እንደተመሰገኑት እንደ ሁለቱ አገልጋዮች እንዲሆንም ወደ አምላኳ ትጸልያለች:: ለካህናት በሚደረገው ጸሎተ ፍትሐት የምናስተውለው ይህንን ነው:: ካህን ሲያርፍ የሚነበበው ይሄ የባለአምስቱ እና የባለሁለቱ መክሊት አገልጋይን ታሪክ የያዘው የወንጌል ክፍል ነው:: ነገር ግን ምንባቡ አንድ መክሊት የተቀበለው ሰው ጋር ሳይደርስ ይቆማል:: የዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የካህኑን አገልግሎት መልካም ዋጋን እንዳገኙ እንደ ሁለቱ ታማኝ አገልጋዮች እንዲያደርግለት ስትማጸን ነው::
በአጠቃላይ ሁላችንም እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ መጠን እየሰራን ጸጋውን እንዲያበዛልን ደግሞ ልንማጸነው ይገባል:: የእናት ቤተ ክርስቲያንም ፍላጎት ይሄ ነው:: በሳምንቱ ታሪካቸው የሚወራው የታማኞቹ አገልጋዮች ብቻ አልነበረም እንደዚሁም የሀኬተኛው ባሪያም ታሪክ ይወሳል:: ነገር ግን ሳምንቱ ገብር ኄር ተብሎ መታሰቢያ የሆነው ለሰነፉ አገልጋይ ሳይሆን ለበጎዎቹ አገልጋዮች መሆኑ የቤተ ክርስቲያንን ጉጉት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል::

የዕለቱ መዝሙር እና ምንባባት ከመጽሐፈ ግጻዌ
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም:- ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡

መልዕክታት
(2 ጢሞ.2÷1-15) ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡ ............
(1 ጴጥ.5÷1-11) እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡  ......... 

ግብረ ሐዋርያት
(የሐዋ.1÷6-8) እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸውአብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

ምስባክ
መዝ. 39÷8 "ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"

ትርጉም አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ

ወንጌል
(ማቴ. 25÷14-30) “መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ” .......
ቅዳሴ: - ቅዳሴ ዘባስልዮስ


“መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ/ ጌታውን በመልካም ምግባር የሚጠብቀው በጎ አገልጋይ ማን ነው? እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ ታማኝ አገልጋይ  (ገብር ኄር)  ሆነን ሠላሳ ፤ ስድሳ እና መቶ ፍሬ አፍርተን የመንግሥቱ ወራሾች የስሙ ቀዳሾች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት ፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን -አሜን

7 comments:

  1. kale hiwoten yasemalen

    ReplyDelete
  2. Kale hiwote yasemalin .... Egizabher yibarkih bizu asawikehenal...

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልኝ…

    ማከያ!

    ቤተክርስቲያን ብዙ የምትገለገልበት ዘርፍ አላት፣ it doesn’t have to be ስብከት፣መዝሙር፣ወዘተ፣ በኔ ጠባብ አመለካከት፣ ወጣ ብለንም ቤተክርስቲያንን በተማርንበት ፕሮፌሽን ማገልገል የውዴቴ ግዴታ እንዲሆ ያስፈልገዋል፣ እንዲህ ስል ደግሞ ከወንዶች በተሻለ ሴቶች የበለጠ ተሳታፊ የሚሆኑበትና ብዙ ትሩፋት የሚሰሩበትን ሁኔታም ይመለከታል፡፡ ምን ትሉኝ እንደሆነ ብዙም ባይሆን አልፎ አልፎ ለመስራት ሲመከር እንደሚስተዋለው…በ ኢንጂነሪንግ(ሜካኒካል፣ኤሌክትሪካል፣ዋተር፣ሶይል፣ሲቪል….ወዘተ)፣ በ አንትራፕሪነር ፊልድ(ቤተክርስቲያንና በውጧ የሉትን ልጆቿን ቢዝነስ ፈጣሪ አድርጎ የሚገለገሉባትን ደብር ከዘውትር ለመና ማዳን)፣ በቪደዎ ኦዲዎ ኤዲቲንግ መንፈሳዊ ይዘት ያለቸውን ከእንደነ ዳንኤል ክብረት የመሳሰሉ የትንሽ ትልቅ ምሁራን ጋር በመተባበር ፊልሞችና ዶኪመንተሪዎች ማዘጋጀት፣ ፖለቲክስ( በዚህ እንኳን አንታማም፣ ግን ከዘር፣ከጉቦ፣ ከመድሎ ከመሳሰሉት ነጻ በሆነ መልኩ ቤተክርስቲያን ተከብራ እንድትኖር ማስቻል....ለምሳሌ ዲፕሎማቶች ወይም ከፍተኛ የመንግስት አካላት ላይ ያሉ ምሁራን ክርስቲያኖች ካሉ እንደ ዋልድባ አይነት የድፍረት ስራ እንዲቆም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ…ወዘተ…)፣ በ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዙርያ ለምሳሌ አንድን አጥቢያ ከአንድ አጥቢያ፣ አንድ ከተማ የሉትን አቢያተ ክርስቲያናት ከሌላ ክፍለ ሃገር ካሉ አቢያተ ክርስቲያናት ጋር በኔትወርክ ማከናኘት፣ ትልቁ የቤተክርስቲያን ችግር ደግሞ በዘመናዊና በተማረ መልኩ አስተዳደርን ማድረግ በዚህ ረገድ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም በማማከር ደረጃም ሊሆን ይችላል ግን የማኔጅመንት ምሁራን የሆነችሁ ምን እናድርግ ብሎ ለመሳተፍ መሞከር….ከሰንበት ትምህርት ቤትና ከሰበካ ጉባኤ ተመራጭነት መጀመር የሚቻል ይመስለኛል)፣ ቲቺንግ ምሩቃን በ አይቲ እና በሌሎችም ፊልድ like ማትስ ፊዚክስ ኬሚስትሪ፣ ወዘተ ሰንበት ትምህርት ቤት በመከታተል ላይ የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች በፕሮግራም ማስጠናትና ለትልቅ ማዕረግ ማብቃት ሊሆን ይችላል…….
    እግዜር እኛን በጤና ለዚህ እውቀት ደረጃ ካበቃን እኛ ደግሞ በዚህ ሥላሴ በሰጠን እውቀት እንደ ግብጽ እስክንድርያ አቢያተክርስቲያናትና ገዳማት በተክርስቲያናችንን አሁን ካለችበት በተሻለ ከፍ ማድረግ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ እየተሞከረ ሊሆን ይችልላል ግን በእውነት ለመናገር ከልብ ብንሞክር ከዚህ የተሻለ መሆንና ማገልገል እንችላለን፡፡

    ReplyDelete
  4. የእግዚአብሔር ቸርነት ፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን -
    አሜን!
    አሜን!
    አሜን!
    03/28/2012 @ 1:28PM

    ReplyDelete
  5. Kale hiwot yasemalin! Beselam betena yitebikilin!

    ReplyDelete
  6. Egziabher tsegawn yabzalih.

    ReplyDelete
  7. ይድረስ ለሆሳዕና ወንድሜ፤ ጥቆማህ መልካም ነው።ቅንም ሐሳብ ነው ። ማከል የፈለኩት savewaldba.org
    አና በሌላውም መስክ የማሕበረ ቅዱሳን ድሕረ ገጽ በሙሉ ከተከታተልክ መልስ ታገኛለሕ ። እናንተም፤ እኛም እነሱም ፤አልተኛንም። የቤተክርስቴያናችን አምላክ ይርዳ። በዚሕ አጋጣሜ እንደ ዲ/ን መላኩ ዓይነት ወንድሞች ሊመሰገኑ ፤ ሊበረታቱ ይገባል። የድንግል ልጅ ቤተክርስቲያናችን ይጠብቅ።

    ReplyDelete